የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ በቂ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብትን ለመተግበር በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ከሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ለመገምገም በአዳማ፣ አዲስ አበባ እና ሃዋሳ ከተሞች ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ታኅሣሥ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ የክትትሉ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ላይ ለመምከር፣ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ እንዲሁም በቂ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲደረግ ለመወትወት ያለመ ነው።

በውይይቱ ከከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ከሲዳማ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ፣ ከሃዋሳ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር፣ ከሃዋሳ ከተማ መሬት አስተዳደር፣ ከግል መኖሪያ ቤት አልሚዎች (ሪልስቴት) እንዲሁም ከመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የተወጣጡ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ኢሰመኮ በክትትሉ የለያቸው ቁልፍ እመርታዎች፣ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ባለድርሻ አካላትም በተቋሞቻቸው መብቱን በማሟላት ረገድ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን እና የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች አቅርበዋል።

በመድረኩ በቂ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት በተሻለ ሁኔታ ተፈጻሚ እንዲሆን ለማስቻል ሁሉን አቀፍ መብትን መሠረት ያደረገ ብሔራዊ የቤቶች ፖሊሲ ማዘጋጀትን ጨምሮ የሕግ እና ተቋማዊ ማዕቀፎችን ማጠናከር፣ ተመጣጣኝነትን፣ አካታችነትን እና እኩልነትን ማረጋገጥ እንዲሁም የዜጎችን በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እና ሌሎች ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች በቂ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ አጽንዖት ተሰጥቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የቤት አቅርቦት አማራጮችን ማስፋት፣ የተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮግራሞችን በስፋት መተግበርና ለዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ፣ ለመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተገቢውን ትኩረት እና ድጋፍ መስጠት፣ የመንግሥት እና የግል አጋርነትን (Public-Private Partnerships) ማስፋፋት እና ማጎልበት፣ የግል መኖሪያ ቤት አልሚ (ሪልስቴት) ተቋማት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ በተሻለ ሁኔታ የሚያገኙበትን አሠራር መዘርጋት እንዲሁም ድጎማዎችን እና የግብር ማበረታቻዎችን በማድረግ አልሚዎቹ የሚያቀርቧቸው ቤቶች ለአነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ መብቶች ሥራ ክፍል ኃላፊ ሃዊ አስፈው በቂ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት መጠለያን ከማግኘት ባለፈ የይዞታ ዋስትናን፣ የመሠረተ ልማት ተገኝነትን፣ የዋጋ ተመጣጣኝነትን፣ ለኑሮ አመቺነትን፣ ተደራሽነትን እና ምቹ መገኛን አጠቃሎ የያዘ በመሆኑ፣ መብቱን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት እነዚህን ማእከል ያደረጉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።