የባለሞያ አስተያየት ከኢሰመኮ
ትዝታ ታደሰ
ከፍተኛ የሕግ ባለሞያ
የሕግ እና የፖሊሲ ሥራ ክፍል
የብሮድካስት አገልግሎት ከሌሎች የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በተለየ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአንድ ሀገር የተመደበውን ውስን ሞገድ የሚጠቀም በመሆኑ፤ ከሌሎች ምክንያቶች በተጨማሪ ይህን ውስን ሃብት ብሎም ዘርፉን የሚያስተዳድር የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ያስፈልጋል፡፡ ነፃነቱ የተጠበቀ ተቋም ማደራጀት፣ ግልጽና ገለልተኛ የፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ሥርዓት መዘርጋት፣ ባለቤትነትንና ብዝኃነትን መወሰን፣ የይዘት ክትትል ሥርዓትን መደንገግ፣ የፕሮግራም ደረጃ ማስቀመጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙና በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚሸፈኑ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡
የማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ መብት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች ላይ ጥበቃ ተደርጎለታል፡፡ ይህ መብት በሕግ የተመለከቱ ገደቦች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ሃይማኖቱን/እምነቱን በይፋ የማምለክ፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብቶችን ያጠቃልላል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት የብሮድካስት ድርጅት ባለቤትነት ላይ አጠቃላይ ክልከላ የሚያስቀምጡ ሀገራት (ለምሳሌ ናይጄሪያ እና ቱርክ) ቢኖሩም፤ በተወሰኑ የማሰራጫ መንገዶች ላይ ብቻ የብሮድካስት ፈቃድ እንዲያገኙ የሚፈቅዱም ሀገራት (ለምሳሌ እንግሊዝ) አሉ። ለዚህ ክልከላ ወይም ገደብ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ውስን የሆነውን ሞገድ በአግባቡ ለማዳረስ እና የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላም እና ብሔራዊ መግባባትን ለማስጠበቅ የሚሉት ይገኙበታል ፡፡
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 የሃይማኖት ተቋማት በተፈቀዱ የብሮድካስት ማሰራጫ መንገዶች ላይ ፈቃድ እንዲያገኙ ይደነግጋል፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንም ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ በማርቀቅ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የሃይማኖት ብዝኃነትና ይህን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች በሚከሰቱባቸውት ሀገራት ውስጥ ለሃይማኖት ተቋማት የሚሰጥ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የሰዎችን ሰብአዊ መብቶች ስጋት ላይ የሚጥል እንዳይሆን በጥንቃቄ ሊመራና ግልጽ መስፈርቶችንና ሂደቶችን የያዘ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል፡፡
የሕግ ማዕቀፍ ከመዘርጋት ባሻገር የፈቃድ አሰጣጥ፣ የይዘት ክትትል፣ የተከለከሉ ተግባራትንና ሌሎች በሕጉ የተደነገጉ ዝርዝር ጉዳዮችን ተግባራዊ በማድረግ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥም ይገባል፡፡ ለምሳሌ በናይጄሪያ ምንም እንኳን ለሃይማኖት ተቋማት የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ መስጠት የተከለከለ ቢሆንም፣ የሃይማኖት ድርጅቶች ፈቃድ ባላቸው የብሮድካስት ጣቢያዎች በሚያስተላልፉት ማስታወቂያ እና የሃይማኖት ፕሮግራም የብሮድካስት ዘርፉን ለውድድርና የበላይነት ለማግኘት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የሃይማኖት ይዘት ያለው ማስታወቂያ አለመከልከሉና በሕጉ ላይ የተቀመጠውም መስፈርት ለትርጉም የተጋለጠ በመሆኑ እንደሆነ ይገለጻል፡፡
የብሮድካስት ፈቃድ ለማግኘት ብቁ የሚያደርጉ ከሃይማኖት ተቋሙ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችና መሰረታዊ መስፈርቶችን በሕግ ማዕቀፉ መደንገግ የመጀመሪያው ነው። ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የማኅበረሰብ ብሮድካስት ፈቃድ አሰጣጥ ደንብ መሰረት የሚያመለክቱ ሰዎች ማመልከቻ ከማስገባታቸው በፊት ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ማኅበረሰቡን ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ማስረዳት፣ የፋይናንስ ምንጫቸውን፣ የፕሮግራም እቅድ እና ሌሎችን መስፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። በአውስትራሊያም ፈቃድ ለማውጣት ያመለከቱበትን ማኅበረሰብ ፍላጎት የሚወክሉ መሆኑን ማሳየት አለባቸው፡፡
