የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የኢፌዲሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ አበረታች እርምጃ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ኮሚሽኑ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የነበረው ሁኔታ በመሻሻሉና የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ ከግምት በማስገባት የአዋጁ አስፈላጊነት እየተገመገመ ተገቢው ማሻሻያ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቦ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግስት የቀረበለትን ውሳኔ ሃሳብ በአፋጣኝ እንደሚያጸድቀው ኮሚሽኑ ተስፋውን እየገለጸ፤ የመንግስት ስራ አስፈጻሚ አካላት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ አሁንም በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው አዋጅ የተነሳ መሆኑን ከሚያጸድቅበት ቀን ጀምሮ ከእስር ያልተለቀቁ ሰዎች የሚኖሩ ቢሆን፤ ከ48 ሰዓታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት አለመቅረብ እስሩ ከሕግ ውጭ የሚያደርገው በመሆኑ የሁሉም የሕግ አስከባሪ አካላት የሕግ ማስከበር ተግባራት የሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ በመደበኛው ሥርዓት እንዲከናወኑ ያሳስባል።