የአካል ጉዳተኞች የተደራሽነት መብት ሲባል ምን ማለት ነው?

ተደራሽነት አካል ጉዳተኞች ከሌሎች ጋር እኩል በሆነ መልኩ ቁሳዊ ከባቢዎችን፣ መጓጓዣዎችን፣ የመረጃ እና ተግባቦት ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ፣ እንዲገለገሉ እና እንዲሳተፉ ማድረግን የሚመለከት ሲሆን፣ አካል ጉዳተኞች ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ እና በሁሉም የሕይወት ዘርፎች የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያስችላል።

ተደራሽነት ራሱን የቻለ መብት ሆኖ በአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት (Convention on the Rights of Persons with Disabilities) እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች ውስጥ የተካተተ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የትምህርት፣ የሥራ፣ በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት፣ በሕዝባዊ ሕይወት ውስጥ የመሳተፍ፣ ፍትሕ የማግኘት እና የጤና የመሳሰሉ ሌሎች የአካል ጉዳተኞች መብቶችን ዕውን ለማድረግ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ነው።

በዚህም ተደራሽነት እኩልነትን እንዲሁም የሁሉንም ሰብአዊ መብቶች ሙሉ እና እኩል ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል።

ለአካል ጉዳተኞች የተደራሽነት መብት ዕውቅና የሚሰጡ ማዕቀፎች የትኞቹ ናቸው?

የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት በአንቀጽ 9 የተደራሽነት መብትን በመደንገግ ምንነቱን በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፣ በአንቀጽ 3 ሥር ከተዘረዘሩት የስምምነቱ 8 መሠረታዊ መርሖዎችም አንዱ አድርጎታል። ስምምነቱ አካል ጉዳተኞች ሁሉንም ሰብአዊ መብቶች እና መሠረታዊ ነጻነቶች በሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የቁሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ከባቢ፣ የጤና እና የትምህርት እንዲሁም የመረጃና ተግባቦት አገልግሎቶች ተደራሽነትን ጠቀሜታ በመገንዘብ፣1 የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች እና መሠረታዊ ነጻነቶች ሙሉ እና እኩል ተጠቃሚነትን ለማስፋፋት፣ ለመጠበቅ እና ለማረጋገጥ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ክብራቸውን ለማጎልበት የወጣ ነው።2 በተጨማሪም የተደራሽነት መብት በሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን (International Covenant on Civil and Political Rights) ዕውቅና ያለው ሲሆን፣ የቃል ኪዳኑ አንቀጽ 25 (ሐ) “ማንኛውም ዜጋ በሀገር ውስጥ ለሕዝብ በተዘረጉ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብትና ዕድል እንዳለው” ይደነግጋል።

ዕድሎችን ሁሉ ለአካል ጉዳተኞች እኩል ለማድረግ የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ደንብ (UN Standard Rules on the Equalization of Opportunities for Persons with Disabilities) በተለይም አካል ጉዳተኞች እንደ ጉዳት አልባ ሰዎች እኩል ተሳትፎ እንዲያደርጉና መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ለማስቻል የሚያስፈልጉ ዕድሎችን ሁሉ እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ ሥራ ወዘተ. ባሉ ወሳኝ ዘርፎች በእኩልነት ማቅረብ እንደሚገባ እና ለዚህም ተደራሽነትን ማረጋገጥ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አጽንዖት ይሰጣል።

በተለያዩ የመብት ዘርፎች የወጡ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችም በየዘርፋቸው ከአካል ጉዳተኞች የተደራሽነት መብት መረጋገጥ ጋር የተያያዙ ግዴታዎችን ያካተቱ ሲሆን፣ ለምሳሌ የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ተደራሽ ያልሆኑ የሕዝብ ማመላለሻዎች፣ የመንግሥት ሕንጻዎች፣ የገበያ ቦታዎች እና ሌሎች መዝናኛ ቦታዎች በሕፃናት ከአድሎአዊ ልዩነት የመጠበቅ፣ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች መሠረታዊ መብቶች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ያስቀምጣል።3

የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 (4) መሠረት የሀገሪቱ ሕግ አካል ሲሆኑ፣ ለአካል ጉዳተኞች የተደራሽነት መብት አግባብነት ካላቸው የሕገ መንግሥቱ ሌሎች ድንጋጌዎችና ብሔራዊ ሕጎች ጋር በአንድነት መነበብ ያለባቸው ናቸው። በአህጉር አቀፍ ደረጃ የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር የአካል ጉዳተኞች መብቶች ፕሮቶኮል (Protocol to the African Charter on Human and Peoples’ Rights on the Rights of Persons with Disabilities in Africa) የአካል ጉዳተኞች የተደራሽነት መብትን የሚመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ያካተተ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንድትፈርም እና እንድታጸድቅ ውትወታ እያደረገ ይገኛል።

የተደራሽነት መብት አላባዎች (elements of accessibility) ምን ምን ናቸው?

