ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር
ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር
በኢሰመኮ አዘጋጅነት የሚካሄደው ውድድር ታዳጊ ተማሪዎች በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያላቸውን ዕውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት ለማሳደግ ታስቦ የሚዘጋጅ ነው
🚨 5ኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለችሎት ውድድር አሁን በመካሄድ ላይ ነው
ሂደቱን ለመከታተል →የምስለ ችሎት ውድድሩ በሕግና ሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች የሚዳኝ ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የሚከተል አስተማሪ የውድድር ዐይነት ሲሆን ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተገቢው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ምናባዊ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ ተመሥርተው አመልካች እና ተጠሪን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት ነው።
ውድድሩ ሁሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች የሚሳተፉበት እና በተለይም የክልል እና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች ትምህርት ቤቶችን እና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን በመምረጥ፣ ክልላዊ የውስጥ ውድድሮች ሲካሄዱ ተማሪዎች እና ሌሎች የት/ቤት ማኅበረሰብ አካላት እንዲከታተሉ በማድረግ እና ውድድሮቹን በማስተባበር የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ በትምህርት ቤቶች እንዲስፋፋ ከኢሰመኮ ጋር በከፍተኛ ትብብር የሚሠሩበት ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡


ኢሰመኮ በሕግ ከተሰጡት ተግባራት እና ኃላፊነቶች መካከል አንዱ ሰብአዊ መብቶችን ማስተዋወቅ እና ማስተማር ነው
የኢሰመኮን ራዕይ ማሳካት
ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት
የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት ማዳበር
ተማሪዎች የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንዲያነቡ፣ እንዲመራመሩ እና ያላቸውን ፋይዳ እንዲረዱ
የሰብአዊ መብቶች ክህሎት ማዳበር
ተወዳዳሪዎች የራሳቸውም ሆነ የሌሎች ሰዎች መብቶች ሲጣሱ ለምን ብለው የሚጠይቁበትን ክህሎት እንዲያዳብሩ
በትምሕርት ቤት ማኅበረሰቡ ላይ የባለቤትነት ስሜት መፍጠር
ከተወዳዳሪ ተማሪዎች በተጨማሪ ውድድሮቹን የሚከታተሉ ሌሎች ተማሪዎች እና የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ አባላት ስለ ሰብአዊ መብቶች ይበልጥ እንዲያውቁ እና ለሌሎች ሰዎች መብቶች እንዲቆረቆሩ
የውድድሩ ሂደት (ይዘት እና ቅርፅ)
ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር በሦስት ደረጃዎች የሚከናወን ነው
ክልላዊ ውድድር
በመጀመሪያ ውድድሩ በክልል ደረጃ ሲደረግ ተወዳዳሪዎች የጽሑፍ መከራከሪያቸውን በማዘጋጀትና በክልል ደረጃ የቃል ክርክር ውድድርን በማድረግ ይጀመራል፡፡ በዚህም ተወዳዳሪዎች በተሰጣቸው ምናባዊ ጉዳይ ላይ በአመልካች እና በተጠሪ (በሁለቱም) ወገን በመሆን የጽሑፍና የቃል ክርክራቸውን ከተለያዩ የሕግ ድንጋጌዎች እና የሰብአዊ መብቶች መርሖች ጋር በማሰናሰል እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡ የውድድሩን ፍትሐዊነት እና ጥራት ለመጠበቅ ሲባል የተሳታፊ ተማሪዎችን ውድድር በየአካባቢያቸው የሚገኙ ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ሕግ እና ሌሎች የሕግ እና ተዛማጅ ባለሙያዎችን በመጋበዝ እንዲዳኙት ይደረጋል፡፡
የጽሑፍ መከራከሪያ ውድድር
በመቀጠልም፣ ከሁሉም ተሳታፊ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በቃል ክርክር 1ኛ በመውጣት አሸናፊ የሆኑ ቡድኖች ለመጨረሻው ሀገር አቀፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ የቃል ክርክር ውድድር ለማለፍ የሚያስችላቸውን የጽሑፍ መከራከሪያቸውን (Essays) ለኮሚሽኑ እንዲልኩ ይደረጋል።
የአሸናፊዎች አሸናፊ የቃል ክርክር ውድድር
በመቀጠልም በኢሰምኮ በሚደረግ የመከራከሪያ ጽሑፍ ምዘና ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ስምንት ቡድኖች ወደመጨረሻው ዙር በማለፍ እና ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት የቃል ክርክር ውድድራቸውን እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡ በዚህም መሠረት የመጨረሻው ሀገር አቀፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ የቃል ክርክር ውድድር በሦስት ዙሮች – (በሩብ ፍጻሜ፣ ግማሽ ፍጻሜ እና ፍጻሜ) ይከናወናል
በሁሉም ደረጃዎች በሚደረጉ ውድድሮች በዳኝነቱ ሂደት ሊከሰት የሚችል ማንኛውንም ዐይነት ወገንተኝነት/አድሎ ለማስቀረት ሲባል የተወዳዳሪዎች የመከራከሪያ ጽሑፎች ልዩ መለያ (ኮድ) ተሰጥቷቸው ለመዛኞች ይተላለፋሉ፡፡ በተጨማሪም በቃል ውድድሩ ወቅት ተወዳዳሪ ቡድኖች በየዙሩ የቡድን ቁጥር እጣ እንዲያወጡ በማድረግ እስከ ውድድሩ ፍጻሜ ድረስ በቡድን ቁጥራቸው ብቻ እንዲታወቁ እና የመጡበት ቦታ ለዳኞች እና ለሌሎች ተሳታፊዎች እንዳይገለጽ ይደረጋል፡፡ በሦስቱም ደረጃዎች አሸናፊ ተማሪዎች በግላቸው እና ተሳታፊ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ዕውቅና እና ሽልማቶች ያገኛሉ።
የምስለ-ችሎት ውድድሩ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ዓመታዊ መርኃ-ግብር ነው
አንደኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር
ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር
ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር
አራተኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር

