Photo credit: Anna Dubuis/DFID
የሳምንቱ የሰብአዊ መብቶች ጽንሰ-ሀሳብ
የካቲት 7-11 2014 ዓ.ም
ውሃ የማግኘት ሰብአዊ መብት ማለት ለሁሉም ሰው በቂ፣ ደኅንነቱና ደረጃው የተጠበቀ፣ በአካል ተደራሽ የሆነ፣ ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ እና ለግል እና ለቤት አገልግሎት የሚውል ውሃን ማግኘት ማለት ነው፡፡ (ተ.መ.ድ)
ውሃ የማግኘት ሰብአዊ መብት ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ እውቅና የተሰጠውና በኢትዮጵያ ሕገ መንግስትም በማኅበራዊ ነክ ዓላማዎች ስር በግልጽ ተካቶ የሚገኝ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2030 ደኅንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ እና የንጽሕና አጠባበቅ አቅርቦትን ለሁሉም የማረጋገጥ እቅድ ይዛለች። (ዘላቂ የልማት ግብ 6)
የሀገራት ውሃ የማግኘት መብትን እውን የማድረግ ስኬት የሚለካው በውሃ መኖር፣ በተደራሽነቱ፣ በተመጣጣኝነቱ፣ በጥራቱና በደኅንነቱ ወይም ለጤና ጎጂ ካለመሆኑ አንጻር ነው፡፡ ውሃ እና የንጽሕና መጠበቂያ አገልግሎት የማግኘት መብት በቂ የሆነ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት አካል ነው፡፡ የዚህም መብት መረጋገጥ በሕይወት የመኖርና የጤና መብትን ጨምሮ ለሌሎች መብቶችን ተጠቃሚነት አስተዋጽዖ ያደርጋል።
የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን በአፍሪካ ውሃ የማግኘት ሰብአዊ መብትን ማስፋፋትና ማስከበርን በተመለከተ መመሪያ ያጸደቀ ሲሆን፣ መመሪያው ሀገራት ውሃ ማግኘት መብት መሆኑን መሰረት ያደረገ የውሃ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት እንዳለባቸው ይገልጻል።