ማብራሪያ
በአረጋውያን ላይ ስለሚደርስ ጥቃት ግንዛቤ ማስጨበጫ (World Elder Abuse Awareness Day) ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. የተሟላ መፍትሔ: በአረጋዊነት ጊዜ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን በፖሊሲ፣ ሕግና ማስረጃ ላይ በተደገፉ ምላሾች መቅረፍ በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር ሲሆን ይህ ማብራሪያም ይህንን ቀን ምክንያት በማድረግ በአረጋውያን ላይ ስለሚደርስ ጥቃት ግንዛቤን ለመፍጠር በማለም የተዘጋጀ ነው፡፡
አረጋውያን እነማን ናቸው?
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) እንዲሁም በአፍሪካ አረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል ትርጓሜ መሠረት አረጋውያን የሚባሉት ዕድሜያቸው 60 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ናቸው። በኢትዮጵያም ይህ ተቀባይነት አግኝቶ ተመሳሳይ ትርጓሜ ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል፡፡
በአረጋውያን ላይ የሚደርስ ጥቃት ምን ማለት ነው?
በአረጋውያን ላይ የሚደርስ ጥቃት የምንለው ሆን ተብሎ በሚደረግ ድርጊት ወይም አስፈላጊው ድርጊት ወይም እርምጃ ባለመወሰዱ ምክንያት በአረጋውያን ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጉዳት ነው፡፡ ድርጊቱ አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጠር ወይም ተደጋጋሚነት ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ በአረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በአብዛኛው የሚፈጸሙት በአረጋውያን ልጆች (ዘመዶች) ተንከባካቢዎች እንዲሁም ሌሎች የቅርብ ሰዎች መሆኑንም የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
በዓለማችን የአረጋውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ባለበት ሁኔታ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አረጋውያን የጥቃት ሰለባ ናቸው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሠረት በዓለማችን ላይ ከ 6 አረጋውያን አንድ አረጋዊ/ት ላይ ጥቃት ይደርሳል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ጉዳይ በዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ዘንድ የሚገባውን ያህል ዕውቅና ያላገኘ እና ቸል የተባለ ጉዳይ ነው፡፡ በአረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንደ ግል ጉዳይ ከፍ ሲልም ስለ ጥቃቱ ማውራት እንደ ነውር የሚታይባቸው ማኅበረሰቦች አሉ፡፡ አረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የሚገባቸውን ያህል ዕውቅና ብሎም መፍትሔ እንዳያገኙ ማነቆ የሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህም፡-
- ጥቃቶቹ የሚፈጸሙት በአብዛኛው በቅርብ ሰዎችና ለሰዎች ብዙም ግልጽ ባልሆኑ ቦታዎች (ለምሳሌ፡- በመኖሪያ ቤቶች፣ በእንክብካቤ ማእከላት ወዘተ) መሆኑና ይፋ የማይወጡ/ተደብቀው የሚቀሩ በመሆኑ፤
- አረጋውያኑ በአብዛኛው በጥቃት አድራሾች ስር የሚተዳደሩ በመሆኑ፤
- የአረጋውያን ጥቃት ትኩረት የማይሰጠው እና መኖሩም እምብዛም የማይታወቅ በመሆኑ፤
- ስለ አረጋውያን ጥቃት በግልጽ ማውራት በማኅበረሰቡ እንደ ነውር የሚቆጠር በመሆኑ፤
- ጥቃት የደረሰባቸው አረጋውያን ፍትሕ ለማግኘት ‘እንዴት?’ እና ‘ወዴት?’ መሄድ እንዳለባቸው መረጃ የማያገኙ በመሆኑ፤
- በቂ እና ግልጽ የሕግ ማእቀፍ እንዲሁም አረጋውያንን የሚያካትት የፍትሕ ሥርዓት አለመኖር ዋነኞቹ ናቸው፡፡
አረጋውያን ላይ የሚደርሱ የጥቃት አይነቶች ምን ምን ናቸው?
አረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የተለያየ መልክ ሊይዙ ይችላሉ:: እነዚህም፡-
- አካላዊ (Physical) ጥቃት፡- አረጋውያን ላይ የሚወሰድ የኃይል እርምጃ ሲሆን ይህም አረጋውያንን መምታት፣ ማሰቃየት፤ መገፍተር፣ አካላዊ እንግልት እና አካላዊ ክልከላ ማድረግን ያካትታል፡፡
- ሥነ ልቦናዊ (Psychological) ጥቃት፡- አረጋውያን ላይ ፍርሀት፣ ጭንቀት እንዲሁም ጥርጣሬን የሚፈጥሩ ድርጊቶች ሲሆኑ፤ ለምሳሌ አረጋውያንን ማስፈራራት፣ ማመናጨቅ፤ የንቀት ንግግሮችን መናገር፣ ስድብ፣ ዛቻ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዳይገናኙ ክልከላ ማድረግን ያካትታል፡፡
- ምዝበራ (Financial abuse)፡- አረጋውያኑ ፍቃዳቸውን ባልሰጡበት ሁኔታ በሕገ-ወጥ እና ተገቢ ባልሆነ መልኩ የአረጋውያንን ሀብት መጠቀም ነው፡፡
- ጾታዊ (Sexual) ጥቃት፡- ፍቃዳቸውን ባልሰጡበት ሁኔታ በግዳጅ ከአረጋውያን ጋር የሚፈጸም ማንኛውም ዐይነት ወሲባዊ ግንኙነት ማለት ነው፡፡
- ቸልታ (Neglect)፡- አረጋውያን የሚፈልጉትን አገልግሎት መንፈግ፣ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን አለማሟላትን ይገልጻል፡፡
- መዘንጋት/መተው (Abandonment)፡- አረጋውያንን ያለተንከባካቢ እና አጋዥ ጥሎ መሄድን፤ አረጋውያኑን እንዲንከባከብ ኃላፊነት የተጣለበት ሰው ሆን ብሎ ወይም በግዴለሽነት ያለሌላ ተንከባካቢ ጥሎ መሄድን ይገልጻል፡፡
አረጋውያን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የት ሊፈጸሙ ይችላሉ?
ከላይ የተዘረዘሩት የጥቃት ዐይነቶች አረጋውያን በቋሚነት እና በጊዜያዊነት በሚኖሩባቸው የተለያዩ ቦታዎች ሊደርሱባቸው ይችላሉ፡፡ አረጋውያን በጋብቻ ሁኔታ፣ ማኅበራዊ ደረጃ፣ ጾታ፣ አካል ጉዳተኝነት፣ ጤና፣ የማይመች የመኖሪያ ቦታ፣ ግጭት፣ ወዘተ የተነሣ በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የራሳቸውን ቤት ጨምሮ በተለያዩ የመኖሪያ ቦታዎች፣ ከልጆች ወይም ከዘመዶቻቸው ጋር፣ በእንክብካቤ ማእከላት፣ በስደተኞች ወይም በተፈናቃዮች መጠለያዎች፣ በሃይማኖት ወይም በአምልኮ አጸዶች፣ ጎዳናዎች፣ ማረሚያ ቤቶች ወዘተ… ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ የመኖሪያ ሁኔታዎች አረጋውያን እንደሚኖሩበት ቦታ እና በሚኖሩበት ቦታ ላይ በቋሚነት በሚንከባከቧቸው ሰዎች ለተለያዩ ጥቃቶች ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ለጥቃት ተጋላጭነታቸውም እንደ ሁኔታው/ቦታው ይለያያል፡፡
ለምሳሌ ግጭት ባለበት አካባቢ የሚኖሩ አረጋውያን ለጥቃት ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሴት አረጋውያን ከወንድ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኛ አረጋውያን ከጉዳት አልባ አረጋውያን በበለጠ ሁኔታ ለጥቃት ተጋላጭ ናቸው፡፡
አረጋውያን ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች አንጻር የኢትዮጵያ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ምንም እንኳ የተጠናቀረ እና አሀዛዊ ሀገራዊ መረጃ ባይኖርም አረጋውያን ላይ የሚደርስ ጥቃት መኖሩን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የማኅበረሰቡ ባህል እና እሴቶች አረጋውያን ብዙውን ጊዜ ከልጆቻቸው ወይንም ከዘመዶቻቸው ጋር እንዲኖሩ የሚያበረታታ በመሆኑ ብዙኃኑ አረጋውያን በዚሁ የአኗኗር ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከላት ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው አረጋውያንም በማእከላት ተሰባስበው ይኖራሉ፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች አረጋውያን በቅርብ ተንከባካቢዎቻቸው/በልጆቻቸው ወይንም በሌሎች የቅርብ ሰዎች ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ በማኅበረሰቡ በከፍተኛ ሁኔታ ሰርጸው በሚገኙት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶች ምክንያት አረጋውያን ስለሚደርስባቸው ጥቃት በግልጽ እንዳያወሩ እና ደብቀው እንዲኖሩ ከፍተኛ ጫና ይደረግባቸዋል፡፡
በተጨማሪም በግጭት እና በጦርነት ምክንያት አረጋውያን ቤት እና ንብረታቸውን በመተው በመጠለያ ካምፕ ውስጥ አልያም ከቀያቸው ርቀው በጎዳና እንዲሁም በሌሎች አማራጭ የመኖሪያ ስፍራዎች ይኖራሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች አረጋውያን ለዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ይጋለጣሉ፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች የሚኖሩ እንዲሁም በግጭቱ ምክንያት መኖሪያቸውን በመጠለያ ካምፕ ያደረጉ አረጋውያን ለጅምላ ጥቃት፣ ለሞት፣ ለአካል እና ለሥነልቦና ጉዳቶች፣ ወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃቶች እንዲሁም ለንብረት ውድመት፣ ዘረፋ እና ገፈፋ መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የምርመራ እና ክትትል ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡
የአረጋውያን ከጥቃት የመጠበቅ መብትን በተመለከተ ያሉ የሕግ ማእቀፎች የትኞቹ ናቸው?
