የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ

ኅዳር 8 ቀን 2014 ዓ.ም. 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ከታወጀበት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ከአዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችን አያያዝ፣ የእስር ሁኔታና የታሳሪዎችን ሁኔታ ለመከታተል በሚያስችለው መልኩ መረጃ ማሰባበሰብ አለመቻሉ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ገለጸ።  

ኮሚሽኑ ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው በተለይም በፌደራል ደረጃ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ የክትትል ቡድኖች በማሰማራት ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ እና በየካ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችንና ማቆያዎችን ጎብኝቷል፣ ታሳሪዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን አነጋግሯል፣ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ደረጃ ካሉ ከፖሊስ አባላት እና አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ መረጃዎችን አሰባስቧል፡፡ በተጨማሪም የሚቀርቡለትን ጥቆማዎች እና አቤቱታዎች መሰረት በማድረግ መረጃዎችን አጠናክሯል፡፡ 

በአንጻሩ የአዲስ ከተማ፣ የልደታ፣ የጉለሌ፣ የቦሌ እና የአራዳ ክፍለ ከተማ ኃላፊዎች ከበላይ ትእዛዝ ካልመጣልን መረጃ አንሰጥም፣ እስረኛም መጎብኘት አትችሉም በማለታቸው ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ኃላፊነት እንዳይወጣ ምክንያት ሆነዋል፡፡  

በኮሚሽኑ ክትትል የታሰሩ ሰዎችን ብዛት በሚመለከት የተሟላ መረጃ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ ኮሚሽኑ በአንጻራዊነት የተሟላ መረጃ ያገኘው ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሲሆን መረጃው በተሰጠበት ኅዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም በክፍለ ከተማው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ 714 ሰዎች መታሰራቸውንና ከነዚህም ውስጥ 124ቱ ሴቶች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል። በሌሎችም ክፍለ ከተሞች በተመሳሳይ ሁኔታ እስሮች ሲከናወኑ ስለነበርና በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሂደት አሁንም የቀጠለ በመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸው ይገመታል። በድሬዳዋ ከተማ ደግሞ እስከ 300 የሚሆኑ ሰዎች ታስረዋል።

የተወሰኑ ሰዎች በሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት መረጃ መሰረት የሚታሰሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ግን ከህብረተሰቡ ተገኘ በተባለ ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ስር እንደሚውሉና ከመካከላቸው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ሰዎች ብዛት ከፍተኛ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በዚህ ረገድ ብሔር ተኮር እስር ስለመከናወኑ ተጠይቀው ለኮሚሽኑ ምላሽ የሰጡት የሕግ አስከባሪ አካላት “ሰዎች የሚያዙት በብሔራቸው ምክንያት ሳይሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ተጠርጥረው እንደሆነና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት ሁለቱም ድርጅቶች ብሔር ተኮር ድርጅቶች ከመሆናቸው አኳያ የሚያዙ ሰዎች የአንድ ብሔር ሊመስሉ እንደሚችሉ” ተናግረዋል፡፡ 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራሉ ተብለው ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠሩ ሰዎችን ይዞ የማቆየት ሥልጣን ለሕግ አስከባሪ አካላት መስጠቱን እና የተባሉት ቡድኖች ብሔር ተኮር ድርጅቶች መሆናቸውን ኢሰመኮ ይገነዘባል። ይሁንና በጥቆማ ላይ የተመሰረቱ እስሮችን በተመለከተ የጥቆማዎቹ መነሻ የሰዎቹ የብሔር ማንነት አለመሆኑን ለማረጋገጥ እና ምክንያታዊ ጥርጣሬ ስለመኖሩ ለማጣራት በቂ ጥረት እየተደረገ አይደለም። በተጨማሪም በአንዳንድ ጣቢያዎች ከአዋጁ ጋር በተያያዘ የተያዙ ሰዎች የትግራይ ተወላጅ አለመሆናቸውን በማሳየት ከእስር ሲፈቱ የኢሰመኮ ባለሙያዎች ተመልክተዋል፡፡  

በተለያዩ አካባቢዎች እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆነና የተወሰኑ 80 ዓመት የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች አረጋውያን ጨምሮ፣ በማጥባት ላይ የሚገኙ ሴቶች፣ በታሳሪዎች ቤተሰቦችና በሌሎች ታሳሪዎች የአእምሮ ህመም እንዳለባቸው አልያም  ተከታታይ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ስለመሆናቸው የሚነገርላቸው ሰዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኮሚሽኑ የክትትል ቡድኖች ተመልክተዋል፡፡  

በአብዛኛው በቁጥጥር ስር የሚውሉ ሰዎች በመጀመሪያ በአቅራቢያ ወደሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች የሚወሰዱ ሲሆን፣ ብዛታቸው እየጨመረ ሲመጣ በየክፍለ ከተማው በሚገኙ ሁለገብ ወጣት ማዕከላትና አንዳንድ የትምህርት ማሰልጠኛዎች ተወስደው እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ በተለምዶ “አባ ሳሙኤል” ተብሎ በሚጠራው ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት የተወሰዱ ሰዎችም እንዳሉ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል ቤተሰቦቻቸው የት እንደታሰሩ ገና ለማወቅ ያልቻሉ ሰዎች አቤቱታም ኮሚሽኑ ተቀብሏል፡፡  

