ማብራሪያ
የመሬት ይዞታን ለልማት/ለሕዝብ ጥቅም/ ማስለቀቅ እና የሰብአዊ መብቶች መርሆች
- መንግሥት ለልማት የመሬት ይዞታን ሊወስድ ይችላል?
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘላቂ ልማት የማግኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብት አላቸው። መንግሥት የዜጎችን የልማት መብት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባሮችን የመፈጸም ግዴታ አለበት። ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ከሚያስፈልጉት ግብዓቶች መካከል አንዱ መሬት ነው። የልማት ሥራ የሚከናወንበትን መሬት ለማግኘት መንግሥታት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የግለሰቦችን ይዞታ ለሕዝብ ጥቅም ብሎ በማስለቀቅ ነው። ሆኖም በሕዝብ ጥቅም እና በግለሰብ ባለይዞታዎች ጥቅም መካከል ሚዛን ለመጠበቅ ሲባል፣ የሰዎችን የግል ይዞታ የመውሰድ ተግባር በሚከናወንበት ጊዜ መንግሥት የሰዎችን ሰብአዊ መብቶች በማይጥስ እና አግባብ ባላቸው የሕግ ማዕቀፎች ላይ የሰፈሩ ቅድመ-ሁኔታዎችን ባሟላ እና የሥነ-ሥርዓት ሂደቶችን በተከተለ መልኩ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት።
2. ይዞታን በማስለቀቅ ሂደት አግባብነት ያላቸው የሰብአዊ መብቶች ገደቦች ምንድን ናቸው?
ይዞታን በማስለቀቅ ሂደት የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሊከሰቱ የሚችሉ ቢሆንም በቀጥታ ደግሞ የንብረት መብት እና የመኖሪያ ቤት መብትን ይጋፋሉ። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 40 በግልጽ ለንብረት መብት ዕውቅና ይሰጣል። በተጨማሪም በአንቀጽ 90(1) ላይ የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚደረግ አስቀምጧል። ከሕገ-መንግሥቱ በተጨማሪ የንብረት እና የመኖሪያ ቤት መብቶች ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች ዕውቅና አግኝተዋል፡፡
ለምሳሌ የመኖሪያ ቤት መብት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 25(1)፣ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 11(1)፣ በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 17፣ በዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 27(3)፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ማናቸውንም ዓይነት መድልዎ ለማስወገድ የወጣው ስምምነት አንቀጽ 14(2(ሸ))፣ በአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት አንቀጽ 28(1) እና ሁሉንም ዓይነት የዘር መድልዎ ለማስወገድ የተደረገ ዓለም አቀፍ ስምምነት አንቀጽ 5(ሠ(iii)) ላይ ዕውቅና አግኝቷል።
በተጨማሪም መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት በአፍሪካ ቻርተር በግልጽ ባይደነገግም በቻርተሩ አንቀጽ 14፣ 16 እና 18(1) ጣምራ ንባብ መሠረት ጥበቃ የተደረገለት መብት መሆኑን የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ባስተናገደው አቤቱታ (ኮሙኒኬሽን) ቁ. 155/96 ላይ ትርጉም (ማብራሪያ) ሰጥቶበታል፡፡ የተ.መ.ድ የኢኮኖሚ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ኮሚቴ በሰጠው አጠቃላይ አስተያየት ቁ. 4 መሠረት በቂ የሆነ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ይዘቶች መካከል ለይዞታ ሕጋዊ ጥበቃ መስጠትና በኃይል ይዞታን ከማስለቀቅ የሕግ ጥበቃ የማግኘት መብትንም ያካትታል፡፡ የንብረት መብትም በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 17፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ማናቸውንም ዓይነት መድልዎ ለማስወገድ የወጣው ስምምነት አንቀጽ 15(2) እና 16(1(ሸ))፣ በአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት አንቀጽ 12(5)፣ ሁሉንም ዓይነት የዘር መድልዎ ለማስወገድ የተደረገ ዓለም አቀፍ ስምምነት አንቀጽ 5(መ(v)) እና በአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 14 ላይ ዕውቅና አግኝቷል።
