የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. 

መግቢያ 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ መሠረት ነጻ የፌዴራላዊ መንግሥት አካል ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) የተቋቋመና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ፣ ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ የሚሠራ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ነው፡፡ በተሻሻለው ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 6/11/ መሠረት ኮሚሽኑ ሕዝበ ውሳኔን ጨምሮ በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል የማድረግ ስልጣን እና ኃላፊነት አለው፡፡ 

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል (ደ/ብ/ብ/ሕ/ክ) የሚገኙ 6 ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እንዲሁም 5 ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) አዲስ ክልል ለመመሥረት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ እና ውጤቱን እንዲያቀርብ ለቦርዱ ማሳወቁ የሚታወስ ነው፡፡

ይህንን ተከትሎም ምርጫ ቦርዱ የሚከተለውን የአፈጻጸም መርኃ ግብር/የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጓል፡- 

  • የሕዝበ ውሳኔ ክንውን ዝግጅቶችን ለማከናወን ከመስከረም 2 እስከ ኅዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ፤ 
  • የሲቪል ማኅበረሰብ እና ሚዲያ ዕውቅና ለመስጠት ከጥቅምት 15 እስከ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ፤ 
  • የመራጮች ምዝገባና ተያያዥ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ከታኅሣሥ 11 እስከ ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ፤
  • ለምርጫ ቅስቀሳ ከጥቅምት 7 እስከ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ እንዲሁም የሕዝበ ውሳኔ ቀን ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲከናወን፤
  • በተጨማሪም በ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ በውጤት አገላለጽ እና ሌሎች የሕግ ጥሰቶች በመስተዋሉ በጌዴኦ ዞን በቡሌ የምርጫ ክልል ድጋሚ ምርጫ የሚከናወን መሆኑን ቦርዱ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ 

ኢሰመኮ እነዚህን በቅድመ-ሕዝበ ውሳኔ እንዲሁም የሕዝበ ውሳኔ ድምፅ መስጫ ቀን ሂደቶች የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶችን ያሟሉ ለመሆናቸው ክትትል ያከናወነ ሲሆን፤ በድኅረ-ሕዝበ ውሳኔ ያሉትንም የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች መከታተሉን ይቀጥላል፡፡ 

ኮሚሽኑ ለድምፅ መስጫ ዕለት የክትትል ሥራ 64 አባላት ያሉት የሰብአዊ መብቶች ክትትል ባለሙያዎችን በቡድን አቀናጅቶ አሰማርቷል፡፡

ክትትል የተደረገባቸው አካባቢዎች 

ኮሚሽኑ ሕዝበ ውሳኔ በሚካሄድባቸው በሁሉም ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ቢያንስ አንድ የክትትል ቡድን አሰማርቷል፡፡ በተጨማሪም ተመጣጣኝ (proportional) የሆነ ሥነ-ዘዴን በመጠቀም ኮሚሽኑ የስምሪት እቅድ ያዘጋጀ ሲሆን በዚህም መሠረት እንደየምርጫ ጣቢያዎች ብዛት በርካታ የሕዝበ ውሳኔ ጣቢያዎች በሚገኙባቸው ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በርካታ የሰብአዊ መብቶች የክትትል ባለሙያዎችን በማሰማራት ሕዝበ ውሳኔውን ተከታትሏል፡፡ እንዲሁም ቀደም ሲል በተሰናዱ መስፈርቶች መሠረት በተለዩ 186 የምርጫ ጣቢያዎች በድምፅ መስጫ ዕለት በመገኘት የሰብአዊ መብቶች ክትትል አከናውኗል፡፡

ይህ ቀዳሚ ሪፖርት በዋናነት ይህንኑ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. የተደረገውንና በኮሚሽኑ ክትትል በተሸፈኑ የምርጫ ጣቢያዎች እና ትኩረት በተደረገባቸው የሰብአዊ መብቶች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ በቅድመ ሕዝበ ውሳኔ እና በድኅረ-ሕዝበ ውሳኔ ያከናወናቸውን ክትትሎች ጨምሮ የደረሱትን አቤቱታዎች እና ጥቆማዎች እንዲሁም የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት በተመለከተ የደረሰባቸውን ግኝቶች ያካተተ ዝርዝር ሪፖርት የማጠናቀር ሥራው እንደተጠናቀቀ ወደፊት ይፋ የሚያደርግ ይሆናል። ስለሆነም በዚህ ቀዳሚ ሪፖርት የተመለከቱ ሁኔታዎች ስለአጠቃላይ የምርጫው ሂደት የተሰጠ ድምዳሜ አይደለም፡፡ 