የተደራሽነት መብት ቢያንስ 4 አላባዎች አሉት። እነዚህም ከባቢን፣ የሕዝብ መጓጓዣን፣ መረጃና ተግባቦትን እንዲሁም የሕዝብ መገልገያዎች እና አገልግሎቶችን የተመለከቱ ናቸው።4

  • ከባቢያዊ ተደራሽነት (physical environment accessibility) በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጪ ያሉ ወደ ማንኛውም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሕንፃዎች እና መገልገያ ቦታዎች የሚወሰዱ መንገዶች ሁሉ ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግን ይመለከታል። ይህም ሲባል የእግረኛ መንገዶች፣ መታጠፊያዎች፣ የውሃና የቆሻሻ ማስተላለፊያ መስመሮች፣ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ምሰሶዎች፣ የትራፊክ መብራቶች እና የመሳሰሉት ከመንገድ ጋር የተገናኙ ቦታዎች ተደራሽነትን የሚያመላክት ነው።
  • የሕዝብ መጓጓዣ ተደራሽነት (transportation accessibility) ሁሉም ሰው ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚጠቀምባቸው እንደ መኪና፣ ባቡር፣ አውሮፕላን፣ የእግረኛ መንገድ የመሳሰሉ የሕዝብ መጓጓዣዎች ሁሉ አካል ጉዳተኞችም ሆኑ ጉዳት አልባዎች በቀላሉ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ እና እንቅፋት የሌለባቸው መሆን እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው።
  • የመረጃና ተግባቦት ተደራሽነት (information and communication accessibility) የአደጋ ጊዜዎችን ጨምሮ በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ የሚኖራቸው በማንኛውም ቦታና ርእሰ-ጉዳይ ላይ የሚተላለፉ መረጃዎች ሁሉ ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ተደራሽ በሆነ መንገድ መድረሳቸውን ማረጋገጥ ማለት ነው። ይህም ተደራሽነት ያለውን መረጃና የተግባቦት ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ የቃል ንግግሮችን፣ የሚታዩ ምልክቶችን፣ ብሬልን፣ በዳሰሳ የሚደረስባቸውን የግንኙነት ዘዴዎች፣ ጉልህ ሕትመቶችን፣ ምቹና ዘርፈ ብዙ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎችና ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን፣ የተጻፉና የተቀረጹ ድምጾችን፣ ግልጽ ቋንቋዎችን እና የሰው አንባቢ እንዲሁም በየጊዜው እየተሻሻሉ የሚሄዱና አማራጭ የተግባቦት ስልቶችን ያካትታል።
  • የሕዝብ መገልገያዎች እና አገልግሎቶች ተደራሽነት (public facilities and services accessibility) በአንጻሩ ማናቸውም ዐይነት ለሕዝብ ክፍት የሆኑ አገልግሎት መስጫዎች እና አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ተደራሽ መሆን አለባቸው ማለት ነው። ይህም የጤና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፣ የግል የንግድ ተቋማትን፣ የገበያ ቦታዎችን፣ መዝናኛዎችን፣ ምግብ ቤቶችን ወዘተ. ለሁሉም ሰዎች እኩል ተደራሽ ማድረግን ይመለከታል።

በተጨማሪም የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚቴ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ሌሎች የተደራሽነት መብት ዝርዝር ክፍሎች አብራርቷል። ከእነዚህም መካከል በስምምነቱ ውስጥ ዕውቅና የተሰጣቸውን በማንኛውም የሕይወት መስክ ራስን ችሎ የመኖር እና እኩል ተሳትፎ የማድረግ መብትን ጨምሮ አካል ጉዳተኞች ሁሉንም መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ተደራሽነት ቅድመ-ሁኔታ መሆኑን እንዲሁም በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት ተደራሽነትን መከልከል እንደ አድሎኣዊ ድርጊት የሚቆጠር መሆኑን አብራርቷል።5

ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ምንድን ናቸው?

ተደራሽነት አካል ጉዳተኞች የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል መብቶችን ሙሉ በሙሉ እና ከሌሎች እኩል ለመጠቀም ሊሟላላቸው የሚገባ መሠረታዊ ቅድመ-ሁኔታ እንደመሆኑ፣ የተደራሽነት መጓደል በአካል ጉዳተኞች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከባድ ተጽዕኖ ያሳድራል። በተለይም ተደራራቢ የአካል ጉዳት ባለባቸው፣ በገጠራማ አካባቢዎች፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በግጭት ዐውድ ፣ በስደተኛነት፣ ፍልሰተኛነት ወይም በመፈናቀል ሁኔታ፣ በተቋም ውስጥ እና በጎዳና ላይ ባሉ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም በሴት፣ ሕፃናት፣ ወጣት እና አረጋውያን አካል ጉዳተኞች ላይ ተደራራቢ፣ ውስብስብ እና ዐይነተ-ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ያስከትላል።