በዚህም መሠረት የንብረት መብት በራሱ ሦስት የተለያዩ ግን የተዛመዱ መሠረታዊ መብቶችን ያቀፈ ነው። አንደኛው፡- ንብረትን በዘፈቀደ ያለመነጠቀ ነጻነት ሲሆን ይህ መብት የጥበቃውን መጠን እና ገደቡንም የሚገልጽ ነው። የንብረት መብት በዘፈቀደ ንብረትን ያለመነጠቅ ነጻነትን ቢያጎናጽፍም በሕግ አግባብ፣ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ እና ተገቢው ካሳ ተከፍሎ ንብረቱ ሊወሰድ የሚችልበትን የንብረት መብት ገደብንም ያካተተ ነው። ሁለተኛው፡- የንብረት ዝርዝር መብቶችን ማለትም በመጠቀም፣ ፍሬውን በመሰብሰብ (አከራይቶም ሆነ የብድር ማሲያዢያ ዋስትና በማድረግ) እና በማስተላለፍ (በኪራይ፣ በስጦታ፣ በውርስም ሆነ በመሸጥ) ሂደት አላግባብ ከሆነ ቁጥጥር እና ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆን ነው። ይህ ሲባል ግን አግባብ የሆነ፣ በሕግ የተደነገገ፣ ቅቡልነት ያለው ዓላማን ለማሳካት የሚያስፈልግ እና ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ አስፈላጊ የሆነን ቁጥጥር እና ጣልቃ ገብነትን የሚያግድ አይደለም። ሦስተኛው የንብረት መብት መገለጫ ንብረትን በሰላም እና ያለፍርሀት መጠቀም ነው። ይህ መብት ለባለመብቶች በሕግ ላይ ከተቀመጠው ገደብ እና አግባብ ውጪ ንብረታቸውን እንደማያጡ እና መንግሥትም ሆነ ማንኛውም አካል ቁጥጥር እንደማያደርግባቸውና ጣልቃ የማይገባባቸው መሆኑን በማረጋገጥ ንብረታቸው ላይ ያላቸውን መተማመንን የሚያጎለበት ነው።
መንግሥት እነዚህን መብቶች የማክበር እና የማስከበር ግዴታ ያለበት ሲሆን ሰዎችን ከቤታቸው እና ከመሬታቸው በኃይል እንዳይፈናቀሉ ማድረግ፣ የይዞታ ዋስትናቸውን መጠበቅ እና የሚሠራው የልማት ሥራ ከፍ ያለ የማኅበራዊ ፍትሕ ዓላማ ለማሳካት ወይም ወደ ተሻለ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የሚወስድ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል (ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ውሳኔ)። ይሁን እንጂ የንብረት እና የመኖሪያ ቤት መብቶች ፍጹም ባለመሆናቸው ሊገደቡ የሚችሉ ሲሆን፤ በመብቶች ላይ ገደብ በሚጣልበት ጊዜ መሠረታዊ የሕግ እና የሰብአዊ መብቶች መርሆችን ባከበረ መልኩ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። እነዚህም መብቶችን ለመገደብ የሚያስችል የሕግ መሠረት (legality)፣ የገደብ እርምጃው የሚያሳካው ቅቡል ዓላማ (legitimacy)፣ ዓላማውን ለማሳካት የገደቡ አስፈላጊነት (necessity) እና የተመጣጣኝነት (proportionality) መርሆዎች ናቸው።
3. ይዞታ ለልማት ተብሎ የሚወሰድበት የሕግ አግባብ እና የሰብአዊ መብቶች መርሆች ምንድን ናቸው?
ይዞታ በመንግሥት ሊወሰድ የሚችለው ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ ተገቢው ካሳ ተከፍሎ እና በሕግ ላይ የሰፈሩትን የሥነ-ሥርዓት ሂደቶችን በተከተለ መልኩ ብቻ ነው። የሕዝብ ጥቅም ሲባል ይዞታ የሚወሰድበት የልማት ሥራ ግለሰቦችን የሚጠቅም ሳይሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ማኅበረሰብን የሚጠቅም ሲሆን ነው። በቀጥታ ሲባል ማኅበረሰቡ የሚሠራውን የልማት ሥራ እንደመብት መጠቀም የሚችልበት ሲሆን፤ ለምሳሌ ለትምህርት ቤት፣ ለሆስፒታል፣ ለመንገድ፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለሰላምና ደኅንነት ጥበቃ ወዘተ የሚሠሩ ግንባታዎች የሚውል ሲሆን ነው። በተዘዋዋሪ ሲባል ይዞታው የሚወሰድለት ፕሮጀክት መሬቱን የበለጠ ውጤታማ እና ምርታማ የሚያደርግ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እና ለመንግሥት የተሻለ የግብር ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን ነው። (የዚህ ቅድመ ሁኔታ ዋና ዓላማም የመንግሥትን በግለሰቦች ይዞታ ላይ የመወሰን ሥልጣንን መገደብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 40(8) እንደተገለጸው ለባለመብቱ ተመጣጣኝ ካሳ በቅድሚያ መክፈል ያስፈልጋል።
የተ.መ.ድ. ልማትን መሠረት አድርጎ ለሚደረግ ይዞታን ስለማስለቀቅ ባወጣው መሠረታዊ መርሆች መመሪያ መንግሥት ይዞታን ከማስለቀቁ በፊት፣ በማስለቀቅ ጊዜ እና ከማስለቀቅ በኋላ ሊያሟላ የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ዘርዝሯል፡፡
በቅድመ ማስለቀቅ ወቅት፡- የማስለቀቅ ውሳኔን ቀድሞ ማሳወቅ፣ በቂ የማስጠንቀቂያ ጊዜ መስጠት፣ ከማስለቀቅ አስቀድሞ የሕዝብና የተጎጂዎችን ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ በሂደቱ ቅር የተሰኘ ባለይዞታ ቅሬታውን የሚያቀርብበትና ዳኝነት የሚጠይቅበት ገለልተኛ እና ነጻ የሆነ አስተዳደራዊና የዳኝነት ሥርዓት መዘርጋት በዋናነት መሟላት እንዳለባቸው ያስቀምጣል። እንዲሁም ይዞታቸውን የሚለቁ ሰዎች ለንብረታቸው በቂ የሆነ ካሳ የማግኘት መብታቸውም ሊረጋገጥ ይገባል፡፡
የካሳው መጠን እና ዓይነት በተቻለ መጠን አጠቃላይ በማስለቀቅ ሂደት ውስጥ የደረሰን ጉዳት የሚክስ እና ዓይነቱም የተነሺውን ፍላጎት ያማከለ እንዲሆን ይመከራል። በኢትዮጵያ ሕግ የከተማ፣ የገጠር ወይም ከገጠር ወደ ከተማ የተካለሉ ይዞታዎች ሲወሰዱ እንዲሁም ይዞታው በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት ሲወሰድ የሚከፈለው የካሳ መጠንና ዓይነት እና ካሳው የሚሰላበት መንገድ ይለያያል።
መንግሥት የሰዎችን ይዞታ ለልማት ለማስለቀቅ መከተል ያለበት ሥርዓትን በተመለከተ አዋጅ ቁጥር 1161/2011 በግልጽ አስቀምጧል። ይህ አዋጅ እንደሚያሳየው ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ይዞታ እንዲለቀቅ ሲደረግ አሠራሩ ግልጽ፣ አሳታፊ፣ ፍትሐዊ እና ተጠያቂነትን የተከተለ መሆን ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም የዚሁ አዋጅ አንቀጽ 8 መንግሥት መሬት በሚያስለቅቅበት ጊዜ ከብዙዎቹ መካከል የሚከተሉት ሂደቶች መፈጸም እንዳለባቸው ያሳያል።
- አስቸኳይ የልማት ሥራ ካልሆነ ተነሺዎች ከመነሳታቸው ቢያንስ ከአንድ ዓመት በፊት ስለልማቱ በማወያየት ማሳወቅ፤
- ለተነሺ የካሳ መጠን እና ዓይነት በመግለጽ በጽሑፍ የማስለቀቂያ ትዕዛዝ መስጠት፤
- ተነሺ ትዕዛዙ በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ ካሳ እና ምትክ ቦታ ወይም ቤት መውሰድ፤
- ተነሺ ካሳና ምትክ ቦታ ከተቀበለ ቀን ጀምሮ ከ120 ቀናት ያልበለጠ የመልቀቂያ የጊዜ ገደብ መስጠት፤
- በሚለቀቀው መሬት ላይ ቋሚ ንብረት ከሌለ ተነሺ ካሳ ከተከፈለው በኋላ በ30 ቀናት ውስጥ ይዞታውን ማስረከብ ናቸው።
ይዞታን በማስለቀቅ ሂደት፡- መንግሥት እና ገለልተኛ የሆኑ አካላት ማስለቀቁ በሚከናወንበት ጊዜ በቦታው ላይ መገኘት፣ ማስለቀቅን የሚያከናውነው የመንግሥት አካል በሚመለከተው አካል የተሰጠ አግባብነት ያለው ፈቃድ መኖሩን ማሳየት፣ የማስለቀቅ ሂደቱ የሰዎችን ሰብአዊ ክብር፣ ደኅንነታቸውን እና በሕይወት የመኖር መብታቸውን የማይጥስ መሆን እንዳለበት ዓለም አቀፍ መርሆቹ ያሳያሉ፡፡ መንግሥት በዚህ ሂደት በተለይ ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡ የማስለቀቁ ሂደት በበዓላት ቀን፣ በምሽት፣ አመቺ ባልሆነ የአየር ሁኔታ መከናወን እንደሌለበት የተ.መ.ድ የኢኮኖሚ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ኮሚቴ በሰጠው አጠቃላይ አስተያየት ቁ. 7 ላይም ተጠቅሷል፡፡
