በተለይም ሀገራችን አሁን በምትገኝበት የሰሜኑ ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነትና ድኅረ -ግጭት ዓውድ፤ የሰላም ግንባታ እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፎች በጦርነት ዓውድ ውስጥ ለተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ተጠያቂነትን፣ እንዲሁም የተጎጂዎችን የተሟላ ፍትሕ እና ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት መብትን (right to effective remedy) ባረጋገጠ መልኩ እንዲተገበር እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በዚሁ አጋጣሚ ከዚህ በፊት ስለ ሽግግር ወቅት የፍትሕ አስተዳደር ያቀረባቸውን ምክረ ሃሳቦችና በተለይም ስለ ጾታዊ ጥቃቶች ተጠያቂነት ሊሰጥ የሚገባውን ልዩ ትኩረት በድጋሚ ለማስታወስ ይወዳል።
የሰላም ግንባታ እና የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች ግጭቶች በዘላቂነት የሚፈቱበትን መንገድ እና ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የተጠያቂነት ማዕቀፍ የሚዘረጋበትን ሥርዓት በመቀየስ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ይህም በግጭቶች ዓውድ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ባሕርይ፣ ክብደት እና የጉዳት መጠንን መሠረት ያደረገ የተጠያቂነት ማዕቀፍ ለመዘርጋት፤ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ ውጤታማ መፍትሔ እና የድኅረ-ግጭት መልሶ ማቋቋም ሥርዓት ለመንደፍ የሚያስችል መደላድል ይፈጥራል።
በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች በተለይም አስከፊ ጦርነት በተካሄደባቸው በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ወሲባዊ ጥቃቶች እና በሴቶች ላይ ያነጣጠሩ ግፍና ጭካኔ የተሞላባቸው የጾታዊ ጥቃት ተግባራት የስልታዊነት አዝማሚያ እንዳሳዩ የኮሚሽኑ ግኝቶች ጠቁመዋል። በርካታ ሴቶች ላይ ለተፈጸሙት መጠነ-ሰፊ እና ስልታዊ ጥቃቶች ምላሽ ከመስጠት አኳያ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የተሟላ የፍትሕ እና የዘላቂ ተሀድሶ ሂደት መሠረታዊ ነው።
የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት የሰላም ስምምነት በአንቀጽ 10 (3) እንደሚገልጸው የኢትዮጵያ መንግሥት የተጠያቂነት፣ የእውነትን ማረጋገጥ፣ የተጎጂዎችን ማካካሻ፣ ዕርቅ እና መፈወስ ያለመ አጠቃላይ ሀገራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ አልሟል። ከሽግግር ፍትሕ ዋና ዋና ስልቶች መካከልም አንዱ ተጠያቂነት እንደመሆኑ መጠን ስምምነቱ ተጠያቂነትን በግልጽ ታሳቢ ያደረገ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን ለመቀየስ ያለመ መሆኑ በጦርነቱ ውስጥ በተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጎጂ ለሆኑት ሴቶች ተስፋን የሚሰጥ ነው፡፡ ይህን ተስፋ ዕውን ለማድረግ በግጭት ውስጥ ለተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች የተጠያቂነት ማዕቀፍን እና በቁልፍ ሂደቶች ውስጥ የተጎጂ ሴቶች ተሳትፎን በተመከለተ ግልጽ ፍኖት በአፋጣኝ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ይህ በሌለበት ሁኔታ የሚከናወኑ የሰላም ግንባታ እና የሽግግር ፍትሕ ጥረቶች ጾታን መሠረት ያደረጉ መድሎዎች እና ጥቃቶች እንዲቀጥሉ ያደርጋሉ። በተለይም በግጭት ወቅት የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን እና የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል፣ የተፈጸሙትን ጥቃቶች እና የወንጀል ድርጊቶች ለመመርመር እና አጥፊዎችን ለመቅጣት፣ እንዲሁም ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በመንግሥት በኩል የተሟሉ እርምጃዎች ገና የሚቀሩ ስለሆነ፤ በሴቶች ላይ አሁንም ሊደርሱ ለሚችሉ ጾታዊ ጥቃቶችና የተጋላጭነት ሁኔታዎች ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
ስለሆነም በግጭት ወቅት ለተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋምና ለወደፊቱም መሰል ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚከተሉትን ቁልፍ ነጥቦች ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
- ከሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ጋር በሚጣጣም መልኩ የሕግ እና የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ማድረግ
በግጭት ወቅት ለሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች የሕግ ተጠያቂነትን በሚመለከት በሀገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ ያሉትን ሰፊ ክፍተቶች ለመቅረፍ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች መሠረት የሕግ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲሁም ለጾታዊ ጥቃቶች ምላሽ ከመስጠት አኳያ የፍትሕ ሥርዓቱን የውጤታማነት ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት አስፈላጊውን የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ በማድረግ በግጭት ወቅት በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የተፈጸሙ ወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃቶችን ለመዳኘት የሰብአዊ መብቶች መርሆችን እና ዓለም አቀፍ ልምዶችን መሠረት ያደረገ የፍትሕ ሂደትን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል።
