የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ግንቦት 23 እና 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ክትትል እና ምርመራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ኢሰመኮ ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በአካባቢው በአካል በመገኘት ከዐይን እማኞች፣ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ባሰባሰባቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው “በተለምዶ ኦነግ ሸኔ” ታጣቂ ቡድን በፈጸመው ጥቃት የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላትና ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን፣ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን፣ የንብረት ውድመት እና ቃጠሎ መድረሱን ለማረጋገጥ ችሏል።   

ኢሰመኮ በምርመራ ሂደቱ እንዳረጋገጠው በአሰኮ ወረዳ ደለተ ጫፋ ቀበሌ አካባቢ ከግንቦት 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በመስተዋሉ የአካባቢው ሚሊሻዎችና የኦሮሚያ ጸረ ሽምቅ ውጊያ ፖሊስ አባላት በስፍራው በመሰማራታቸው “በተለምዶ ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን እና በተሰማሩ የጸጥታ አካላት መካከል ግጭት ተፈጥሯል። ግጭቱን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ላይ ታጣቂ ቡድኑ ባደረሰው ጥቃት ከአካባቢው መሸሽ ባልቻሉ ኃይሉ ንጉሴ እና ሰሙ አባይነህ በተባሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንዲሁም በአካባቢው ከብቶች በመጠበቅ ላይ የነበረ ባቶ ሰፈኖ የተባለ የእስልምና እምነት ተከታይ በአጠቃላይ የሦስት ሲቪል ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ ችሏል።  

በተጨማሪም ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ባልታወቁ ቤቶች ላይ ቃጠሎ መድረሱን፣ የጠለታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መቃጠሉን፤ ቢዮ ቡጡሌ የሼክ ሙስተፋ መስጅድ አጥር ላይ ጉዳት መድረሱን፣ በድለተ ጫፋ ጤና ጣቢያ፣ በነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶችና የንግድ መደብሮች ላይ በመደዳ ዘረፋ መፈጸሙን እንዲሁም ከ2,650 በላይ የሚገመቱ የአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ አረጋግጧል።

ኢሰመኮ በአርሲ ዞን በሽርካ፣ በአሰኮ፣ በአንቆሎ ዋቤ፣ ጉና እና መርቲ ወረዳዎች ላይ በታጣቂዎቹ ሲፈጸሙ የነበሩ ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ እና ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ በተለያዩ ጊዜያት ማሳሰቡ ይታወሳል። መንግሥት በአካባቢው ላይ በተደጋጋሚ መሰል ጥቃቶች እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መከሰት መቀጠላቸው አሳሳቢ መሆኑን ከግምት በማስገባት ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የጀመራቸውን ጥረቶች በማጠናከር በአስቸኳይ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሰማሩ እና ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ ነዋሪዎችን ወደ ተረጋጋ ሕይወት የመመለስ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በመንግሥትና በሌሎች አጋር አካላት በጥቃቶቹ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ የአስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች ኢሰመኮ ያሳስባል።  በሌላ በኩል ኢሰመኮ ጉዳዩን አስመልክቶ ዝርዝር የምርመራ ሪፖርት ይፋ የሚያደርግ መሆኑን እየገለጸ፤ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በአግባቡ ሳያረጋግጡ የሚሰነዘሩ ፍረጃዎችና ቅስቀሳዎች ተጨማሪ ግጭት እንዲፈጠር የማነሳሳት ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ ማናቸውም ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀርባል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ኢሰመኮ በዜጎች ላይ ለደረሰው ሞትና ጉዳት ማዘኑን ገልጸው በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አሳሳቢ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ አክለውም መንግሥት ሁኔታውን ለማረጋጋት እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ያከናወናቸው ተግባራት መቀጠል ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በማንኛውም ጊዜ የጸጥታ ሥጋት ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ በቂ የጸጥታ ኃይሎች በመመደብና ተመሳሳይ ጥቃቶችን የመከላከል ሥራ በመሥራት የነዋሪዎች በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት እና የንብረት መብቶች ለአደጋ እንዳይጋለጡ እንዲያደርግ፣ ተገቢውን ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እና ተጎጂዎችን ለመካስና ለማቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ እንዲሁም ሁሉም አካላት የተፈጠሩ ችግሮችን ከማውገዝ ባሻገር ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ መግለጫዎች እና ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል።