የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቀድሞው ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የሚገኙ 6 ዞኖች (ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ እና ወላይታ) እና 5 ልዩ ወረዳዎች (አሌ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ዲራሼ) የተደረገ ሕዝበ ውሳኔ እንዲሁም በወላይታ ዞን የተደረገ ድጋሚ ሕዝበ ውሳኔ ላይ ያከናወነውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ባለ 50 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ክትትሉ ከታኅሣሥ 26 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. የቅድመ ሕዝበ ውሳኔ፤ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝበ ውሳኔ ዕለት እንዲሁም ከጥር 30 እስከ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. የተካሄደውን የድኅረ-ሕዝበ ውሳኔ በተመረጡ አካባቢዎች በአካል በመገኘት የተከናወነ ነው። በተጨማሪም በወላይታ ዞን የተደረገው የድጋሚ ሕዝበ ውሳኔ ሂደት ላይ ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ክትትል፣ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝበ ውሳኔ ዕለት ክትትል እንዲሁም ሰኔ 13 እና 14 የድኅረ ሕዝበ ውሳኔ ክትትል አከናውኗል።
የክትትሉ ዓላማ በሕዝበ ውሳኔ ወቅት ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እንዲሻሻል ማድረግ፤ በሕዝበ ውሳኔ ወቅት ለሚከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የውትወታ ሥራዎችን መሥራት፣ የድምፅ መስጠት ሂደቱ ለሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች የነበረውን ተገዢነት መገምገም እና በሕዝበ ውሳኔ ጊዜ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች በመሰነድ ወደፊት በሚደረጉ ሕዝበ ውሳኔዎች የተሻለ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ባህል እንዲጎለብት አስተዋጽዖ ማድረግ ነው።
ኮሚሽኑ ሕዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው በሁሉም ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በተመጣጣኝ ቢያንስ አንድ የክትትል ቡድን ያሰማራ ሲሆን ከአጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በ186 ጣቢያዎች ላይ ክትትል ተደርጓል። ይህም ሰባት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን ይጨምራል። የዳግም ሕዝበ ውሳኔ በተካሄደበት በወላይታ ዞን ለሕዝበ ውሳኔው ከተዘጋጁ 1804 የሕዝበ ውሳኔ ጣቢያዎች ውስጥ ናሙና በመውሰድ 27 ጣቢያዎች ላይ ክትትል ተደርጓል።
አስፈላጊውን መረጃ ለማሰባሰብ እና ክትትሉን ለማድረግ በዋነኝነት የክትትል ዘዴዎች (tools)፣ መጠይቆች እና ሌሎች ቅጾች ላይ መሠረት ያደረገ ምልከታ፤ የጋራ ቡድን ውይይት እና ቃለመጠይቅ ተከናውኗል። በተጨማሪም በነጻ የስልክ መስመር (hotline) አቤቱታዎችን መቀበል እና መመልከት ሌሎች ኮሚሽኑ ለክትትሉ የተጠቀማቸው የመረጃ ማሰባሰቢያ መንገዶች ነበሩ።
ኮሚሽኑ ከሕዝበ ውሳኔ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የዜጎች የመምረጥ መብት፣ የአመለካከት እና ሐሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብት እንዲሁም የእኩልነት እና ከአድሎ ነጻ የመሆን መብት በሪፖርቱ በዋነኝነት የተካተቱ መብቶች ናቸው። ሪፖርቱ የቅድመ ሕዝበ ውሳኔ፤ የሕዝበ ውሳኔ ዕለት እና ድኅረ ሕዝበ ውሳኔ ዋና ዋና የክትትል ግኝቶችን ያካተተ ነው።
በቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ክትትል ወቅት ከተለዩት ዋና ዋና ግኝቶች መካከል ግልጽ ባልሆነ ቦታ ላይ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች፤ የምርጫ ጣቢያ መሆኑን የሚገልጽ ምልክት የሌለባቸው ቤቶች እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋዊያን እና ለነፍሰጡር ሴቶች ተደራሽ መሆን በማይችሉ አካባቢዎች የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በተለይ በአርባ ምንጭ የምርጫ ክልል፣ በጎፋ ዞን በሣውላ ከተማ በስፋት መኖራቸው ተጠቃሽ ናቸው። ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ተማሪዎች በኦይዳ ወረዳ ሸፍቲ ቀበሌ በሶላካሬ ንኡስ ምርጫ ጣቢያ እና በቡልቂ ከተማ በቡልቂ ልዩ 01 ሀ ንኡስ 1 ምርጫ ጣቢያ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸው እና በሳውላ እና ቡልቂ ከተማ አስተዳደሮች ሥር በሚገኙ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ አስገዳጅ መመሪያ በትምህርት ቤቶች በኩል መልእክት መተላለፉ በኮሚሽኑ ከተለዩ ግኝቶች ውስጥ ናቸው።
