በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምሥራቅ ምድብ ችሎት የወንጀል ችሎት ዳኛ የሆኑት 1ኛ ዳኛ ደሳለኝ ለሚ፣ 2ኛ ዳኛ ሙሀመድ ጅማ እና 3ኛ ዳኛ አብዲሳ ዋቅጅራ ጥቅምት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚሠሩበት ፍርድ ቤት በአዳማ ከተማ ኦሮሚያ ፖሊስ ተወስደው መታሰራቸውን ተከትሎ፤ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እስራቱ ፈጽሞ ሕገወጥና በዳኝነት ነጻነት ላይ የተፈጸመ ጥቃት በመሆኑ በአስቸኳይ ከእስር ሊለቀቁና ድርጊቱ ተጣርቶ ተገቢው እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢሰመኮ ስለጉዳዩ ባደረገው ማጣራት ዳኞቹ በሕግ የተሰጣቸው ልዩ ጥበቃ መብት በሕጋዊ መንገድ ሳይነሳና ዳኞች መሆናቸው ሳይገለጽ ከወረዳ ፍርድ ቤት ተሰጥቷል በተባለ የእስር ትእዛዝ ከሥራ ገበታቸው ላይ ተነስተው የታሰሩ ሲሆን፤ የእስር ትእዛዙን የሰጠው የወረዳ ፍርድ ቤት ታሳሪዎቹ ዳኞች መሆናቸውን እንደተረዳ የእስር ትእዛዙን የሻረ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ሆኖም ዳኞቹ ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ወቅት ድረስ በእስር ላይ ናቸው፡፡ ስለሆነም ዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ዳኞቹ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ አጥብቀው አሳስበዋል፡፡