የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለ5ኛ ጊዜ ለሚያካሂደው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር የማስጀመሪያ ስልጠና የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በ12 ክልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳደሮች ሰጥቷል፡፡ የስልጠናው ዓላማ የውድድሩን አጠቃላይ ገጽታ ማስገንዘብ እና በዚህ ዓመት ለውድድር የተመረጠውን የሰብአዊ መብቶች ርዕሰ ጉዳይ ለተወዳዳሪ ተማሪዎች እና አሰልጣኝ መምህራን ማስተዋወቅ ነው።



በዚህ ስልጠና ከአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ደሴ፣ ዲላ፣ ድሬዳዋ፣ ግልገል በለስ፣ ሐረር፣ ጅግጅጋ፣ ለኩ፣ መቐለ፣ ሜጢ፣ ሚዛን፣ ሰመራ እና ወልቂጤ ከተሞች ከ105 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተወከሉ ተወዳዳሪ ተማሪዎች፣ የክልል ትምህርት ቢሮ አስተባባሪዎች፣ አሰልጣኝ መምህራን፣ ርዕሳነ መምህራን እና የተማሪ ወላጆች ተሳትፈዋል።



በስልጠናው በዚህ ዓመት የውድድር ምናባዊ ጉዳይ ማለትም “ለልማት ሲባል በግዳጅ ከመፈናቀል ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች (Development based forced eviction and human rights)” ዙሪያ በሚነሱ የሰብአዊ መብቶች ዝርዝር ጉዳዮች እንዲሁም በጽሑፍ እና በቃል ክርክር አቀራረብ መመሪያዎች ላይ ገለጻ ተደርጓል። ስልጠናው ትምህርት ቤቶች እና ተወዳዳሪ ተማሪዎች ለውድድሩ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያግዛቸውን ግብአት ያገኙበት ነበር።



ኢሰመኮ ክልላዊ የምስለ ችሎት ውድድሩን ሚያዚያ 4 እና 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ለማካሄድ ያቀደ ሲሆን በዚህ የውድድር ምዕራፍ የጽሑፍ እና የቃል ክርክር ሂደትን በማለፍ አሸናፊ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የጽሑፍ መከራከሪያ ውድድር ይቀርባሉ።




ኢሰመኮ በየዓመቱ የሚያካሂደው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምስለ ችሎት ውድድር ሰብአዊ መብቶችን በትምህርት ቤቶች ለማስፋፋት ከሚጠቀምባቸው መንገዶች መካከል አንደኛው ሲሆን በትምህርት ቤቶች ያሉ ታዳጊ ተማሪዎች ስለ ሰብአዊ መብቶች ዕውቀት የሚያገኙበት እና መብቶች ሲጣሱ ለምን ብለው የሚጠይቁበትን ክህሎት እንዲያዳብሩ የሚረዳ ነው።