የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ አካባቢዎች በተከሰተ የፀጥታ መደፍረስ የተሳተፉ ሰዎችና ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ ያደረሷቸው ጥቃቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ባሕርያትን የሚያሟሉ መሆናቸውን በምርመራ ሪፖርቱ አመለከተ።
ኢሰመኮ ከሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩ ሦስት ተከታታይ ቀናት በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የባለሞያ ቡድኖቹን ወደ 40 የክልሉ አካባቢዎች የላከ ሲሆን፣ የምርመራውን ግኝቶች ታኅሣሥ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።
በ59 ገጽ ሪፖርቱ እንደተመለከተው፣ በዚህ መጠነ ሰፊ ጥቃት የተሳተፉት ብዙ ቁጥር ያላቸው እና ከቦታ ቦታ በቡድን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች ሲሆኑ፤ በጩቤ፣ በድንጋይ፣ በእሳት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ፣ በዱላ፣ በዶማ፣ በገጀራ እና በመጥረቢያ ተጠቅመው ሰዎችን ደብድበዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ ፍጹም ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በማሰቃየት እና በማረድ ጭምር ሰዎችን ገድለዋል። በጥቃቶቹ የ123 ሰዎች ሕይወት አልፏል፣ 500 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
በአብዛኛው በቡድን የተደራጁ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ፣ በብሔርና በሃይማኖታቸው ተለይተው የተመረጡ ሲቪል ሰዎችን፣ ቢያንስ በ40 የተለያዩ ቦታዎች በተስፋፋና ለሦስት ቀናት በቆየ ሁከት ማጥቃታቸው፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንደሚያደርገው የኮሚሽኑ ግኝቶች ያመላክታሉ።
ምንም እንኳን የፀጥታ ኃይሉ በየቦታው የገጠመውን መጠነ ሰፊ የፀጥታ መደፍረስ ችግር እና የፀጥታ አባሎቹንም የሕይወት መስዋዕትነት በሚጠይቅ ሁኔታ በመሰማራታቸው ኃላፊነታቸው እጅግ ፈታኝ የነበረ መሆኑን መገንዘብ ቢቻልም፤ በተወሰኑ ቦታዎች የኃይል አጠቃቀም ተመጣጣኝነት ከፍተኛ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል። በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ፣ ሰልፍ ውስጥ ያልነበሩ፥ በመንገድ ወይም በቤታቸው በር ላይ የተገደሉ፣ ለማሸማገል ጣልቃ የገቡ የአገር ሽማግሌዎችን እና የአዕምሮ ህመምተኛ ጭምር እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በኢትዮጵያ የሚታየው የግፍና የጭካኔ ወንጀሎች መደጋገም፣ የችግሩን ስር መሰረት ለመፍታት የሚያስችል የተሟላ ብሔራዊ የግፍና ጭካኔ ወንጀል መከላከያ ስትራቴጂ ነድፎ በአፋጣኝ በስራ ላይ ማዋል እንደሚገባ የሚያሳይ መሆኑን” ገልጸዋል።