የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ 

የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት፣ ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች መብቶችን በተመለከተ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ብሔራዊ ምርመራ (National Inquiry) ለማካሄድ ከፌዴራልና ከዘጠኝ ክልሎች የተወጣጡ የፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የፍትሕ ተቋማት ተወካዮች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ስብሰባ ተካሂዷል።

ውይይቱ ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ጉዳይ የሚደረገውን የመጀመሪያውን ብሔራዊ ምርመራ ያስተዋወቀ ሲሆን፤ ብሔራዊ ምርመራን ለማካሄድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በአጋርነት ለመስራት የሚያስችል መግባባትን ፈጥሯል። በተጨማሪም ኢሰመኮ ብሔራዊ ምርመራን በተመለከተ ሊጫወት ስለሚችለው ሚና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራን በብሔራዊ ደረጃ ለማካሄድ ያለበትን ኃላፊነትና ግዴታ በባለድርሻ አካላት ዘንድ ግንዛቤን ለማሳደግ ግብዓትን ከተሳታፊዎች አሰባስቧል።

በዚህም መሰረት ብሔራዊ ምርመራ ማለት ውስብስብና ተደጋጋሚ በመሆናቸው፣ አልያም በሀገር አቀፍ ደረጃ ወይም በበርካታ አካባቢዎች የሚታዩ፣ በርካታ ሰዎችን (ሕጻናትን፣ ሴቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችን) የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሰለባዎች የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ለመወያየትና ሰፋ ያሉ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሚጠቅም ዘዴ መሆኑ ተገልጿል። በተለይም በአንድ ተቋም ብቻ ለመመርመር አዳጋች የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን ለመመርመር ምቹ አጋጣሚን ይፈጥራል። እንዲሁም ብሔራዊ ምርመራ ዝቅተኛ የሕዝብና የፖለቲካ ዕውቅና ያላቸውን የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ጎልተው እንዲታዩ ያስችላል።

ብሔራዊ ምርመራ ባለድርሻ ማኅበረሰቡ በግልጽ የሚሳተፍበት ሲሆን፣ የመገናኛ ብዙኃንንም ትኩረት በመሳብ ውስብስብ እና ስልታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ የሚደረጉ ውይይቶችን ለሰፊው ማኅበረሰብ እንዲተዋወቅ ያደርጋሉ። በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደታየውም ብሔራዊ ምርመራ አሳታፊ መሆኑ የፖለቲካ ትኩረትን በመሳብ የፖሊሲና የሕግ ቀረጻ እና ትግበራን ለመፍጠር የሚያችል ብቃትን ለማደራጀት ይረዳል።

በስብሰባው ላይ በተለይም ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ የሚያተኩሩት የመጀመሪያ ዙር ብሔራዊ ምርመራዎች በአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄዱና  የወንጀል ፍትሕ አስተዳደርን ሪፎርም ለማድረግ እየተቀረጸ ያለው ፕሮግራም አካል እንደሆኑ ተገልጿል።

በዝግጅቱ መክፈቻ ባሰሙት ንግግር የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “እንደዚህ አይነት የመጀመሪያውን ብሔራዊ ምርመራ ለማካሄድ የተመረጠው ጉዳይ ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ጉዳይ ቢሆንም፣ በቀጣይ በሕይወት የመኖርንና በነፃነት የመንቀሳቀስን መብቶች ጨምሮ በሌሎች የመብቶች ጉዳይ ላይ የሚካሄድ ይሆናል” ብለዋል።