የባለሙያ አስተያየት ከኢሰመኮ
ሽመልስ አሻግሬ 
የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል 
ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያ 
shimels.ashagre@ehrc.org 

የዓለም አቀፉ የብሬል ቀን ዓላማ የዐይነ ስውራንን እና የከፊል ዐይነ ስውራንን ሰብአዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ እውን ለማድረግ ብሬል አስፈላጊ የመገናኛ ዘዴ እንደሆነ ግንዛቤ መፍጠር ነው። ዐይነ ስውራን ወይም ከፊል ዐይነ ስውራን ብሬልን መጠቀማቸው ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ጠቃሚ መረጃ ከማስገኘት በተጨማሪ ብቃትን፣ ነጻነትን እና እኩልነትን የሚያሰፍን ነው። በመሆኑም መንግሥታት ለብሬል ትምህርት መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ተገቢ እርምጃ መውሰድ አለባቸው።

በኢትዮጵያ ዐይነ ስውራን እና ከፊል ዐይነ ስውራን ከትምህርት፣ ከሥራ እና ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ጋር በተያያዘ በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጥሟቸዋል። የብሬል ዕውቀት ማነስ ዋነኛው የተግዳሮቶች ምንጭ መሆኑ ይነገራል። የብሬል ዕውቀትን በመላ ሀገሪቱ ማስፋፋት በዋነኝነት የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም የዐይነ ስውራን ማኅበራትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የብሬል ትምህርት በሁሉም ደረጃ ባለ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲስፋፋ በመደገፍ አስተዋጽዖ ሊያደርጉ ይችላሉ።

በተጨማሪም ከዚህ በታች የተጠቀሱት እርምጃዎች በዚህ ረገድ ጠቃሚ ይሆናሉ፡-

  • በሁሉም ደረጃ አካታች ትምህርትን ለማስፈጸም ብሬል በጣም አስፈላጊ ነው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ አብዛኞዎቹ ዐይነ ስውራን እና ከፊል ዐይነ ስውራን በብሬል መጻፍ አይችሉም።1 የዚህ ችግር መንስዔ በመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ብሬልን ለዐይነ ስውራን እና ከፊል ዐይነ ስውር ሕፃናት ለማስተማር ብቃት ያላቸው መምህራን አለመኖራቸው ነው። በመሆኑም መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ የልዩ ፍላጎት ሥርዓተ ትምህርትን ከዚህ አኳያ በድጋሚ ማጤን ያስፈልጋል።
  • በዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት እንደተመላከተው መንግሥት ከዐይነ ስውራን እና ከፊል ዐይነ ስውራን ማኅበራት ጋር በቅንጅት መሥራት አለበት። የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ ዐይነ ስውራን እና ከፊል ዐይነ ስውር ሕፃናትን በአካቶ የትምህርት ሥርዓት ማስተማር ቢሆንም ትምህርት ቤቶቹ ተገቢ የሆኑ የብሬል ማስተማሪያዎች እና መምህራን የሏቸውም። ይህ ችግር በመላ ሀገሪቱ ያሉ የብሬል ዕውቀት ባላቸው አባላት የተቋቋሙ ማኅበራትን የማሳተፍ ጠቃሚነት የሚያሳይ ነው።
  • በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዐይነ ስውራንን እና ከፊል ዐይነ ስውር ተማሪዎችን ተመጣጣኝ ማመቻቸት ፍላጎቶች የሚያስተናግዱት የድምጽ መቅረጫዎችን በማቅረብ ነው። ተማሪዎችም መምህራን የሚሰጡትን ትምህርት ለማስታወስ የድምጽ መቅረጫዎችን ይጠቀማሉ። ከዝቅተኛ ወጪያቸው አንጻር ብዙ ተማሪዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚቆዩበት ጊዜ እነዚህን መሣሪያዎች ይመርጣሉ። ሆኖም እነዚህን መሣሪያዎች በብቸኝነት መጠቀም በተማሪዎች የእንግሊዘኛ ቃላት ችሎታ እንዲሁም የአጻጻፍ ክህሎታቸው ላይ አሉታዊ ውጤትን ያስከትላል ።
  • የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በዐይነ ስውራን እና ከፊል ዐይነ ስውራን ተማሪዎች ሕይወት ላይ የራሳቸው የሆነ አወንታዊ ተጽዕኖ አላቸው። ደጋፊ ሶፍትዌሮች የተጫኑባቸው ኮምፒውተሮች፣ ዐይነ ስውራንን እና ከፊል የዕይታ ችግር ያለባቸው ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ጉዟቸው የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ቀርፎላቸዋል። የኮምፒውተር ስክሪን ለማንበብ የሚያስችሉትን ጆብ አክሰስ ዊዝ ስፒች (Job Access with Speech- JAWS) እና ነንቪዥዋል ዴስክቶፕ አክሰስ (Nonvisual Desktop Access- NVDA) መተግበሪያዎችን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም እነዚህን ሶፍትዌሮች መጠቀማቸው የዐይነ ስውራንን እና ከፊል ዐይነ ስውር ተማሪዎች የብሬል ዕውቀት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን አሳድሯል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኮምፒውተር ጽሕፈትን ወደ ብሬል ጽሑፍ የሚቀይር መሣሪያ (Refreshable Braille Display) ማቅረብ አለባቸው። ይህም ሙሉውን ሰነድ በብሬል ማተም ሳያስፈልግ ተማሪዎች ሶፍትኮፒ ሰነዶችን በብሬል እንዲያነቡ እንዲሁም የቃላትና የጽሑፍ ክህሎታቸውን ለማዳበር የሚረዳ ነው።
  • የዐይነ ስውራንን እና ከፊል ዐይነ ስውራንን መረጃ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ፣ በተቻለ መጠን መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሁሉንም የቀለም ጽሑፎች ወደ ብሬል የሚቀይር ማሽን ኢምቦሰር (Embosser) በመግዛት ሰነዶቻቸው በብሬል እንዲገኙ ማድረግ ይኖርባቸዋል።