በተመሳሳይ በዲራሼ ልዩ ወረዳ የምርጫ ክልል በሚገኙ 85 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ በዕቅዱ መሠረት አለመከናወኑ፤ በዲራሼ ልዩ ወረዳ በተለይ በቡሳ ባሶ የምርጫ ጣቢያ 1 እና 2፤ በአርባምንጭ የምርጫ ክልል በዘይሴ ወዘቃ ጸናኦ ቁ-3 የምርጫ ጣቢያ እና በካራት ከተማ አስተዳደር እስር፣ ማስፈራሪያ፣ ወከባ እና ሌሎች ጣልቃ ገብነቶች በስፋት መስተዋሉ በሪፖርቱ ተካቷል። በተጨማሪም የጸጥታ አስከባሪ አካላት ተሳትፎ እና የጸጥታ ሁኔታ፤ የመራጮች ትምህርትና ቅስቀሳ እና የመራጮች ምዝገባ የተከናወነበት የጊዜ ሰሌዳ እና ሰዓትን የተመለከቱ ግኝቶች በሪፖርቱ ተጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑ በሕዝበ ውሳኔ ዕለት ባከናወነው ክትትል ማስፈራራት፣ ድብደባ እና ልዩ ልዩ ጫና የማድረግ ድርጊቶች በተወሰኑ የሕዝበ ውሳኔ ጣቢያዎች ላይ የተስተዋሉ መሆናቸው በሪፖርቱ ተካቷል። ለምሳሌ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ አስተዳደር ጊዶ 2 የምርጫ ጣቢያ የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ አባላት መራጮችን ሲያዋክቡ እንደነበር፤ በጋሞ ዞን ቁጫ ወረዳ ሞርካ 1 የምርጫ ጣቢያ ፖሊስ መራጮችን ሰልፍ ለማስያዝ በሚል ሰበብ መራጮችን ሲደበድብ የነበረ መሆኑና በአንድ መራጭ ላይ የመድማት ጉዳት መድረሱ እና አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዘይሴ ኤልጎ ሉዳ 1 የምርጫ ጣቢያ የአካባቢው ሚሊሻዎች ቢያንስ 20 የሚሆኑ መራጮችን ሲያስፈራሩና ሲደበድቡ መታየታቸው በሕዝበ ውሳኔ ዕለት የተፈጸሙ የመብቶች ጥሰቶች ናቸው። እንዲሁም የጸጥታ ኃይሎች የደንብና ሥነ-ምግባር ጥሰቶች፤ በተከለከለ ቦታ ላይ የተደራጁ ምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸው፤ የመራጮች ጣቢያ ተደራሽነት እና አደረጃጀት ምቹ አለመሆን፤ የመራጮች ካርድ ወይም መታወቂያ ያልያዙ መራጮች በሕዝበ ውሳኔው ድምፅ እንዲሰጡ መደረጉ እና ምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱበት ጊዜ ሰዓቱን ያልጠበቀ መሆን በሪፖርቱ ከተካተቱ ግኝቶች መካከል ናቸው።
የድኅረ ሕዝበ ውሳኔ የክትትል ግኝቶችን በተመለከተ በአብዛኞቹ ክትትል በተደረገባቸው ቦታዎች ላይ ከሕዝበ ውሳኔው ሂደት እና ውጤት ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ከባድ ወይም መጠነ ሰፊ ተቃውሞ፣ ወይም የደረሰ ከባድና መጠነ ሰፊ ጉዳት አልታየም። ሆኖም በቁጫ ወረዳ ቁጫ ጋሌ ቀበሌ ከሕዝበ ውሳኔ ምርጫ ጋር በተገናኘ በርከት ያሉ ታሳሪዎች መኖራቸውን ኮሚሽኑ ተመልክቷል። በዚሁ ወረዳ ኮሚሽኑ ክትትል እያደረገ በነበረበት ወቅት ተቃዋሚ ናቸው በተባሉ ሰዎች ላይ የማስፈራራትና፣ የስድብ ድርጊቶች ሲፈጸሙ የነበረ ሲሆን የኮሚሽኑ አባላትም ለተወሰኑ ሰዓታት እንዳይንቀሳቀሱ ታግተው መቆየታቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በተመለከተ በሪፖርቱ ከተካተቱ ግኝቶች ውስጥ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጠቅላላም ሆነ ልዩ የመራጮች ትምህርት አለመሰጠቱ፤ ኮሚሽኑ ክትትል ያደረገባቸው አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች አደረጃጀት ለአረጋዊያን፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ እና ነፍሰጡር ሴቶች ምቹ እና ተደራሽ ባልሆነ መልኩ የተደራጁ መሆናቸው ይገኙበታል።
ኮሚሽኑ በቅድመ ሕዝበ ውሳኔ፣ የሕዝበ ውሳኔ ዕለት እና ድኅረ ሕዝበ ውሳኔ የክትትል ግኝቶች መሠረት የሕግ ጥሰቶች እና የአሠራር ክፍተቶችን ለማሻሻል ያስችላሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦች በሪፖርቱ በዝርዝር አካቷል። ዜጎች በነጻነት እና ከማንኛውም አድሎአዊ አሠራር ነጻ በሆነ መልኩ የመምረጥና በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ መብቶቻቸውን ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ማናቸውም የማዋከብ፣ የማሰር እና ሌሎች የድምፅ መስጠት ሂደትን የሚያደናቅፉ ድርጊቶችን ማስወገድ፣ የመንግሥት እና የምርጫ አስፈጻሚ አካላት በድምፅ መስጠት ሂደት ላይ ጣልቃ ከመግባት መታቀብ፣ የምርጫ ጣቢያዎች ለነፍሰጡር ሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ተደራሽ እንዲሆኑ እና አደረጃጀቱ አመቺ እንዲሆን ማድረግ እና የምርጫ ጣቢያዎች በሕግ በተፈቀደ ቦታ ብቻ እንዲደራጁ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ኮሚሽኑ አመላክቷል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል መሠረት አጠቃላይ የሕዝበ ውሳኔ ሂደቱ ከመለስተኛ የምርጫ አስተዳደር ግድፈቶች ውጭ ሰላማዊ፣ ሥርዓታዊ እና ከጎላ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነጻ የነበረ መሆኑ አበረታች ሲሆን፤ በሌላ በኩል በዚህ ሪፖርት የተዘረዘሩት ጉድለቶችና ጥሰቶች በቀላሉ ሊታዩ ስለማይገባ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ለወደፊቱ ተመሳሳይ ጥሰቶችን መከላከል ይገባል” ብለዋል፡፡