የውድድሩ ቀጣይነት
የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በትምህርት ሥርዐት ውስጥ እንዲጠናከር በትብብር ለመሥራት ኢሰመኮ እና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም. የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ከዘረዘራቸው ተግባራት መካከል የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት ውድድርን በጋራ ማካሄድ እንደመሆኑ የውድድሩ ተደራሽነት እየሰፋ እና በተሻለ ጥራት እየተከናወነ እንደሚቀጥል የታመነ ነው፡፡
በቀጣይ በሚደረጉ ውድድሮች ላይም በሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር ከዚህ በፊት ያልተሳተፉ ትምህርት ቤቶችን እንዲሳተፉ ለማድረግ፣ እንዲሁም የተወዳዳሪ ትምህርት ቤቶች እና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ቁጥር በየዓመቱ ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት በማጠናከር የውድድሩን ዓላማ ለማሳካት ይሠራል፡፡
ተዛማጅ ዜናዎች

በክልል ደረጃ ሲካሄድ የቆየው 5ኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር ተጠናቀቀ
ውድድሩን በበላይነት ካጠናቀቁት 14 ትምህርት ቤቶች መካከል በጽሑፍ ክርክር የላቀ ነጥብ የሚያስመዘግቡ 8 ቡድኖች በግንቦት ወር በአዲስ አባባ ከተማ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ

ለ5ኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር ተሳታፊዎች የተሰጠ የማስጀመሪያ ስልጠና
ውድድሩ ተማሪዎች ስለ ሰብአዊ መብቶች ዕውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ የሚረዳ ነው

5ኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድርን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተካሄደ ውይይት
የውድድሩ ምናባዊ ጉዳይ “ለልማት ሲባል በግዳጅ ከመፈናቀል ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች” ላይ ያተኩራል

4ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት (Human Rights Moot Court) ውድድር ተጠናቀቀ
ወቅታዊ እና ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎችን ተገንዝቦ አስተዋፆ የማድረግ ዐቅም ያለው ትውልድ በማፍራት ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይቻላል

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: የችሎት አርበኛዋ – DW Amharic
ነዋሪነቷ በሀዋሳ ከተማ የሆነችው የ17 ዓመቷ አዳጊ ናዝራዊት ከበደ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰሞኑን በአገር አቀፍ ደረጃ አዘጋጅቶት በነበረው የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት ውድድር አሸናፊ ሆናለች

ኢሰመኮ የሚያዘጋጀው 3ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት (Human Rights Moot Court) ፍጻሜ ውድድር
ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሰብአዊ መብቶች መርሖች እና እሴቶች የታነጸ ትውልድ ማፍራት አስፈላጊ ነው

የውድድሩ ባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች
የትምህርት ሚኒስቴር በተለይም የክልል እና የከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች ተወዳዳሪ ትምህርት ቤቶችን እና ተማሪዎችን በመምረጥ እና ክልላዊ የውስጥ ውድድሮችን በማስተባበር፣ ውድድሩ በሚካሄደባቸው ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የትምህርት ቤቶች ርዕሰ-መምህራን፣ የተወዳዳሪ ተማሪዎች አሰልጣኝ መምህራን፣ ቤተሰቦች እና በየአካባቢው የሚገኙ የሕግ እና የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች የሚያደርጉት ትብብር ለዝግጅቱ በስኬት መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያደርግ ነው፡፡
በሌላ በኩል ያለፉትን ሦስት ዙር ዓመታዊ ምስለ ችሎት ውድድሮች ለኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች የምስለ-ችሎት ውድድር ዝግጅቱን በገንዘብ በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሲያበረክቱ ቆይተዋል፡፡ ከነዚህም ለጋሽ ድርጅቶች መካከል የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም – United Nations Development Program (UNDP)፣ የጀርመን ኤንባሲ፣ የኖርዌይ ኤንባሲ እና የዴንማርክ ሰብአዊ መብቶች ተቋም – Danish Institute for Human Rights (DIHR) ይገኙባቸዋል፡፡