የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጸጥታ ጥበቃ እና ከገጽታ ግንባታ ጋር በተያያዘ ምክንያት በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. የንግድ ቦታቸው የፈረሰባቸው የሰላም ለሁሉም የአካል ጉዳተኞች ማኅበር አባላት ያቀረቡትን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ከግንቦት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ምርመራ አከናውኗል። ኢሰመኮ በምርመራው አቤቱታ አቅራቢዎችን እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የምክትል ከንቲባ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ፣ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እና የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን በማነጋገር እንዲሁም በአካል ምልከታ መረጃና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በግኝቶቹ መሠረት ውትወታ ሲያደርግ ቆይቷል።  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ የሸራ/ላስቲክ ቤቶችን እና ተለጣፊ ኮንቴነሮችን በማፍረስ በክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች አማካኝነት አማራጭ ተለዋጭ ቦታዎችን ያቀረበባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ኢሰመኮ በተወሰኑ የከተማዋ አካባቢዎች ለአካል ጉዳተኞች የተሰጡ አማራጭ ቦታዎችን በአካል በመገኘት ምልከታ አድርጓል። ለምሳሌ ምልከታ ያደረገባቸው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 7 በተለምዶ ጎላ ሚካኤል፣ ሪሞ ሳይት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለሰላም ለሁሉም የአካል ጉዳተኞች ማኅበር አባላት እንደ አማራጭ የቀረቡት ተለዋጭ ቦታዎች (በተለምዶ “ሼድ” በመባል የሚታወቁ የመሸጫና የማምረቻ ስፍራዎች እንዲሁም ሌሎች ባዶ ቦታዎች) በዊልቸር እና በአካል ድጋፍ ለሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኛ ሠራተኞች ተደራሽ አለመሆናቸውን ለመገንዘብ ችሏል። የገበያ ዕድል ከመፍጠር አንጻርም የተወሰኑት ቦታዎች ለማምረቻ እንጂ ለችርቻሮ ንግድ የማይሆኑ/የማያመቹ መሆናቸውን አቤቱታ አቅራቢዎቹ ያስረዳሉ።  

የንግድ ሱቆቹ ከፈረሱበት ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ ከ181 በላይ የሚሆኑ የሰላም ለሁሉም ማኅበር አባላት ከንግድ ቦታቸው ተነስተዋል። በዚህም ሳቢያ ሁኔታቸው እንደተባባሰ እና ሌላ የገቢ ምንጭ የሌላቸው በመሆኑ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር መቸገራቸውን፤ ጥቂት የማይባሉ አካል ጉዳተኞች ወደ ልመና ለመውጣት መገደዳቸውን፣ በአጠቃላይ ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ላይ መሆናቸውን አቤቱታ አቅራቢዎቹ ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢሰመኮ ዋና መሥሪያ ቤት በድጋሚ በአካል በተገኙበት ወቅት አስረድተዋል። ኢሰመኮ የምርመራውን አጠቃላይ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ያካተተ ሪፖርት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታኅሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በመላክ እና በአካል በመቅረብ ጭምር ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ከከተማ አስተዳደሩ እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ምላሽ ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል።  

መንግሥት የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባሕል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን፣ እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ሕጎችና ሰነዶች መሠረት የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ያከበሩ ሊሆኑ ይገባል። በተለይም የአካል ጉዳተኞችን የመሥራት እና ፍትሐዊና ምቹ የሥራ ሁኔታዎችን የማግኘት መብት የሚያረጋግጡ እና ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩና በማኅበረሰቡ ውስጥ ሙሉና ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ሊሆኑ እንደሚገባ እነዚህ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ይደነግጋሉ።  

ከዚህ አንጻር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔዎች እና እርምጃዎች በሥራ ላይ ተሰማርተው ቋሚ ገቢ የሚያገኙ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚፈጥሩትን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማጠናከር፣ ለሰላም ለሁሉም የአካል ጉዳተኞች ማኅበር አባላት እንዲሁም በአጠቃላይ በሀገሪቱ በሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች የንግድ ቦታቸው ለሚፈርስባቸው አካል ጉዳተኛ ነጋዴዎች የአካል ጉዳታቸውንና ፍላጎታቸውን ያማከለ ተደራሽና ተመጣጣኝ የሆነ ምትክ ቦታ እንዲያቀርብ ኢሰመኮ ያሳስባል። 

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ፣ የሥራ ዕድል ያላገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች ያሉ መሆናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት፣ በሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ አካል ጉዳተኞችን ማበረታታት እንደሚገባ ገልጸው፤ “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሰላም ለሁሉም የአካል ጉዳተኞች ማኅበር አባላት ከባቢያዊ ተደራሽነትን በበቂ ሁኔታ የሚያሟሉ ምትክ ቦታዎችን እንዲያመቻች” ጥሪ አቅርበዋል።