የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ሰኔ 19 ቀን የማሰቃየት ተግባር ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን የመደገፍ ዓለም አቀፍ ቀን እንዲሆን ባወጀው መሰረት በተለያዩ የዓለማችን ክፎሎች በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቷል፡፡
የማሰቃየት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት ድርጊት የሚከለክል ጠንካራ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የሕግ ማዕቀፍ ቢኖርም ሰዎች ለዚህ አይነት ድርጊት ሰለባ ሲሆኑ ይታያል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ ኢሰመኮ ባወጣቸው ሪፖርቶች እንደተመለከተው በጦርነቱ አውድ በሲቪል ሰዎች እንዲሁም በተሳታፊ ወገኖች አባላት ላይ የጭካኔ እና የማሰቃየት ተግባር የተሞላበት ጥቃት እንደደረሰባቸው ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የማሰቃየት ተግባር ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን የመደገፍ የዓለም አቀፍ ቀንን አስመልክቶ አውድ ጥናት በማዘጋጀት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ ጋዜጠኞች፣ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ያሳተፈ መድረክ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. አካሂዷል። በዝግጅቱ ሰለባ ለሆኑ ተጎጂዎች ፍትሐዊ እና በቂ የሆነ ካሳ የማግኘት መብት እንዳላቸው፤ መንግሥት ይሄንን መብት የማስጠበቅ ግዴታ እንዳለበት እና የድርጊቱ ሰለባ ተጎጂዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ተጽዕኖው በቤተሰቦቻቸው እና በማኅበረሰቡም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ተገልጿል።
በዝግጅቱ የ UN Voluntary Fund for Victims of Torture የባለ አደራ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ሎረንስ ሙሩጉ ሙቴ ከዓለም አቀፍ መስፈርቶች አንጻር እዲሁም የጭካኔ ከተሞላበት ኢሰብዓዊ ድርጊት ተጎጂ ፍትሕዊና በቂ ካሳ አግኝቶ በተቻለ መጠን ከጉዳቱ ሙሉ በሙሉ የሚያገግምት ሁኔታ የሚፈጥር ሕጋዊ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊነት በተመለከት የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ የኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ የስራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ሕጎድ ላይ ዳሰሳ እና በሕጉ ክፍተቶች ላይ ማብራርያ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም የጭካኔ ተግባራት ዙርያ ያተኮር አውደ ርዕይ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በጉዳዩ ዙርያ የሚያውጠነጥኑ ስዕሎች ቀርበውበታል። አውደ ርዕዩ እስከ ሳምንቱ ማብቂያ በኢሰመኮ ዋና መሥሪያ ቤት መግቢያ የሚታይ ይሆናል። እንዲሁም በአውደ ጥናቱ ማብቅያ የማሰቃየት ተግባር ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን የሚደርስባቸውን አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት የሚያሳይ አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል (ፊልም) ለስብሰባው ተሳታፊዎች ለዕይታ ቀርቧል፡፡ ፊልሙን እዚህ ማግኘት ይችላሉ።
በአጠቃላይ አውደ ጥናቱ አስተማሪ እና ወቅታዊ የሆኑ ሀሳቦችን በፈጠራ ሥራዎች በታገዘ መልኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተሻለ የአሠራር ስልት ለመፍጠር እንዲያስችል እና የመፍትሔ ሃሳቦችን ላይ ለመወያየት አስችሏል፡፡