የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ረቂቁ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ከአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች አንጻር ሊያካትታቸው በሚገቡ ነጥቦች ዙሪያ  የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ በሚገኘው በኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት ምክክር አካሂዷል፡፡ ኢሰመኮ በአዋጅ ከተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል በመንግሥት የሚወጡ ሕጎች በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችና በሕገ-መንግሥቱ ዕውቅና ከተሰጣቸው ሰብአዊ መብቶች ጋር የማይቃረኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገኝበታል፡፡

የምክክር መድረኩ ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት በረቂቅ ሕጉ ላይ ካቀረባቸው አጠቃላይ እና ዝርዝር አስተያየቶች እና ምክክሮች በተጨማሪ፤ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ እና ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መብቶች ለማስጠበቅ በተከታታይ የሚያከናውነው  የውትወታ ሥራ አካል ነው፡፡

በምክክሩ ረቂቅ ሕጉ የአካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ሰብአዊ ክብር የሚነኩ ቃላቶችን እንዲያስወግድ እንዲሁም በወንጀል ምርመራ፣ በክስ፣ በፍርድ እና በውሳኔ አፈጻጸም ሂደቶች ውስጥ ሁሉ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን የሚገጥማቸውን ተቋማዊ፣ ከባቢያዊ፣ የመረጃ እና ተግባቦት ተግዳሮቶችን የሚያስወግድ እንዲሆን የሚያስችሉ አስተያየቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የምክክሩ ተሳታፊዎችም በኮሚሽኑ ከቀረቡ አስተያየቶች መካከል ቢሻሻሉ ያሏቸውን  እና ተጨማሪ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡

በምክክሩ ማጠቃለያ የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ፤ “ረቂቅ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕጉ በተሰጡ አስተያየቶች ዳብሮ እና በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት  በተለያየ መልኩ ግንኙነት የሚኖራቸውን የአካል ጉዳተኞችን እና የአረጋውያንን ሰብአዊ መብቶች ሊያስከብር እና ልዩ ልዩ ፍላጎቶቻቸውን ሊያሟላ በሚችል መልኩ ተሻሽሎ እንዲወጣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል” ብለዋል፡፡  በቀጣይም ኮሚሽኑ የተሰጡ አስተያየቶችን በማጠናቀር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሕግ፣ ፍትሕ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚልክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በምክክሩ የፌዴራል ዳኞች እና የፖሊስ ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ ከአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ማኅበራት እንዲሁም ከልዩ ልዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ 28 ተሳታፊዎች የተገኙበት ሲሆን ከእነዚህም መካከል  አስሩ (10) አካል ጉዳተኛ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡


የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዴ.ሪ.) ረቂቅ “የወንጀል ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ”ን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የቀረበ የማሻሻያ ምክረ ሃሳቦች

News Analysis: Rights Commission recommends several changes to improve draft Criminal Procedure Code