የአረጋውያን ከማንኛውም ጥቃት የመጠበቅ መብት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ዕውቅና ተሰጥቶት የሚገኝ መብት ነው፡፡ ለዚህ መብት ዕውቅና ከሰጡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መካከልም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን፣ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሎአዊ ልዩነት ለማስወገድ የተደረገ ስምምነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አረጋውያን ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ ከሌሎች ጋር እኩል የመሆንና ከአድሎ እና መገለል የመጠበቅ መብት አላቸው፡፡
በአፍሪካ የአረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል አንቀጽ 8 እና 9 መሠረት አረጋውያን ከጥቃት እና ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲሁም ሴት አረጋውያን ጾታን መሠረት ካደረገ ጥቃት፣ አድሎ እና ከወሲባዊ ትንኮሳ የመጠበቅ መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡
በተጨማሪም አረጋውያን የተጠበቁላቸውን ሰብአዊ መብቶች ከሌሎች እኩል እንዲጠቀሙ ለማስቻል የተ.መ.ድ. የሚከተሉትን የአረጋውያን መርሖች ያወጣ ሲሆን እነዚህን መርሆች መንግሥት በተቻለ መጠን በፖሊሲ እና ፕሮግራሞቹ እንዲያካትት ይጠበቃል።
- ነጻነት (Independence)፡- አረጋውያን ምግብ፣ ንጹሕ ውሃ፣ መኖሪያ ቤት፣ ልብስና የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶችን ማግኘት እንዲችሉ በቤተሰብ እና በማኅበረሰብ ሁኔታዎች ሊመቻቹላቸው እንደሚገባ፤
- ተሳትፎ (Participation)፡- አረጋውያን ጉዳያቸውን በሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንዲሁም ዐቅምና ፍላጎታቸው ከግምት ተወስዶ ልምድና ዕውቀታቸውን ለአዲሱ ትውልድ እንዲያካፍሉ መድረኮች ሊመቻቹላቸው እንደሚገባ፤
- እንክብካቤ (Care)፡- እንደማኅበረሰቡ ባህላዊ እሴቶች፣ አረጋውያን ከቤተሰብና ከማኅበረሰቡ እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ፤
- ራስን መቻል (Self-fulfillment)፡- ዐቅማቸው ጎልብቶ በማኅበረሰቡ ውስጥ በትምህርት፣ በባህል፣ በቁሳቁስ እንዲሁም መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ውጤታማ የሆኑ አጋጣሚዎችን መጠቀም እንዲችሉ ማድረግ እንደሚገባ፤
- ክብር (Dignity)፦ አረጋውያን ክብር እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ ከማንኛውም የጥቃት ዐይነቶች ተጠብቀው በክብር ሊኖሩ እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡
በአጠቃላይ በአረጋውያን ላይ የሚደርስ ጥቃት ከመቀነስ ብሎም ከማስወገድ አኳያ ዓለም አቀፍ የአረጋወያን መብቶች ስምምነት መኖር የጎላ ሚና የሚኖረው በመሆኑ ስምምነቱን አስመልክቶ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን መደገፍ እና ማፋጠን አስፈላጊ ነው፡፡ በተጨማሪም መንግሥት እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በአረጋውያን ላይ ስለሚደርሱ ጥቃቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ እንዲሁም አረጋውያንን ከሚደርስባቸው ጥቃት በመጠበቅ ረገድ ያለባቸውን ኃላፊነት መወጣት እና ጥቃት ፈጻሚዎችም ጉዳያቸው በሕግ አግባብ እንዲታይ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