የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) “የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጥበቃ” አስመልክቶ ከመንግስት ተቋማት፣ ከሀገራዊ እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ባለሞያዎች ጋር አውደ ጥናት አዘጋጅቷል። ከየካቲት 17 እስክ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አባባ በተካሄደው ስብሰባ ከተሳተፉ መንግስታዊ ባለድርሻ አካላት ጋር የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መብቶች ለማስጠበቅ እና ለማስከበር የሚረዳ የሕግ ማዕቀፍን ለመቅረጽ፣ ለመተግበር፣ እንዲሁም ተቋማዊ መዋቅሮች እና ቅንጅታዊ አሰራሮች ሊዘረጉ ስለሚቻልባቸው ሁኔታዎች ውይይት ተደርጓል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በመድረኩ እንደገለጹት “ዜጎች በቅድመ መፈናቀል፣ በመፈናቀል እና በድኅረ-መፈናቀል ወቅት መብቶቻቸው እንዳይጣሱ መጠበቅ እና ተጥሰው ሲገኙ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ የተቀናጁ አሰራሮችን መዘርጋት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
ለሁለት ቀናት የተካሄደው ስብሰባ በጥር ወር 2014 ዓ.ም. በተለይም ከመንግስታዊ ተቋማት ጋር ከተደረገው ስብሰባ የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህ ሁለተኛ ዙር ስብሰባ ከተለያዩ ሀገራት ልምድ በመነሳት በአንድ በኩል የሀገር ውስጥ መፈናቀልን ለማስተዳደር የሚያስችል የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፍ መቅረጽ፣ በሌላ በኩል መፈናቀልን መከላከል፣ ለተፈናቃዮች አስፈላጊውን ጥበቃና ሰብአዊ እርዳታ ማቅረብ አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል። ዝግጅቱ በዚህ እና ተፈናቃዮችን መመለስ፣ ማቋቋም እና ከህብረተሰቡ ጋር ማቀላቀልን በተመለከተ የተቋማት ሥልጣንና ኃላፊነት በግልጽ ለማስቀመጥ እና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር የሚያስችል ተመሳሳይ አረዳድ ለመፍጠር ያቀደ ነበር።
በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ጉዳይ ሰፊ ልምድ ያላቸው የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ልዩ ዘጋቢ (Special Rapporteur) ፕሮፌሰር ቻሎካ በያኒ፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (International Committee of the Red Cross) የመጡት አንጄሊክ ሳር በስብሰባው ተገኝተዋል። ሁለቱ ከፍተኛ ባለሞያዎች ኢሰመኮ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ እየሰራ ያለውን ስራ አድንቀው፣ በስብሰባው ላይ የተፈናቃዮችን መብቶች የሚያስጠብቅ የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት፣ የመንግስታዊ ተቋማት አወቃቀርንና ቅንጅትን ለማጠናከር የሚያግዙ በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ የጸደቁ የስብአዊ መብቶች ስምምነቶችን፣ መልካም ተሞክሮዎችን እና አሰራሮችን አካፍለዋል።
ኢሰመኮ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን ለማረጋገጥ ከሚያከናውናቸው ዋነኛዎቹ እና መደበኛ ተግባራት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል ማድረግ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀልን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እና ተቋማዊ መዋቅር እንዲዘጋጅ የውትወታ ስራዎችን ማከናወን ናቸው። ከዚህ ጋር በተገናኘ ኮሚሽኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንዲሁም በተናጠል በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች፣ በካምፖች እና በግዜያዊ መጠለያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ በርካታ የክትትል ስራዎች ሰርቷል፡፡