ከማስለቀቅ በኋላ፡- የማስለቀቅ ሂደቱ እንደተከናወነ መንግሥት ይዞታቸውን ለለቀቁ በተለይም ራሳቸውን ለማቋቋም ላልቻሉ ሰዎች አስፈላጊ ምግብ፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ፣ የንጽሕና አገልግሎቶች፣ መሠረታዊ መጠለያ እና ቤት፣ ተገቢ የሕክምና አቅርቦት እና ለሕፃናት ትምህርትን ማቅረብ አለበት፡፡ በኢትዮጵያም የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 44(1) እንደሚያሳየው መንግሥት በሚያካሂዳቸው ፕሮግራሞች ምክንያት ሰዎች ሲፈናቀሉ ወይም ኑሯቸው ሲነካባቸው አስቀድሞ ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ወይም ሌላ አማራጭ ማካካሻ መስጠት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት በቂ እርዳታ በማድረግ ሰዎችን ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር አለበት።
መንግሥት በሕግ የተቀመጡ የሥነ-ሥርዓት ሂደቶችን ሳይከተል፣ የሕዝብ ጥቅም ላልሆነ ተግባር፣ ተገቢ ካሳ ሳይከፈል ወይም የተወሰደው ይዞታ በተባለለት ጊዜ ለተባለለት ዓላማ ጥቅም ላይ ካልዋለ ተነሺው አቤቱታውን በቅደም ተከተል ለዚሁ ዓላማ ለተቋቋሙት አስተዳደራዊ አካላት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ተነሺው በቅድሚያ ጉዳዩን ለአቤቱታ ሰሚ አካል ካቀረበ በኋላ በውሳኔው ካልተስማማ ቅሬታውን ለይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ማቅረብ ይችላል። በይግባኝ ሰሚው ጉባኤ ውሳኔ ቅር የተሰኘ ተነሺ ጉዳዩን በይግባኝ ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት እንዲታይለት መውሰድ ይችላል።
4. ከላይ የተጠቀሱት ይዞታን የማስለቀቅ ሂደቶች አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ ለተያዙ ይዞታዎች ተፈጻሚ ይሆናል?
በመሠረቱ ከላይ የሰፈሩት ይዞታን የማስለቀቅ መሠረታዊ እና ሥነ-ሥርዓታዊ ጥበቃዎች ታሳቢ ያረጉት መደበኛና ሕጋዊ ይዞታዎችን ነው። ሆኖም ኢመደበኛ ይዞታዎችንም ጭምር የማስለቀቅ ሂደት በዘፈቀደ ሳይሆን ሕጋዊ አሠራርን የሚከተል እና መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብር መሆን አለበት፡፡
ኢመደበኛ ይዞታዎች እንደየነገሩ ሁኔታ እየታየ የከተሞችን ፕላን እና ሽንሻኖ ስታንዳርድን የተከተሉ ከሆነ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች በሚያወጧቸው ደንቦች በሚወሰነው አግባብ ወደ መደበኛ ይዞታ ሊለወጡ እንደሚችሉ የከተማ መሬት ሊዝ አዋጅ 721/2004 አንቀጽ 6(4) ይደነግጋል። ሆኖም ይሄም ሂደት አዋጁ በወጣ በአራት ዓመታት ውስጥ ብቻ ተፈጻሚ እንደሚሆን በአንቀጽ 6(5) ላይ ተደንግጓል።
ከዚህ ውጪ ከሆነ እና ይዞታውን ለሕዝብ ጥቅም የተፈለገ ከሆነ በቦታው ላይ የሰፈረ ንብረት ካለ ለንብረቱ ካሳ መክፈል ሳያስፈልግ ለ30 ቀናት የሚቆይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ወይም በቦታው በሰፈረው ንብረት ላይ በመለጠፍ ብቻ እንዲለቀቅ ማድረግ እንደሚቻል የአዋጅ ቁጥር 1161/2011 አንቀጽ 8(8) ይደነግጋል።
5. መንግሥት በኃይል ማፈናቀል ፈጽሟል የሚባለው መቼ ነው?
ቅድመ ማስለቀቅ፣ በማስለቀቅ ወቅት እንዲሁም ድኅረ ማስለቀቅ ጊዜ መንግሥት ሊያሟላ የሚገባቸው የሰብአዊ መብቶች መርሆችን ያልተከተለ ሲሆን በኃይል ማፈናቀል እንደተፈጸመ ይቆጠራል፡፡ ይዞታ የማስለቀቅ ተግባር በአጠቃላይ ሰዎችን ቤት አልባ እንዲሆኑ እና ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ ማድረግ የለበትም፡፡ (የተ.መ.ድ የኢኮኖሚ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ አስተያት ቁ. 7)፡፡