የኢሰመኮ ባለሞያ አስተያየት
በፋንታሁን መንግሥቴ
የሰብአዊ መብቶች ኦፊሰር
የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች የሥራ ክፍል
የማራካሽ ስምምነት በዋናነት ለዓይነ-ሥውራን እና ሌሎች የሕትመት ውጤቶችን መደበኛ በሆነ የንባብ ስልት ማንበብ ለማይችሉ አካል-ጉዳተኞች (print disabled) በዓለም አቀፍ ደረጃ እያጋጠማቸው ያለውን ‘ረሀበ-ንባብ’ (book-famine) ለመቅረፍና የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እ.ኤ.አ. በ2013 በዓለም የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት (WIPO-World Intellectual Property Organization) አስተባባሪነት በተዋዋይ መንግሥታት የተፈረመ የሰብአዊ መብቶች ሰነድ ነው፡፡ ስምምነቱ በዚሁ ድርጅት ከሚተዳደሩ ዓለም አቀፍ የቅጂ መብት ስምምነት ማዕቀፎች አንዱ ሲሆን፤ የሕትመት ውጤቶችን በተደራሽና አማራጭ ቅርጽ በማመቻቸት የቅጂ ባለመብቶችን የባለቤትነት መብት በማይጋፋ መልኩ በሀገራት የቅጂና ተዛማጅ ብሔራዊ ሕግጋት ላይ ተጨማሪ ገደቦችን እና ልዩ ሁኔታዎችን የሚጨምር ነው፡፡
ስምምነቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1181/2012 የጸደቀ ሲሆን፤ ትምህርት ሚኒስቴርና የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ተግባራዊ እንዲያደርጉና እንዲከታተሉ በማጽደቂያ አዋጁ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል (የማራካሽ ስምምነት ማጽደቂያ አዋጅ ቁጥር 1181/2012 አንቀጽ 3)፡፡
ስምምነቱ ከመጽደቁ በፊት በኢትዮጵያ የቅጂና ተዛማጅ ሕግ መሰረት አንድን የሕትመት ሥራ ለዓይነ-ሥውራንና መደበኛ በሆነ የንባብ ስልት ማንበብ ለማይችሉ ሌሎች ሰዎች ለምሳሌ፡ ወደ ብሬል፣ ድምፅ ወይም ሌላ ተደራሽ ወደሆነ ቅርጽ/ፎርማት ለመቀየር፣ ለማባዛት፣ ለማሰራጨትና ለሕዝብ ለማቅረብ ሲፈለግ የቅጂ ባለመብቷ/ቱን ፈቃድ ማግኘት የግድ ሲሆን፤ ይህ ካልሆነም የፍትሐ-ብሔር እና የወንጀል ኃላፊነት ያስከትል ነበር፡፡ አሁን ግን በስምምነቱ መሰረት የሕትመት ሥራዎች በተደራሽ አቀራረብ ለዚሁ ዓላማ እስከዋሉ ድረስ ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልግም በሕግም አያስቀጣም። (የስምምነቱ አንቀጽ 4 (2) (ሀ))
የማራካሽ ስምምነት ተዋዋይ ሀገራት የሕትመት ሥራዎችን በተደራሽ አቀራረብ ለማዘጋጀት እና ለማሰራጨት እንዲሁም የሥራዎችን ድንበር ተሻጋሪ ልውውጥ ለማመቻቸት የሚያስችሉ የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች ልዩ ሁኔታዎችን ወይም ገደቦችን በብሔራዊ ሕጎቻቸው ላይ እንዲያካትቱ የሚጠይቅ ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት የወጡ የሕትመት ሥራዎችን ወይም በኢትዮጵያ የታተሙ ቅጂዎችን በድንበር ሳይገደቡ ተደራሽ የሕትመት ሥራ ቅጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ወይም ለሌላ ሀገር ተጠቃሚዎች በማሰራጨት ዓለምአቀፍ ትብብርን ያጠናክራል (የስምምነቱ አንቀጽ 5)፡፡ በተለይም ሀገራችን በማደግ ላይ ያለች በመሆኗ ባደጉ ሀገራት በተሻለ ቴክኖሎጂ የተሠሩ ተደራሽ የሕትመት ሥራዎችን ለዓይነ-ሥውራንና በመደበኛ የንባብ ስልት ለማንበብ ለማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለማቅረብ ያስችላል፡፡ ኢትዮጵያ አባል በሆነችበት በተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት መሰረት አካል ጉዳተኞች የመማር እና መረጃን የማግኘት እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር በባሕል፣ በኢኮኖሚ፣ እና በማኅበራዊ ሕይወት በእኩልነት የመሳተፍ መብት አላቸው (የተ.መ.ድ. አካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት)፡፡
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 210/1992 እንደተሻሻለው አንቀጽ 6 (8) መሰረት ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶችን በሃገር ውስጥ ቋንቋዎች የመተርጎም እና የማሰራጨት ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚሁ መሰረት ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ለዓይነ-ሥውራን ብሔራዊ ማኅበር ጋር በመተባበር የማራካሽ ስምምነትን በአማርኛ አስተርጉሞ አሳትሟል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 4 (1) (ሀ) እንደተደነገገው ተዋዋይ መንግሥታት የሕትመት ሥራዎችን በአማራጭ አቀራረብ ተደራሽ የማድረግ፣ የማባዛት፣ የማሰራጨትና ለህዝብ የማቅረብ ግዴታን አስመልክቶ በብሄራዊ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ሕጎቻቸው በልዩ ሁኔታ መደንገግ እና ይህንኑ የሚተገብር የተፈቀደለት አካል ማቋቋም ይጠበቅባቸዋል።(የማራካሽ ስምምነት አንቀጽ 4 (1 እና (2))
በመሆኑም በኢትዮጵያ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብሔራዊ የቅጂና ተዛማች መብቶች ሕጎች አካል የሆነ የማስፈጸሚያ ሕግ ሊወጣለት ይገባል፡፡