2. የተጎጂዎችን መብት ማዕከል ያደረገ የወንጀል ምርመራ ስልት ተግባራዊ ማድረግ
የጾታዊ ጥቃት ወንጀል ምርመራዎችን በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መሠረት ለማከናወን አፋጣኝ፣ ገለልተኛ፣ ነጻ፣ የጾታዊ ጥቃቶች አፈጻጸም ውስብስብነትን ታሳቢ ያደረገ ውጤታማ የምርመራ ስልት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መተግበር አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መሠረት የተጎጂዎችን መብቶች ማዕከል ያደረገ፣ እንዲሁም የሥርዓተ-ጾታ ትንታኔዎችን እና የሴቶች መብቶች መስፈርቶችን ባካተተ መልኩ የምርመራ ሂደቱን በተገቢው ጥራት እና ወቅታዊነት ማከናወን ይኖርበታል።
3. ክስ መመስረትና አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ
መንግሥት በማናቸውም ጊዜ እና በተለይም በግጭት ወቅት የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን የመመርመር፣ ክስ የመመስረት እና የድርጊቱን ፈጻሚዎችን የመቅጣት ኃላፊነት አለበት። ስለዚህም ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ፍትሕን ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊ የምርመራ እና ክስ የመመስረት ሥራዎች ወቅታዊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
4. ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የካሳና የተሐድሶ ማዕቀፍን ማረጋገጥ
መንግሥት ተገቢውን የሕግ ማዕቀፍ በመቅረጽ በግጭት ዓውድ ለተከሰቱ ጾታዊ ጥቃቶች ውጤታማ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል የፍትሐ ብሔር አማራጭ፣ የትግበራ ማዕቀፍ፣ እንዲሁም ተጎጂዎች የማገገሚያ ወይም የተሐድሶ ድጎማ የሚያገኙበትን ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል።
5. ሕብረተሰቡን ማስተማር
ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የመድልዎ እና የዳግም ጥቃት ሰለባ በመሆናቸው መንግሥት ይህን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሕብረተሰቡን ማስተማር፣ እንዲሁም መድልዎ እና መገለል የሚፈጽሙ ግለሰቦች እና ቡድኖችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
6. የተቀናጀ የድጋፍ እርምጃዎችን መውሰድ
ከግጭቶች ጋር በተያያዘ የተጎዱ ሴቶችን እና ሕፃናትን ለመደገፍ፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልጉ ሥራዎችን ለማስቀጠልና ለማስተባበር በተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሠራር የተጠናከረ፣ ውጤታማና ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት የሚስችል መሆን ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም በግጭት ዐውድ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ሕፃናት የማገገሚያና መልሶ የማቋቋሚያ፣ የጤና እና የሥነ-ልቦና ድጋፍ፣ የፍትሕ እና ሌሎች አገልግሎቶች አቅርቦትን የማስተባበር ሥራ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መቀላጠፍ ይኖርበታል።’
7. ተአማኒ የሆነ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት መቀየስ እና ተግባራዊ ማድረግ
በግጭት ዓውድ ለተፈጸሙ መጠነ-ሰፊ እና ውስብስብ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የተሟላ ፍትሕ እና ውጤታማ መፍትሔ ለመስጠት ግጭቶች እና ጥቃቶች እንዳያገረሹ በዘላቂነት ለመፍታት የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ መዘርጋት አስፈላጊ ነው። ተጠያቂነት፣ የጉዳት ማካካሻ፣ ዕውነትን የማውጣትና የማወቅ እንዲሁም ሁለንተናዊ ማገገምን ማዕከል ያደረገ፣ በሰብአዊ መብቶች መርሆች እና በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፎች ላይ የተመሠረተ ተአማኒነት ያለው ሀገር አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት መቀየስ እና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል።
8. በሰላም ግንባታና በሽግግር ፍትሕ ወቅት ሴቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው እና ድምፃቸው እንዲካተት ማድረግ
የሴቶች ተሳትፎ ዘላቂ ሰላምን እና የተሟላ ፍትሕን ለማስፈን ወሳኝ ነወ። በሰላም ድርድርና ስምምነት እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ውስጥ በሁሉም ደረጃ እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች የሴቶችን ትርጉም ያለው ተሳትፎ እና የውሳኔ ሰጪነት ሚና ማረጋገጥ ይገባል። ማናቸውም የሰላም እና የፍትሕ ማዕቀፍ ግንባታ ጥረቶች የተጎጂ ሴቶችን ጥያቄ፣ ፍላጎት እና ድምፅ በአግባቡ ያካተቱ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አጠቃላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሙሉ በሙሉ በመፍታት ጾታዊ እኩልነትን ማስፈን፣ በጾታዊ ጥቃቶች እና በሥርዓተ-ጾታ ላይ የተመሠረቱ ጥሰቶች እና ዋና መንስኤዎቻቸው ላይ ልዩ ትኩረት መስጠትም ያስፈልጋል።