የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ኅዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም.
ኢሰመኮ የደረጃ “A” እውቅና (ወይም አንደኛ ደረጃ እውቅና -“A” Status Accreditation) እንዲያገኝ አስተዋጽዖ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ምስጋናውን አቀረበ
ከጠንካራ የግምገማ ሂደት በኋላ የሚሰጠውን የዓለም አቀፉ የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (Global Alliance of National Human Rights Institutions (GANHRI)) የደረጃ “A” (አንደኛ ደረጃ) እውቅና ማግኘቱ ኮሚሽኑ የፓሪስ መርሆችን ሙሉ በሙሉ ማሟላቱን የሚያሳይ ነው።
የዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (GANHRI) የእውቅና ገምጋሚ ንዑስ ኮሚቴ እ.ኤ.አ. ከጥቅምት 8 እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2021 ባደረገው ጉባዔ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጥምረቱ የተከናወነውን ጠንካራ የግምገማ ሂደት ማለፉን ተከትሎ፣ ለኮሚሽኑ የደረጃ “A” እውቅና (አንደኛ ደረጃ እውቅና – “A” Status Accreditation) መስጠቱን በዛሬው ዕለት አስታዉቋል (ሙሉ ሪፖርቱ- በእንግሊዘኛ)። ጥምረቱ ኮሚሽኑ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም የሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ እና ለማስፋፋት እየተጫወተ ያለውን ሚና አድንቆ፣ በተለይም እ.ኤ.አ. በኅዳር ወር 2013 በጥምረቱ ተለይተው የነበሩ ጉድለቶችንም ለማስተካከል ያደረገውን ጥረት አመስግኗል።
የዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (GANHRI) 118 ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት የሆኑ አባላት ህብረት ሲሆን ከፓሪስ ስምምነቶች ጋር የተጣጣሙ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት መመስረትን እና መጠናከርን የሚያበረታታ ነው። እ.ኤ.አ. በ1993 የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ያጸደቀውና በአጭሩ የፓሪስ መርሆች ተብሎ የሚጠራው የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት መርሆች (Principles Relating to the Status of National Institutions) የተቋማቱን ተዓማኒነትና ብቃት ለመገምገም የሚያገለግል ሰነድ ሲሆን፣ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋማት በሕግ፣ በአሰራር፣ በአባልነት፣ በፖሊሲ እንዲሁም በፋይናንስ ገለልተኛ እና ከጣልቃ ገብነት ነጻ እንዲሆኑ ይደነግጋል። የፓሪስ መርሆች መገምገሚያ መስፈርቶች፡- የተቋማቱ ኃላፊነት እና ሥልጣን ስፋት፣ የሰው ሃብታቸውን ብዝኃነት፣ የተግባራትና እና የገንዘብ አቅም፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና ትብብር ናቸው። የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ (UNOHCHR) የጥምረቱ (GANHRI) ጽሕፈት ቤት ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፣ የጥምረቱ የእውቅና ገምጋሚ ንዑስ ኮሚቴ (Sub-Committee on Accreditation- SCA) ደግሞ በዚሁ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት እየታገዘ የእውቅና ጉዳዮችን ገምግሞ ምክረ-ሃሳቦችን የሚያቀርብ ገለልተኛ አካል ነው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅታዊ አቋሙን እና አሰራሩን ለማሻሻል ያስቻሉ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ የተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ የተቋሙን የአሰራር እና የበጀት አስተዳደር ነፃነት ከማረጋገጡም ባሻገር በምርጫ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል ስራዎችን እንዲያከናውን እንዲሁም ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የእስር ቦታዎችን ለመጎብኘት በማስቻሉ የኮሚሽኑን ሥልጣን ከማጠናከር አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ያገኘው እውቅና ትልቅ እመርታ መሆኑን አመልክተው፣ ተቋሙን በማሻሻል ሂደት ውስጥ በመሳተፍ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም የኮሚሽኑን ተልዕኮ በማስፈጸም ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ላሉት የኮሚሽኑ ሰራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡ “ኮሚሽኑ ከኅዳር 2006 ዓ.ም ጀምሮ ከነበረበት “B (2ኛ ደረጃ) ወደ “A” (አንደኛ ደረጃ) ማደጉን የሚያረጋግጥ እውቅና መሰጠቱ ኮሚሽኑ ገለልተኛ፣ ውጤታማ እና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን የሚያሟላ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም መሆኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያረጋግጥ ነው” በማለት አክለው ገልጸዋል።
ኢሰመኮ ወደ ደረጃ “A” (አንደኛ ደረጃ) መሸጋገሩ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት እና በስሩ በሚገኙ ተቋማት ውስጥ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የጠቅላላ ጉባዔ አካላት ውስጥ ነጻ ተሳትፎ እንዲኖረው የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር፣ በዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ጥምረት (GANHRI) ውስጥ አባል ለመሆን፣ ድምጽ ለመስጠት እና የአመራር ቦታዎችን ለመያዝ ብቁ ያደርገዋል።
ኮሚሽኑ ለሁሉም አጋሮቹ እና ባለድርሻ አካላት አክብሮቱን እየገለጸ በተለይም ሕዝቡ ለኮሚሽኑ ለሰጠው አመኔታ እና ትብብር ምስጋናውን ያቀርባል። በመጨረሻም ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችን የማስፋፋት እና የማስጠበቅ ተልዕኮውን መወጣቱን እንደሚቀጥል በመግለጽ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪውን ያቀርባል።