የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያቋቋሙት የኢሰመኮ-ሲቪል ማኅበራት የትብብር መድረክ ዘንድሮ “ሰብአዊ መብቶች የዕለት ተዕለት ፍላጎቶቻችን ናቸው” (Human Rights: Our Everyday Essentials) በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን ዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶች ቀን ታኅሣሥ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በኢሰመኮ ዋና መሥሪያ ቤት አክብሯል።

የምስራች ለገሰ፣ የኢሰመኮ የፕሮግራምና አጋርነት ሥራ ክፍል ዳይሬክተር

መርኃ ግብሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ የጸደቀበትን 76ተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ሰላም ለሰብአዊ መብቶች መከበር እንዲሁም ለሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ፍላጎቶችና እንቅስቃሴዎች መሠረት መሆኑን በማስታወስ ባለድርሻ አካላት ለሰላም፣ ሰብአዊ ክብር እና ፍትሕ በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ ለማስተላለፍ ያለመ ነው።

በመርኃ ግብሩ የኢሰመኮ፣ የትብብር መድረኩ አባል የሆኑ ሲቪል ማኅበራት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የምርጫ ቦርድ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም የአጋር ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በዝግጅቱ የኢሰመኮ እና ሲቪል ማኅበራት የትብብር መድረክ ተወካዮች የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን የሚከበርበትን መሪ ቃል ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር የሰላም እና ሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነትን በሚመለከት የጋራ መልእክት በቪዲዮ ያስተላለፉ ሲሆን ፍትሕ፣ ሰላምና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በጋራ ለመሥራት ጥሪ ቀርቧል። የቪድዮው መልእክትም በኢሰመኮ እና በትብብር መድረኩ አመራሮች እና አባል ሲቪል ማኅበራት ድረ ገጾች እና የተለያዩ ማኅበራዊ ትሥስር ገጾች በተመሳሳይ ሰዓት ተደራሽ ተደርጓል። ከጋራ መልእክቱ በተጨማሪ በዝግጅቱ ላይ ስለሰብአዊ መብቶችና ሰላም አስፈላጊነት የሚገልጹ የሥነ-ጥበብ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን ዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶች ቀን መሪ ቃል ማእከል ያደረገ ውይይት ተካሂዷል። በተጨማሪም በኢሰመኮ 5ተኛው ዙር የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ላይ ለውድድር የቀረቡ ፎቶግራፎች በዐውደ ርዕይ መልክ ቀርበዋል።

የኢሰመኮ የፕሮግራምና አጋርነት ሥራ ክፍል ዳይሬክተር የምስራች ለገሰ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን በትብብር መድረኩ ሲከበር ሰላም ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ሰብአዊ መብቶችም ለሰው ልጆች ህልውና፣ ክብር፣ ፍትሕና ደኅንነት ያላቸውን የማይተካ ሚና ዕውቅና በመስጠት በባለድርሻ አካላት መካከል የጋራ ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።