የክትትል ዋና ዋና ግኝቶች 

እምርታዎች

  1. አጠቃላይ የጸጥታ ሁኔታን በሚመለከት ሕዝበ ውሳኔው በተረጋጋ ሁኔታ እና አሳሳቢ የጸጥታ ሥጋት ሳይከሰት የተካሄደ መሆኑ፤ 
  2. የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ በእኩልነት የመሳተፍ መብት እንዲሁም መፈናቀል ሁኔታን መሠረት ያደረገ መድሎ ሳይደረግባቸው በሕዝበ ውሳኔው መሳተፋቸውን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ማቋቋሙ፤ በተጨማሪም በሌሎች መደበኛ የምርጫ ጣቢያዎችም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ተመላሾች በምርጫው የሚሳተፉበት ሁኔታ መመቻቸቱ፤
  3. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኮሚሽኑ ጋር በነበረው ወቅታዊ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት መሠረት በምርጫው ሂደት ላይ የታዩ ጉድለቶችን ወይም ግድፈቶችን ለማስተካከል አፋጣኝ የእርምት እርምጃዎች መወሰዳቸው፤ ለምሳሌ በሰላም በር አካባቢ ተሰማርቶ የነበረው የኮሚሽኑ የክትትል ቡድን የገጠመውን ተግዳሮት ቦርዱ ተገቢውን ክትትል በማድረግ በአፋጣኝ ሊፈታ መቻሉ እንዲሁም ኮሚሽኑ በቅድመ-ሕዝበ ውሳኔ በመራጮች ምዝገባ ወቅት ባደረገው ክትትል በጋሞ ዞን ጋሌ ቀበሌ ጎጎራ የሠፈራ ጣቢያ ላይ የሚገኙ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ የቤተሰብ ኃላፊዎች በመራጮች ምዝገባ አለመካተታቸውን ተመልክቶ በሰጠው ምክረ-ሐሳብ መሠረት ቦርዱ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ በምርጫው እንዲሳተፉ መደረጋቸው፤
  4. በምርጫው ሂደት የተከሰቱ የሕግ ጥሰቶችን እና ሥርዓትን ያልተከተሉ አሠራሮችን በተመለከተ ቦርዱ ወቅታዊ ምላሽ በመስጠት ሕጋዊ የአስተዳደር እርምጃዎች መወሰዳቸው፤ ለምሳሌ በወላይታ ዞን በሌ የምርጫ ማእከል ሶርቶ ቀበሌ ሶርቶ 1 ምርጫ ጣቢያ ድምፅ በመስጠት ሂደት ወቅት የተወሰኑ የቀበሌ አስተዳደር ኃላፊዎች በምርጫ ጣቢያው የመታወቂያ ወረቀት ሲያድሉ መገኘታቸውን ተከትሎ፤ ቦርዱ ምርጫ ጣቢያው ላይ የተፈጸመው የሕግ ጥሰት እስኪጣራ ድረስ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ እንዲቋረጥ አድርጎና ጉዳዩ ከተጣራና በተጠርጣሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ከተወሰደ በኋላ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ እንዲቀጥል መደረጉ፤
  5. የሀገር ውስጥ ሲቪል ማኅበራት የምርጫ ታዛቢዎች መሳተፋቸው፤
  6. በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋውያን፣ ለነፍሰ ጡሮች እና ሕፃናት ልጆች ለያዙ እናቶች ቅድሚያ ይሰጥ የነበር መሆኑ ከአዎንታዊ ጎኖች ውስጥ ናቸው፡፡

አሳሳቢ ክስተቶች

ከላይ የተዘረዘሩት አበረታች እምርታዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የሚከተሉት አሳሳቢ ክስተቶችና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች ተለይተዋል፦

