የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ብሔራዊ ምርመራ የማስጀመሪያ ዐውደ ጥናት የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራልና የክልል የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አካላት በተገኙበት አካሂዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የማስጀመሪያ ዐውደ ጥናቱን ተከትሎ ከሰኔ 27 እስከ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ኮሚሽኑ የብሔራዊ ምርመራ አካል የሆነውን ሕዝባዊ አቤቱታ መቀበያ መድረክ በሃዋሳ ከተማ አካሂዷል፡፡ በሃዋሳ የተካሄደው ሕዝባዊ አቤቱታ መቀበያ መድረክ ትኩረት ያደረገው በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ነፃነታቸውን አለአግባብ የተነፈጉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ሲሆን በመድረኩ ላይ ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው፣ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና ተመራማሪዎች የተገኙበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ኮሚሽኑ በሕዝባዊ አቤቱታ መድረኩ የተሰጡትን ምስክርነቶች እና የቀረቡ የሰነድ ማስረጃዎች፣ የመንግሥት ምላሽ፣ የኃይማኖት አባቶች ምልከታ፣ የምሁራን አስተያየቶች እና የምርምር ግኝቶች ከኮሚሽኑ የክትትል እና ምርመራ ግኝቶች ጋር በማመሳከር በክልሉ ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ስልታዊ/ሥርዓታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን መለየት ችሏል፡፡ እነዚህ የተለዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን፣ ምክረ-ሃሰቦችን እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶችን ያካተተ ረቂቅ ሪፖርት አዘጋጅቶ በዚሁ ረቂቅ ሪፖርት ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ኅዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በሃዋሳ ከተማ በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ውይይት ተደርጓል፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ የረቂቅ ሪፖርቱ ይዘት የቀረበ ሲሆን የሕዝባዊ ምርመራው ሂደት እና ሥነ-ዘዴ እንዲሁም ምርመራው መሰረት ያደረጋቸው የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች አጭር ማብራሪያ ለውይይት መነሻ ቀርቧል፡፡ በሕዝባዊ ምርመራው ዋና ዋና ግኝቶች፣ የተለዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና ምክረ-ሃሳቦችም ቀርበዋል፡፡ በሕዝባዊ ምርመራው ከተለዩት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል የአካል ደኅንነት እና የነፃነት መብት፣ ከማሰቃየት፣ ከጭካኔ እና ኢሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ መብት፣ የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸውን ክስ እና ምክንያቱን የማወቅ መብት፣ ፍርድ ቤት በ48 ሰዓት ውስጥ የመቅረብ መብት፣ እንዲሁም ምክንያታዊ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ ችሎት ፊት የመቅረብ መብት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ይህንኑ መሰረት በማድረግ የሕግ እና የፖሊሲ እንዲሁም የአሠራር ማሻሻያዎችን የሚመለከቱ ምክረ-ሃሳቦች ተሰጥተዋል፡፡
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በመክፈቻ ንግግራቸው እና በውይይቱ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት በሰላም እና ጸጥታ ማስከበር እንዲሁም በወንጀል ምርመራ ሂደቶች ውስጥ የሰዎችን መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ማክበር የመንግሥት ግዴታ መሆኑን በአጽንዖት ገልጸዋል።ብሔራዊ ምርመራው እንዳሳየው በክልሉ ሰዎች በስፋት እና በተደጋጋሚ ከሕግ ውጪ እና በዘፈቀደ ነፃነታቸውን የሚነፈጉት በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት፣ ከመዋቅር እና ከወሰን ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ችግሮች በመሆኑ እነዚህን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በክልሉ የሚነሱ የመዋቅርና የወሰን ጥያቄዎችን በዘላቂ ሁኔታ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ውይይቱን የመሩት የሲቪል እና ፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በሰላም እና ጸጥታ ዘርፍ፣ በፖሊስ፣ በዓቃቤ ሕግ፣ በፍርድ ቤት እና በማረሚያ ቤቶች የሚከናወኑ ተግባራት በዋነኝነት የሰብአዊ መብቶችን እውን የሚያደርጉ በመሆናቸው አሠራሮቻቸውን ማሻሻል ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅ እና መሟላት መሰረት ነው ብለዋል፡፡