ተደራሽነት ከብዙኃን ሰዎች አጠቃላይ ፍላጎት ጋር የተያያዘ እና አስቀድሞ ሊሟላ የሚገባ ግዴታ (ex-ante duty) እንደመሆኑ ይህንኑ ለማረጋገጥና የአካል ጉዳተኞች መብቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲከበሩ ለማስቻል ሊወሰዱ የሚገባቸው በርካታ እርምጃዎች አሉ።

ከእነዚህም መካከል፦

  • ሁለንተናዊ ንድፍ (universal design)፦ ሁለንተናዊ ንድፍ ሁሉም አዳዲስ ሕንጻዎች፣ መሠረተ-ልማቶች፣ እቃዎችና ምርቶች፣ ተቋማት፣ ቴክኖሎጂዎች እና አገልግሎቶች ከመነሻው የንድፍ ደረጃቸው አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ በማድረግ፤ በኋላ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን በእጅጉ ከመቀነስ ባሻገር የተሟላ፣ እኩል እና ያልተገደበ ተደራሽነት ያለው የሰዎችን ክብርና ብዝኃነት ያከበረ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል እርምጃ ነው።6
  • ተመጣጣኝ ማመቻቸት (reasonable accommodation)፦ ተደራሽነት ሰፊ፣ ከቡድኖች ጋር ተያያዥነት ያለው እና አስቀድሞ ሊሟላ የሚገባው ግዴታ (ex-ante duty) ሲሆን፣ ተመጣጣኝ ማመቻቸት ከአንድ ግለሰብ ጋር የተያያዘ እና ለግለሰቡ ባስፈለገው ጊዜ የሚሟላ ግዴታ (ex-nunc duty) ነው። በመሆኑም ተመጣጣኝ ማመቻቸት በአንድ በተወሰነ ሁኔታ ውስጥ ለአካል ጉዳተኛ ግለሰብ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል እርምጃ ነው።7
  • ነባር መሰናክሎችን ማስወገድ (removing existing barriers)፦ አስቀድሞ የነበሩ ሕንጻዎች፣ መሠረተ-ልማቶች፣ ዕቃዎችና ምርቶች፣ ተቋማት፣ ቴክኖሎጂዎች እና አገልግሎቶች ላይ ያሉ መሰናክሎችን ለማስወገድ የሚደረጉ የማሻሻያ እርምጃዎችን የሚመለከት ሲሆን፣ በአዲስ መልክ በሚገነቡት መሠረተ ልማቶች ወይም በሚዘረጉት አገልግሎቶች ላይ ከሚደረገው የተለየ ነው።8 ይህም በዋናነት ነባር መሰናክሎችን ለማስወገድ እና አዳዲሶቹን ሕንጻዎች፣ መሠረተ-ልማቶች፣ ዕቃዎችና ምርቶች፣ ተቋማት፣ ቴክኖሎጂዎችና አገልግሎቶች ከጅምሩ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስፈልገው ስልት፣ የሚወስደው ጊዜ እንዲሁም በጀት የተለያየ በመሆኑ ነው።

በተጨማሪም መንግሥት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መሰናክሎችን ለመለየት እና ለማስወገድ የሚያስችሉ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች እንዲሁም ብሔራዊ የተደራሽነት መመዘኛዎችን (national accessibility standards) ማዘጋጀት፤ የእነዚህን ማዕቀፎች ትግበራ መከታተል የሚችል ሰፊ ሥልጣን፣ በቂ ዐቅም፣ ብቃት እና ሃብት ያለው ተቋም ማቋቋም፤ እንዲሁም ተደራሽነትን አስመልክቶ ለሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ስልታዊ በሆነ ዘዴ እና ያለማቋረጥ መስጠት ይጠበቅበታል።9


1 የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት፣ መቅድም፣ ንዑስ ዠ።

2 የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት፣ አንቀጽ 1።

3 የተመድ የሕጻናት መብቶች ኮሚቴ፣ አጠቃላይ ትንታኔ ቁ. 9፣ 1999 ዓ.ም.፣ አንቀጽ 39።

4 ተጨማሪ ለማንበብ፡ https://www.un.org/esa/socdev/enable/disacc.htm

5 የተ.መ.ድ. የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚቴ፣ አጠቃላይ ትንታኔ ቁ. 2፣ አንቀጽ 23።

6 የተ.መ.ድ. የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚቴ፣ አጠቃላይ ትንታኔ ቁ. 2፣ አንቀጽ 15።

7 የተ.መ.ድ. የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚቴ፣ አጠቃላይ ትንታኔ ቁ. 2፣ አንቀጽ 25 እና 26።

8 የተ.መ.ድ. የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚቴ፣ አጠቃላይ ትንታኔ ቁ. 2፣ አንቀጽ 24።

9 የተ.መ.ድ. የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚቴ፣ አጠቃላይ ትንታኔ ቁ. 2፣ አንቀጽ 25 እስከ 30።