የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር ኖት ፎር ፕሮፊት ሎው (International Center for Not for Profit Law) ከተባለ ዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር በሲቪል ምህዳር ላይ ክትትል የማከናወኛ ዘዴን በተመለከተ ለኮሚሽኑ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች እንዲሁም ለከተማ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የካቲት 28 እና 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ሁለት ቀናት በቆየው ስልጠና በሲቪል ምህዳር ምንነት እና በውስጡ ስለሚካተቱ የነጻነት መብቶች ማለትም የመሰብሰብና የመደራጀት፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፤ የሕዝባዊ ተሳትፎና የፖለቲካ ተሳትፎ የማድረግ ነጻነቶች ምንነት እና በእያንዳንዱ ውስጥ የተካተቱ አላባውያን ላይ ያተኮሩ ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች መስፈርቶችን መሠረት ያደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ይዘቶች ቀርበዋል፡፡ እንዲሁም በሲቪል ምህዳር ላይ የሚጣሉ ገደቦችና ጥበቃዎችን በተመለከተ ክትትል የማድረግ አስፈላጊነት ላይ ምክክር የተደረገ ሲሆን የክትትል ሥነ-ዘዴዎችን የማዘመን ክንውኖችም በስልጠናው ተካተዋል፡፡ በተጨማሪም የመረጃ አሰባሰብና ማረጋገጥ፣ የመረጃ ማከማቸት፣ የዲጂታል ደኅንነትና መሰል ይዘት ያላቸው ሌሎች ጉዳዮች በስልጠናው ተዳሰዋል ፡፡
በስልጠናው የሲቪል ምህዳር የክትትል ሥነ-ዘዴዎች እና መሳሪያዎች ውስጥ የተካተቱ ቁልፍ ክንውኖችና መለኪያዎች፣ እንዲሁም የመረጃ መሰብሰቢያ ቅጾችን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳይ አጭር ማብራሪያ መቅረቡን ተከትሎ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ የስልጠናው ተሳታፊዎች የሲቪል ምህዳር ክትትል ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች እንዲሁም የሂደቱን ደኅንነትና ትክክለኛ ውጤት መገኘቱን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ምክክር አካሂደዋል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ጅብሪል (ዶ/ር) በስልጠናው መክፈቻ ላይ ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የተካተቱ መብቶችና ነጻነቶች ተግባራዊነት ላይ ክትትል የሚያከናውን መሆኑን ጠቅሰው ስልጠናው የሲቪል ምህዳር ሁኔታ የመከታተያ ዘዴን ለመተግበር እና የባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማጠቃለያው ሰልጣኞች የሲቪል ምህዳር ክትትል ሂደትን ተከትሎ ስለሚዘጋጀው የክትትል ሪፖርትና በሪፖርቱ የሚካተቱ መረጃዎችና ትንታኔ ምን መምሰል እንዳለበት የተለያዩ ሐሳቦችን በማቅረብ ወጥ ግንዛቤ መያዝ የሚያስችላቸውን ውይይት አድርገዋል፡፡