የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል፣ በጅማ እና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞኖች እንዲሁም በጅማ ከተማ አስተዳደር በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ አተገባበር ላይ ባከናወናቸው የክትትል ሥራዎች፣ ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች ዙሪያ ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. የውትወታ መድረክ በጅማ ከተማ አካሂዷል። መድረኩ ኢሰመኮ ባከናወናቸው ክትትሎች የተለዩ መልካም ተሞክሮዎችን፣ ተግዳሮቶችን እና የተፈናቃዮች መብቶች የሚከበሩበትን ሁኔታ ለመገምገም እና ልምድ ልውውጥን ለማጎልበት ያለመ ነው።

በመድረኩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን፤ ከኦሮሚያ ፕሬዚደንት ጽሕፈት ቤት፣ ከኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ፣ ከክልሉ የዞንና የወረዳ ቡሳ ጎኖፋ ተወካዮች፤ ከመንግሥታዊ ተቋማት፣ ከሰብአዊ ድጋፍና ልማት አጋር ድርጅቶች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም የጅማ እና የምስራቅ ሐረርጌ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ በጅማ ከተማ ለበርካታ ዓመታት ሲኖሩ ለነበሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ፣ ቤት እና የመተዳደሪያ ድጋፎችን በመስጠት ተፈናቃዮች ወደ መደበኛ ኑሮ እንዲሸጋገሩ ማድረግን ጨምሮ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በመንግሥት ተቋማት፣ በአካባቢው ማኅበረሰቦች እና በአጋር ድርጅቶች ቅንጅታዊ ጥረት የተከናወኑ ሥራዎች በመልካም ተሞክሮነት ተነስተዋል። በሌላ በኩል በዞኑ ከመልሶ ማቋቋም፣ ከመሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት፣ ከመሠረተ ልማት እና ከማኅበራዊ ውህደት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመፍታት ሂደቱ በተሟላ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ማድረግ እንደሚገባ አጽንዖት ተሰጥቶታል።

በተጨማሪም በጅማ ከተማ አስተዳደር እና በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ላሉ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እና የተፈናቃዮችን መብቶች ለማስከበር ባለድርሻ አካላት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ሰብአዊ ክብርን ባማከለ ሁኔታ በቅንጅት ለመሥራት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።

በኢሰመኮ የትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ በካምፓላ ስምምነት እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርሖች እና መስፈርቶች መሠረት መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል። አክለውም ኢሰመኮ የተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በመከታተል፣ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸምን በመገምገም፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል ገልጸዋል።