  • በ 9 የምርጫ ጣቢያዎች የአካባቢው መንግሥት አመራሮች በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ለመራጮች ምን መምረጥ እንዳለባቸው በመንገርና ትዕዛዝ በመስጠት፣ የማስፈራራት፣ የማዋከብ እና በመራጮች ላይ ጫና የሚያሳድሩ ድርጊቶችን መፈጸማቸው፤
  • በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር.1162/2011 ላይ ክልከላ ከተደረገባቸው ቦታዎች ውስጥ 6 የምርጫ ጣቢያዎች በሕክምና መስጫ ቦታ፣ በማኅበረሰብ ፖሊስ ማእከል፣ በግል መኖሪያ ቤት እና በፖለቲካ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢዎች ውስጥ የነበሩ መሆኑ፤ (ኮሚሽኑ ስለዚህ ጉዳይ ባደረገው ማጣራት በአንዳንድ ቦታዎች የምርጫ ጣቢያን ለማደራጀት አማራጭ አመቺ ቦታ በመጥፋቱ የሚከሰት ችግር ሲሆን፤ ቦርዱ የተቻለውን ያህል ጥረት እያደረገበት መሆኑንና ለወደፊቱም ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተለው መሆኑን ኮሚሽኑ ተረድቷል።)
  • በ15 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ከ500 ሜትር ርቀት በታች ዩኒፎርም የለበሱ እና/ወይም የታጠቁ የጸጥታ አካላት (የአካባቢው ፖሊስ እና ሚሊሻዎች) መታየታቸው፣ (በአንጻሩ የተሟላ የምርጫ ጣብያ አስፈጻሚዎች ባልነበሩባቸው የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የጸጥታ ኃይሎች የመራጮች ሰልፍ ሥርዓቱን ሲያስከብሩ እና አጠቃላይ ጥበቃ ሲያደርጉ የነበረ መሆኑንም ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡) 
  • በቡርጂ ልዩ ወረዳ በዳሊዮ የምርጫ ጣቢያ 851 መራጮች ተመዝገበው የነበሩ ቢሆንም በምርጫው ዕለት ከ 3 የምርጫ ጣቢያዎቹ ሠራተኞች በስተቀር አንድም ሰው እንኳን በምርጫው ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው፤
  • በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን ተደራሽ ያልነበሩ መሆኑ፣ በ 35 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለመራጮች በተዘጋጀ የሚስጥራዊ ድምፅ መስጫ ቦታ ውስጥ አብሮ በመግባት ሚስጥራዊነቱ ያልተጠበቀ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት መታየቱ፣ በ 21 የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ካርድ እና/ወይም መታወቂያ ካርድ ሳይዙ እንዲመርጡ የተፈቀደላቸው ሰዎች መታየቱ፣ በ 7 የምርጫ ጣቢያዎች በሕግ ከተቀመጠው የሰዓት ገደብ ውጪ ዘግይተው ወይም ቀድመው የተከፈቱ መሆኑ። 

መደምደሚያ እና ማጠቃለያ 

ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው ቦታዎች ከታዩ መለስተኛ የምርጫ አስተዳደር ግድፈቶች (minor electoral irregularities) ውጪ፤ አጠቃላይ ምርጫው ሰላማዊ፣ ሥርዓታዊ እና ከጎላ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነጻ የነበረ ነው (peaceful, orderly and free from major human rights violations)።

ከላይ የተጠቀሱት እምርታዎችን ማጠናከር እና መልካም አሠራሮችን ተቋማዊ አድርጎ መቀጠል እንዲሁም የአሠራር ግድፈቶች እና ጉድለቶችን ማረም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ዜጎች፣ የጸጥታ እና ሌሎች የመንግሥት አካላት ኃላፊነት በመሆኑ የሁሉንም ጥረትና በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በተለይም፡-

  • የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎችን የመመልመል እና የማሠማራት ክንውን ላይ ገለልተኝነት፣ ሙያዊ ብቃትና ሥነ-ምግባር እንዲሁም በቂ የሆነ ስልጠና መተግበሩን ለማረጋገጥ እንዲሁም በዚህ የምርጫ ሂደት ተገቢውን ብቃትና ሥነ ምግባር ያሳዩ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችለውን ሥርዓት ለማበጀት የሚያደርጋቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ 
  • የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምርጫ የመታዘብ ሽፋን ለማስፋት ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ፣ እንዲሁም 
  • የጸጥታ እና አግባብነት ያላቸው የመንግሥት አካላት ሁሉ በምርጫ እና ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ በሚጠይቁ ሂደቶች ላይ አስፈላጊውን ትብብር እና ቅንጅት እንዲኖር እንዲያስችሉ ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል። 

የሕዝበ ውሳኔ ሂደቱን በተመለከተ የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በሕዝበ ውሳኔ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ባደረጉባቸው አካባቢዎች መራጮች ድምፅ ለመስጠት ያሳዩት ተነሳሽነት እና ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ገልጸው “ዜጎች በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ እና ሰብአዊ መብቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ በመተግበር የሰብአዊ መብቶች ባህልን ለማዳበር አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