የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) በምስራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በመስፋፋት ላይ በመሆናቸውና ባሕሪያቸውን እየቀየሩ ብሔር ተኮር ወደ ሆነ የእርስ በእርስ ግጭት ሊያመራ የሚችል በመሆኑ፣ መንግስት በቂ የፀጥታ ኃይሎችን በአፋጣኝና በቋሚነት በአካባቢው ሊያሰማራ እንደሚገባ አሳሰበ።

ኮሚሽኑ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጊዳ ኪራሙ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ የምስራቅ ወለጋ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በአስጊ ሁኔታ እንደሚገኙ ገልጾ፣ ወደ ወረዳው የሚወስዱ የተዘጉ መንገዶችን ማስከፈትን ጨምሮ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌዴራሉ ኃይሎች ጋር ሊቀናጁ እንደሚገባ ማሳሰቡ ይታወሳል። ይሁንና የክልሉ የፀጥታ ኃላፊዎች ለኢሰመኮ እንደገለጹት በኪራሙ ወረዳ፣ ሀሮ ከተማ ላይ የነበረው “የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ለሌላ ስራ አካባቢውን ለቅቆ መውጣቱን” ተከትሎ፣ በሀሮ አዲስ አለም ቀበሌ ከመስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሲቪል ሰዎች “በኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡በዚሁ ከተማ ይህንኑ ግድያ ምክንያት በማድረግ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት የተደራጁ የተወሰኑ የአካባቢው እና አጎራባች ክልል ነዋሪዎች በሲቪል ሰዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የተጎጂዎች ቤተሰቦችና  የአካባቢው አስተዳደር  አካላት  ለኮሚሽኑ  ከሰጡት  መረጃ  መረዳት  ተችሏል፡፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በኡሙሩ ወረዳ ደግሞ ከነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም.  ጀምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች በሆኑና “እራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ” በሚል መሳሪያ እንዲታጠቁ ስለመደረጋቸው ወይም እንደተፈቀደላቸው በሚነገር የአካባቢው ነዋሪዎቸ በተፈጸሙ ጥቃቶች በተመሳሳይ በርካታ ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥቃቶችና ግድያዎች የብሔር ማንነትን መሰረት አድርገው አንድ ጊዜ በአማራ ብሔር ተወላጆች፣ ሌላ ጊዜ በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ብሔር ተኮር ጥቃቶች በመሆናቸው፣ በአካባቢው ነዋሪዎች በሆኑ በሁለቱ ብሔር ተወላጆች መካከል ከፍተኛ ውጥረትና የእርስ በእርስ ግጭት ስጋትን ፈጥሯል፡፡

ይህንኑ ግጭት በመሸሽ ከምስራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ፣ ጉደያ ቢላ ወረዳ፣ ኪረሙ ወረዳ፣ ሌቃ ዱለቻ ወረዳ፣ በዲጋ ወረዳ፣ እና ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በአጠቃላይ 43,139 በላይ ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ የዞኑ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡፡ በተጨማሪም ወደ እነዚህ አከባቢዎች የሚያደርሱ መንገዶች አሁንም ዝግ በመሆናቸውና በአከባቢው ያለው ውጥረት አሁንም ባለመርገቡ ምክንያት ሰዎች መሰረታዊ አቅርቦቶችንና ሕክምና ለማግኘት ጭምር በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ በተለይም የአካባቢውንም ሆነ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ስምሪት በተመለከተ  በተደጋጋሚ እየታየ ያለው አንዱ ችግር የፀጥታ አስከባሪዎች አንድ አካባቢን ለቅቀው መሄዳቸውን ተከትሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በመሆናቸው፤ የዚህን ችግር እጅግ አሳሳቢነት ኮሚሽኑ ከዚህ በፊትም ማሳወቁን አስታውሰው፣ “ግጭቱ ሙሉ በሙሉ ባሕሪውን በመቀየር ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳይለወጥ እና የአካባቢው ሰላምና ደህንነት ሙሉ በሙሉ እስከሚረጋገጥ ድረስ በቂ የፀጥታ ኃይሎች በተለይ ለግጭትና ጥቃት ተጋላጭ  የሆኑ አካባቢዎች ላይ በቋሚነት ተመድበው  መንግስት የሁሉንም ነዋሪዎች ደኅንነት የማስጠበቅና ከጥቃት መከላከል ግዴታና ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል፡፡  ዋና ኮሚሽነሩ አክለው፣  በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች  አፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ አሳስበዋል።