የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችንና አባላትን፣ የሚዲያ አባላትንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ዒላማ ያደረገ እስር እና ወከባ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን ገለጸ። ኢሰመኮ በተለያየ ዓይነት ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ከተያዙ ሰዎች ውስጥ በተለይ የሚዲያ አባላትን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን እንዲሁም የማኅበረሰብ አንቂዎችን (Activists) ጉዳይ በተመለከተ ክትትል ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ ከእነሱም መካከል ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር የዋሉ፣ የሚዲያ አዋጁን (የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013) በሚጻረር መልኩ የታሰሩ፣ በተራዘመ ቅድመ-ክስ እስር ወይም ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር የቆዩ መኖራቸውን፣ በተወሰኑት ላይ የወንጀል ክስ ተመሥርቶ የነበረ ቢሆንም ክሱ በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ባለመሆኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ ወይም በፖሊስ ውሳኔ ከተራዘመ እስር በኋላ በነጻ ወይም በዋስትና የተለቀቁ መኖራቸውንም ኮሚሽኑ ተመልክቷል።
ኮሚሽኑ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እስከ አሁን ድረስ በእስር ላይ ከሚገኙት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አመራሮችንና የሌሎችም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ላይ የሚደርሱ እንግልት እና እስሮችን ጠቅሶ መንግሥት የሰዎችን በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ መብታቸውን የሚገድቡ ተግባሮችን የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት ማሳሰቡ የሚታወስ ነው። በቅርብ ጊዜ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ያተኮሩ እስሮች እና ማዋከብ እናት ፓርቲን፣ በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን እና የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲን ይጨምራል፡፡
በዚህ ወር ውስጥ ብቻ ከታሰሩ የሚዲያ አባላት መካከል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነው ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውን (አራት ኪሎ ሚዲያ) ጨምሮ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው (የኔታ/መድሎት ሚዲያ)፣ ጋዜጠኛ አራጋው ሲሳይ (ሮሃ ኒውስ/Roha News)፣ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው (ኢትዮ ሰላም)፣ ጋዜጠኛ ጌትነት አሻግሬ (የአማራ ድምፅ/Voice of Amhara)፣ ጋዜጠኛ በየነ ወልዴ (ጉራጌ ሚዲያ ኔትወርክ )፣ ጋዜጠኛ ሰናይት አያሌው (አሻራ ሚዲያ) ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ (ኢ ኤም ኤስ) እንዲሁም በማኅበረሰብ አንቂነት (Activist) እና በሚዲያ ሥራም የሚታወቁት መስከረም አበራ (ኢትዮ ንቃት) ይገኙበታል፡፡ ከፊሎች በእስር ወቅት ተገቢ ላልሆነ አያያዝ የተዳረጉ፣ ከፊሎች ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ እስር ተዳርገው የነበሩ እና፣ ከፊሎችም ከተለያየ ጊዜ መጠን እስር በኋላ የተለቀቁ ናቸው፡፡
መንግሥት የወንጀል ተግባሮችን ሁሉ የመከላከል፣ የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና የማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚያተኩር እስር ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብቶች ላይ የሚያስፈራራ፣ የሚያሸማቅቅ እና የሚገድብ ውጤት (chilling effect) እንዳይኖረው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ነው፡፡
በመሆኑም የመንግሥት የጸጥታ አካላት በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና በማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ ካተኮረ እስርና ማዋከብ እንዲቆጠቡ፣ በወንጀል የተጠረጠሩና በበቂ ሕጋዊ ምክንያት በቅድመ-ክስ ሊታሰሩ የሚገባቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሁኔታም በሕግ በተመለከተው መንገድ ብቻ በጥብቅ ጥንቃቄ አንዲፈጸምና የተጠረጠሩ ሰዎችን ሁሉ ከምርመራ በፊት ከማሰር እንዲቆጠቡ፣ በተጨማሪም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 (የሚዲያ አዋጅ) መሠረት በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፣ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ-ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ፤ በዚሁ መሠረት እንዲፈጸምና በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ ኢሰመኮ ያሳስባል፡፡
በተጨማሪም የሚዲያ ሠራተኞች የፓለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የማኅበረሰብ አንቂዎች ለሕጋዊና ሰላማዊ ሥራ ያለባቸውን ልዩ ኃላፊነት ኢሰመኮ አስታውሷል፡፡