የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሚያዝያ ወር 2017 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ወር 2018 ዓ.ም. የጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች ሰብአዊ መብቶች ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያደረገውን ክትትልና የለያቸውን ግኝቶች መሠረት በማድረግ ከተለያዩ የፌደራል እና የክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ታኅሣሥ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል።

በውይይቱ የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት፣ የስደተኛ እና ተመላሾች አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ብሔራዊ መታወቂያ ጽሕፈት ቤት፣ ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር (The International Committee of the Red Cross (ICRC)፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (United Nations High Commissioner for Refugees (UNHCR))፣ ጀሱት የስደተኞች አገልግሎት (Jesuit Refugee Service (JRS))፣ የሉተራን የዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን (Lutheran World Federation (LWF))፣ ኦክስፋም (OXFAM)) እንዲሁም ከአዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ጅግጅጋ እና ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤቶች የተወከሉ ተሳታፊዎች፣ የስደተኞች እና የስደተኛ መር ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል። በመድረኩ ኢሰመኮ ከሚያዝያ ወር 2017 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ወር 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ባካሄዳቸው የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ሰብአዊ መብቶች ክትትሎች የተለዩ ግኝቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ክትትሉ በጥንካሬ ከለያቸው ግኝቶች መካከል በበቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች የስደተኞች ምዝገባ መካሄዱ፣ የሰነድ ማጣራት ሂደት መሻሻሉ፣ የዲጂታል መታወቂያ እና ወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት መስፋፋቱ እንዲሁም በመታወቂያ ከቦታ ቦታ መዘዋወር የመቻል ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉ ተጠቅሰዋል። በአንጻሩ ሰነዶችን በፍጥነት በማግኘትና ማሳደስ ረገድ ክፍተት መኖሩ፣ የመዘዋወር መብት እንደ ልዩ ሁኔታ መወሰዱ፣ የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች አላግባብ በፖሊስ የመያዝና ለተራዘመ ጊዜ በእስር የማቆየት እንዲሁም ከፈቃዳቸው ውጭ ወደ መጡበት ሀገር የመመለስ ሁኔታ፣ በፍትሕ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ የቋንቋ ተግዳሮቶች እልባት አለማግኘት፣ ከሕግ ድጋፍ አገልግሎቶች ጋር የተያያዙ ውስንነቶች፣ የፍርድ ውሳኔ አለመተግበር እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መጨመር በክትትሉ የተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።

በውይይቱ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የስደተኞች ቁጥር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፋይናንስ እና ሰብአዊ ድጋፍ መቀነስ፣ በአለም አቅፉ ማሕበረሰብ በኩል ኃላፊነትን የመጋራት ግዴታ በመወጣት ረገድ ክፍተቶች መኖራቸው እንዲሁም የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅሎ መኖር እንደ ብቸኛ አማራጭ መታየቱ በዘርፉ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ በተሳታፊዎች ተነስቷል። በተለይም የፋይናንስና የሰብአዊ ድጋፍ መቀነስ በስደተኞች ምዝገባና ሰነድ ማግኘት፣ በመሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት፣ በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እና በተጋላጭ ቡድኖች ልዩ ጥበቃ ላይ ያለው ጫና ተገልጿል።

በውይይቱ አሳሳቢ ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ምክረ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን በፖሊስ፣ በፍርድ ቤት እና በኢሚግሬሽን አካላት መካከል የቅብብሎሽ ሥርዓትን ማጠናከር እና የመረጃ ልውውጥን መደበኛ ማድረግ፣ ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎች አማራጭ የማቆያ ቦታዎችን እና መፍትሔዎችን ማዘጋጀት፣ ተጋላጭ ቡድኖችን መለየት እና መደገፍ፣ የዋስትና መብት ተግባራዊ መደረጉን ማረጋገጥ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የመያዝ እና ማቆየት ሁኔታን ማስቀረት፣ ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ የሕግ አፈጻጸምን ለማጠናከር የሚረዱ መመሪያዎችን ማውጣት እንዲሁም የፖሊስ ጣቢያዎችን ክትትል ማጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል።

ብርሀኑ አዴሎ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሀኑ አዴሎ መድረኩ የኢሰመኮ የክትትል ግኝቶችን በግልጽ ለማጋራት፣ በባለድርሻ አካላት መካከል የጋራ መግባባት ለመፍጠር እና በውይይቱ የተነሱ ሐሳቦች ወደ ተግባር የሚያመሩበትን የአሠራር ስልት በጋራ ለመለየት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ የስደተኞችና የጥገኝነት ጠያቂዎች መብቶች ጥበቃ በሀገራዊ እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች መሠረት እንዲተገበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም ኢሰመኮ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መብቶች ጥበቃ ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።