አንዳንዶቹ ጣቢያዎች እና የማቆያ ስፍራዎች በጣም የተጣበቡ፣ በቂ መጸዳጃ የሌላቸው እና በቂ አየር እና ብርሃን የማያገኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አረጋውያንንና የአእምሮ ህመምተኛ እንደሆኑ የሚነገር ሰዎችን ጨምሮ 241 ሰዎች ስፋቱ 20 ሜትር በ 10 ሜትር ብቻ በሚገመት አንድ የወጣቶች ሁለገብ አዳራሽ ተይዘው በግቢው ያለውን ብቸኛ መጸዳጃ ቤት ለመጋራት ተገድደዋል፡፡ በአንዳንድ ጣቢያዎች ሴቶች እና ወንዶች በአንድ ክፍል ውስጥ ተቀላቅለው መያዛቸውንና በክፍሉ ውስጥ የአእምሮ መረበሽ የሚታይባቸው ሰዎችም እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡ 

ኢሰመኮ ጉብኝት ባደረገበት ጊዜ በአብዛኛዎቹ ማቆያ ስፍራዎቹ ታሳሪዎች የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት አለመዘርጋቱን እና ከታሳሪዎች መካከልም  በህመም የሚያቃስቱ ሰዎች እንደነበሩ ለመመልከት ተችሏል፡፡ ኮሚሽኑ በጎበኛቸው ማቆያ ስፍራዎች ምንም ዓይነት የኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ ጥንቃቄዎች አይደረጉም፡፡  ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት ያልቻሉ ሰዎች፣ በድንገት ከስራ ቦታቸው ወይም ከመንገድ ላይ በመታሰራቸው አስፈላጊ የስራ ሰነዶች እና ቁሳቁስ ለመስሪያ ቤታቸው ማስረከብ ያልቻሉ ሰዎችንም ኮሚሽኑ አነጋግሯል። 

የአብዛኛዎቹ ታሳሪዎችም ቅሬታ የተያዙት በብሔራቸው ምክንያት እንደሆነ እንደሚያምኑና እና የተጠረጠሩበትን እና የተያዙበትን ምክንያትም እንዳልተነገራቸው መሆኑን ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ታሳሪዎች በማቆያ ስፍራዎቹ በጥበቃ ላይ በተሰማሩት የፖሊስ አባላትም ሆነ በተያዙበት ወቅት ድብደባ  ወይም አካላዊ ጥቃት እንዳልደረሰባቸው ለኮሚሽኑ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ጉብኝት ባደረገባቸው የተወሰኑ ቦታዎች የሚሰሩት የፖሊስ አባላትም በተቻላቸው አቅም ታሳሪዎችንና ቤተሰቦቻቸውን በአግባቡ ለማስተናገድ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የታሳሪዎቹ ብዛት የእስር ሁኔታውን በአግባቡ ለማስተዳደር እንዳስቸገራቸው  መመልከት ይቻላል፡፡ 

በአንዳንድ ክፍለ ከተማዎች አረጋውያንን እና ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ከእስር መለቀቃቸው አበረታች እርምጃዎች ታይተው ነበር፡፡ ይሁንና ከእስር የመፍታትና የማጣራት ሂደቱ ወጥ ባለመሆኑና በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች በእድሚያቸው ወይም በሕክምና ምክንያት የተለቀቁ ሰዎች “የተለቀቃችሁት ከኮማንድ ፖስት እውቅና ውጪ ነው” በሚል ተመልሰው መታሰራቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡ 

በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ለማረጋገጥ እንደቻለው ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መተግበር ባለበት መንገድ በተለይም “የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነፃ መሆን” የሚሉትን የሰብአዊ መብት መርሆዎችን ባከበረ መልኩ አለመተግበሩን ተመልክቷል።

ስለዚህም ኢሰመኮ ለሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ አካላት የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲደረጉ ጥሪውን ያቀርባል፦  

  • በጥቆማ ብቻ የተያዙ ሰዎችን ጉዳይ በመመልከት አዋጁ በሚጠይቀው መሰረት ምክንያታዊ ጥርጣሬ መኖሩን የሚያረጋገጥ መረጃ ያልተገኘባቸውን ሰዎች ፣ እንዲሁም በተለይም በቁጥጥር ስር የዋሉ አረጋውያን፣ የሚያጠቡ እናቶች እና የጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ፣ 
  • ማንኛውም እስር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መንፈስ በመረዳት በተመጣጣኝነት፣ በጥብቅ አስፈላጊነታቸው እና ከመድልዎ ነፃ በሆነ መልኩ እንዲከናወን፣ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ጥብቅ ክትትል እንዲያደርጉ፣ በተለይም የሚያዙ ሰዎች ሁሉ የታሰሩት በምክንያታዊ ጥርጣሬ መሰረት ብቻ መሆኑን የሕግ አስከባሪ አካላት በጥብቅ እንዲያረጋግጡ፣
  • የታሰሩ ሰዎችን ሰብአዊ አያያዝ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ በተለይም የጤና፣ የመጸዳጃ እና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲመቻቹ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡  
  • በተጨማሪም ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ወቅትን ጨምሮ በማናቸውም ጊዜ ሰብአዊ መብቶችን የሚከታተል መሆኑን በመገንዘብ እና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለኮሚሽኑ የክትትል ተግባራት ትብብር የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው በመረዳት ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ ያሳስባል።