የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2018 በጀት ዓመት 4ኛው ሩብ ዓመት፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ለፖሊስ አባላት፣ ለዐቃቤያነ ሕግ፣ ለዳኞች፣ ለማረሚያ ቤቶች ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለሃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተከታታይ የሰብአዊ መብቶች ስልጠናዎችን ሰጥቷል። ስልጠናዎቹ በዋናነት በሽግግር ፍትሕ፣ በተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች አያያዝ እንዲሁም በሕፃናት መብቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው።

በሩብ ዓመቱ ለፖሊስ እና ለማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ከተሰጡ ስልጠናዎች መካከል ከተለያዩ አካባቢዎች ለተውጣጡ የፖሊስ አባላትና የሥራ ኃላፊዎች በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ሰዎችን መብቶች ማክበርና የኃይል አጠቃቀም መርሖች ዙሪያ በመቐለ፣ በሮቤ እና በሶዶ ከተሞች ስልጠና ተሰጥቷል። በተመሳሳይም ከመቐለ እና ጅማ ከተሞች ለተወጣጡ የማረሚያ ቤት ፖሊሶችና የሥራ ኃላፊዎች የታራሚዎችን ሰብአዊ መብቶችና ክብር በጠበቀ አያያዝ ዙሪያ የክህሎት እና ዐቅም ማሳደጊያ ስልጠና ተከናውኗል።


በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሕፃናትን መብቶች ከማስጠበቅ አኳያ ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ አዳዲስ ዐቃቢያነ ሕግ በቢሾፍቱ ከተማ ሰፊ ስልጠና ተሰጥቷል። ስልጠናው በወንጀል እና በፍትሐብሔር ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን መብቶች ያማከለ የፍትሕ አሰጣጥ እና ጥበቃ ላይ የመፈጸም ዐቅም ለመፍጠር ያለመ ነው። በዚህ ስልጠና ከሕፃናት የፍትሕ ሂደት ጋር በተያያዘ ብዙ ልምድ እና እውቀት ያካበቱ የፌዴራል ፍ/ቤት ዳኛ ለስልጠናው ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከት ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለተውጣጡ ዳኞች በቦንጋ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ፣ ዳኞች ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችን በፍርድና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ዐቅም ለማጎልበት የሚያስችል ስልጠና አግኝተዋል።

በተጨማሪም በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ የሃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ያላቸውን ሚና እንዲሁም የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ የዳሰሰ ስልጠና በሮቤ ከተማ ተከናውኗል። በዚህም የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን እውቀት እና ክህሎት ማግኘት ችለዋል፡፡ በተመሳሳይ ወጣቶች ሰብአዊ መብቶችን በማክበር ለሰላምና ለአብሮነት ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ያለመ ስልጠና ከተለያዩ የወጣት ማኅበራትና አደረጃጀቶች ለተውጣጡ አባላት በባሕር ዳር ከተማ ተሰጥቷል።

ኢሰመኮ በ2018 በጀት ዓመት 4ኛው ሩብ ዓመት ያካሄዳቸው እነዚህ የስልጠና መድረኮች፤ በማኅበረሰቡና በአስፈጻሚ አካላት ዘንድ የሰብአዊ መብቶች መከበርን ከማጠናከር ባለፈ፣ ሰልጣኞች የሰብአዊ መብቶች መርሖችን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ተግባራዊ የሚያደርጉበት እውቀት እና ክህሎት እንዲያገኙ ዕድል የፈጠሩ ናቸው።