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ላይ ለሃይማኖት ተቋማት የተፈቀደው የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ አይነት በግልጽ ያልተደነገገ በመሆኑ፣ ይህን አዋጅ ተከትሎ በሚወጣው የፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ ላይ በግልጽ መደንገግ ይኖርበታል፡፡
በሃይማኖት ተቋማት ባለቤትነት የተያዘ የብሮድካስት ድርጅት ከመንግሥትና ከግል ዘርፉ፣ እንዲሁም ከሌሎች ተዋንያን ተጽዕኖ ነጻ ሊሆንም ይገባል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት የብሮድካስት ድርጅቶች ምንም እንኳን ለትርፍ ያልተቋቋሙ ቢሆኑም፣ በብሮድካስት አገልግሎቱ የሚያገኙት ገቢ በሚኖር ጊዜ ገቢውን እንዴት ሊጠቀሙት እንደሚገባ መደንገግ ያስፈልጋል። በአንዳንድ ሀገራት የማኅበረሰብ ብሮድካስት አገልግሎት የሚያገኘውን ገቢ ድርጅቱ ለተቋቋመለት ማኅበረሰብ ጥቅም ብቻ ሊያውለው የሚችል ሲሆን (ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካ ብሮድካስት ሕግ፣ አንቀጽ 35(2))፣ በሌሎች ደግሞ በብሮድካስት አገልግሎቱ ላይ ብቻ የሚውል እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ለሃይማኖት ተቋም የሚሰጠው የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ አይነት በማኅበረሰብ ብሮድካስት አገልግሎት ስር ሊሸፈን ስለመቻሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውንም የአንዳንድ ሀገራት ልምድ መሰረት በማድረግ፤ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ አሰራር ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ወደፊት በሚወጣው መመሪያ በዚህ መሰረት የሚፈጸም ከሆነ፤ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ወይም ከብሮድካስት አገልግሎቱ የሚገኘው ገቢ ለማሰራጫ ጣቢያው አገልግሎት ብቻ ሊውል እንደሚገባ በግልጽ ሊደነገግ ይገባል፡፡
ሌላው ዋነኛው ጉዳይ የይዘት ክትትል ነው፡፡ ማንኛውም የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪ ባለፈቃድ በፕሮግራሙ በሕግ የተከለከሉ ይዘቶችን ከማስተላለፍ መቆጠብ አለበት፡፡ ብሔርን ወይም ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ፣ ሃሰተኛ መረጃ ወይም የግጭት አነሳሽ ንግግሮች እንዳይሆኑና በአጠቃላይ የሚድያና ተያያዥ የሆኑ ሕጎችን የሚጥሱ ይዘቶችን ማስተላለፍ የሚከለክል መሆን አለበት፡፡
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 70 ላይ እንደተደነገገው፣ ማንኛውም የብሮድካስት አገልግሎት ባለፈቃድ በሚያሰራጨው ሃይማኖት ተኮር ፕሮግራም ለሁሉም ሃይማኖቶችና እምነቶች ተገቢ ክብር እንደተሰጣቸው ማረጋገጥ አለበት፡፡ የሃይማኖትና የእምነት ነፃነትንና መሰረታዊ ሰብአዊ መብትን ሊጠብቅም ይገባል፡፡ ስለሆነም ለሃይማኖት ተቋማት የብሮድካስት ፈቃድ አሰጣጥ የሚወጣው ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ እነዚህን ግዴታዎች ያካተተና ተጠያቂነትንም በዚሁ አግባብ የሚያረጋግጥ ሊሆን ይገባል፡፡
ከይዘት ክትትል ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ ማስታወቂያ ሲሆን፣ በሌሎች ሕጎች ያልተከለከለ ይዘት ያለው ማስታወቂያ መሆኑን፣ ታማኝ የሆነ፣ ተመልካቹን የማይጎዳ፣ የማያሳስት እና ተገቢ በሆነው የአየር ሰዓት ማስተላለፍ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ሃይማኖትን የተመለከቱ ማስታወቂያዎችም የፕሮግራሙን ተከታዮች የማያሳስቱ፣ በሌሎች ሃይማኖቶች ላይ የጥላቻ ይዘት ያለው መልዕክት የማያቀርቡ፣ የሚተዋወቀው ሃይማኖት ተከታይ እንዲሆን የማያስገደዱ ወይም ገንዘብ ማግኘትን መሰረት ያደረገ ቃል መግባትን የሚያስወገዱ መሆን የሚሉት መስፈርቶች በግልጽ ሊደነገጉ ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ናቸው። የይዘት ክትትልን በተገቢው ለመተግበር በቅድሚያ መሰረታዊ የይዘት ደረጃዎችን በግልጽና በዝርዝር መደንገግ፣ የቅሬታ ማቅረቢያ መንገድ መዘርጋት፣ አፈጻጸሙን የሚከታተል አካል ማቋቋም አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች በመሆናቸው በሕግ ማዕቀፉ ሊካተቱ ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሊያሰራጩት ስለሚችሉት የዜና ሽፋን፣ ሊያካትቱት ስለሚገባቸው የፕሮግራም አይነቶች፣ የፖለቲካ ይዘት፣ ከሌሎች ብሮድካስት ማሰራጫዎች የተገኙ ይዘቶችን መልሶ ስለማሰራጨት፣ በንግድ የብሮድካስት አገልግሎት ባለፈቃዶች እንዲሰራጩ የተፈቀዱ ይዘቶችን ስለማሰራጨት፣ ቅድሚያ ሰጥተው ወይም በቂ የአየር ሰዓት ሊመድቡለት ስለሚገባው ይዘት ላይ ልዩ ገደብ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ በግልጽ መደንገግ እንደሚያስፈልግም ይታመናል፡፡