የመንቀሳቀስ ነጻነት ምንድነው?

የመንቀሳቀስ ነጻነት በዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ (Universal Declaration of Human Rights)፣ በሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን (International Covenant on Civil and Political Rights)፣ በአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር (African Charter on Human and Peoples’ Rights) እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጥበቃ የተደረገለት ሰብአዊ መብት ነው። በውስጡም በአንድ ሀገር ውስጥ በመረጡት አካባቢ የመዘዋወር እና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት ነጻነትን፣ የራስን ጨምሮ ከማንኛውም ሀገር የመውጣት ነጻነትን፣ እንዲሁም ወደ ራስ ሀገር የመግባት (entry to one’s own country) ነጻነትን ያካትታል።

የሲቪልና ፖለቲካ መብቶችን ተፈጻሚነት የሚከታተለው የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አጠቃላይ ትንታኔ እንዳመለከተው የመንቀሳቀስ ነጻነት ለሌሎች ሰብአዊ መብቶች ተግባራዊነት ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ነው። በዚህም ምክንያት ለምሳሌ በሕይወት የመኖር፣ የመሥራት፣ የንብረት፣ የምግብ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የቤተሰብ፣ የትምህርትና የጤና መብቶች ዕውን እንዲሆኑ ሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል።

የመንቀሳቀስ ነጻነት በውስጡ ምን ምን ጥበቃዎችን ይዟል?

የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች ለመንቀሳቀስ ነጻነት ጥበቃ ማድረጋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን በአንጻራዊነት ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዟል። የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 27 እንደሚያመለክተው በቃል ኪዳኑ አንቀጽ 12 ስለመንቀሳቀስ ነጻነት የተደነገገው በውስጡ በ3 ንዑስ ምድቦች ሊቀመጡ የሚችሉ ነጻነቶችን ያካትታል።

1. በመረጡት አካባቢ የመንቀሳቀስ እና መኖሪያ ቦታ የመመሥረት ነጻነት

በአንድ ሀገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ያለ ማንኛውም ሰው በነጻነት የመንቀሳቀስ እና የመኖሪያ አካባቢውን በነጻነት የመምረጥ መብት (liberty of movement and freedom to choose residence) አለው1 በአንድ ሀገር ውስጥ “በሕጋዊ መንገድ ያለ ሰው” የሚለው አገላለጽ በመርሕ ደረጃ ዜጎችን እና ሕጋዊ መስፈርቶችን አሟልተው በአንድ ሀገር ግዛት ውስጥ የተገኙ ወይም በሕገ ወጥ መንገድ ገብተውም ቢሆን የቆይታ ሁኔታቸው ሕጋዊ የተደረገላቸውን የውጭ ዜጎች ያካትታል።2 በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 32 (1) “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ” የዚህ መብት ተጠቃሚነት ተደንግጓል። የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር በአንጻሩ የተገኘበትን ሀገር ሕጎች እስካከበረ ድረስ “ማንኛውም ሰው” ይህ መብት እንዳለው በአንቀጽ 12 (1) ይገልጻል።

2. የራስን ጨምሮ ከየትኛውም ሀገር የመውጣት ነጻነት

    ማንኛውም ሰው የትኛውንም ሀገር፣ የራሱንም ጭምር፣ ለቆ የመውጣት ነጻነት (freedom to leave any country, including one’s own) አለው።3 የመብቱ ተፈጻሚነት አንድ ሰው ሀገሩን ለቆ በሚወጣበት ዓላማ፣ ከሀገር ወጥቶ በሚቆይበት ጊዜ ወይም ለመዳረሻነት በመረጠው ሀገር ሊወሰን አይገባም።4 ከሀገር መውጣት ዓለም አቀፍ ጉዞና የጉዞ ሰነዶችን የሚጠይቅ እንደመሆኑ፣ ሀገራት ከሀገር ለሚወጡ ዜጎች ፓስፖርት መስጠት ወይም ፓስፖርቱ ጸንቶ የሚቆይበትን ጊዜ ማራዘም አለባቸው።5

    3. ወደ ሀገር የመግባት መብት

      ማንኛውም ሰው ወደ ሀገሩ የመግባት መብቱን (the right to enter one’s own country) በዘፈቀደ አይከለከልም።6 የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 27 እንደሚያብራራው፣ ይህ መብት በዜግነት ያልተገደበ ይልቁንም ከአንድ ሀገር ጋር ልዩ ትሥሥር ያላቸውን ሰዎች የሚያጠቃልል እና ከሀገር ወጥቶ ወደ ሀገር መመለስን (return) ብቻ ሳይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደሀገር መግባትንም የሚሸፍን ነው። የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር በትርጉም ከቃል ኪዳኑ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ድንጋጌ ይዞ የሚገኝ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 32 (2) “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገሩ የመመለስ መብት አለው” ይላል።

      የመንቀሳቀስ ነጻነት ላይ የሚጣሉ ገደቦች ምን ሁኔታዎችን ማሟላት አለባቸው?

      የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን የሰዎች በመረጡት አካባቢ የመንቀሳቀስ እና መኖሪያ ቦታ የመመሥረት እንዲሁም የራስን ጨምሮ የትኛውንም ሀገር ለቆ የመውጣት ነጻነት ላይ በልዩ ሁኔታ ገደብ ሊደረግ እንደሚችል ያመለክታል። በቃል ኪዳኑ አንቀጽ 12 (3) እንደተደነገገው ይህ ገደብ የሚከተሉትን ሁኔታዎች ማሟላት አለበት።7

      • በመብቶቹ ላይ ገደብ ሊደረግ የሚችለው ብሔራዊ ጸጥታን፣ ሰላምና ደኅንነትን፣ የሕዝብን ጤና፣ መልካም ሥነ-ምግባርና የሌሎችን መብቶችና ነጻነቶች ለመጠበቅ ነው።
      • በተጠቀሱት ዓላማዎች መሠረት በመብቶቹ ላይ የሚጣለው ገደብ በሕግ በግልጽ የተደነገገ መሆን አለበት።
      • ገደቦቹ በሕግ ሲደነገጉም ሆነ ሲተገበሩ የተነሱበትን ዓላማ ለማሳካት የአስፈላጊነት (necessity) እንዲሁም የተመጣጣኝነት (proportionality) መርሖዎችን ማክበር አለባቸው።
      • በመብቶቹ ላይ በሕግ የሚጣለው ገደብ እንዲሁም ተግባራዊ የሚደረግበት ሁኔታ በቃልኪዳኑ ከተረጋገጡት ሌሎች መብቶች ጋር በሚስማማ አኳኋን መሆን አለበት።

      የመንቀሳቀስ ነጻነትን ከማረጋገጥ አንጻር የመንግሥታት ግዴታዎች ምንድን ናቸው?

      በሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 12 መሠረት የቃልኪዳኑ አባል ሀገራት የሰዎችን የመንቀሳቀስ ነጻነት የማረጋገጥ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ ይህም የማክበር (duty to respect)፣ የመጠበቅ (duty to protect) እና የማሟላት (duty to fulfill) ግዴታዎችን ያካትታል።

      • የማክበር ግዴታ፦ የቃል ኪዳኑ አባል ሀገራት የሰዎች የመንቀሳቀስ ነጻነት ላይ ጣልቃ ከመግባት ወይም ነጻነቱን ከሚያጣብቡ ተግባራት ሊቆጠቡ ይገባል። ለምሳሌ በመብቱ ላይ የሚጣሉ ገደቦች እና የአፈጻጸማቸው ሁኔታ በቃል ኪዳኑ አንቀጽ 12 (3) በተፈቀደው መሠረት መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው።
      • የመጠበቅ ግዴታ፦ መንግሥታት የሰዎችና የቡድኖች የመንቀሳቀስ ነጻነት ግለሰቦችን ጨምሮ በማናቸውም አካላት እንዳይጣሱ ጥበቃ ሊያደርጉ ይገባል። ለምሳሌ የሴቶችን በመረጡት ቦታ የመንቀሳቀስ ወይም መኖሪያ ቦታ የመመሥረት ነጻነት አሳልፎ ለሌላ ሰው የሚሰጥ ልማድ ቢኖር የመንቀሳቀስ መብትን ስለሚጥስ መንግሥት ጥበቃ ማድረግ አለበት።
      • የማሟላት ግዴታ፦ የመዘዋወር ነጻነትን ሙሉ በሙሉ ዕውን ለማድረግ መንግሥታት አዎንታዊ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው፤ ይህም ለምሳሌ አስፈላጊ የመታወቂያ ሰነዶችን እና መሠረተ ልማቶችን ማቅረብን እንዲሁም የመንቀሳቀስ ነጻነትን የሚያስፋፉ ተቋማዊ እና ሕጋዊ ማዕቀፎችን ማሟላትን ይጨምራል።

      1 የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን፣ አንቀጽ 12 (1)።

      2 የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 27፣ ፓራግራፍ 4።

      3 የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን፣ አንቀጽ 12 (2)።

      4 የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 27፣ ፓራግራፍ 8።

      5 የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 27፣ ፓራግራፍ 9።

      6 የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን፣ አንቀጽ 12 (4)።

      7 የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 27፣ ፓራግራፍ 11 – 18።