የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሲፈጸም እንደ ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ያሉ የመንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ብሔራዊ፣ አህጉራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች፣ ለዚሁ ዓላማ በጊዜያዊነት የሚቋቋሙ እውነት አፈላላጊ አደረጃጀቶች፣ ሚዲያዎች ወዘተ. የየራሳቸውን ምርመራ ሊያከናውኑ ይችላሉ። እነዚህ ምርመራዎች የየራሳቸው ስያሜ፣ ባሕሪ፣ የአከዋወን ሥነ-ዘዴ እና ግብ አላቸው።
ከእነዚህ የምርመራ ዐይነቶች ዋነኞቹ የሆኑት የሰብአዊ መብቶች ምርመራ እና የወንጀል ምርመራ በተግባር ከአንድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጥርጣሬ ሊነሱ የሚችሉ እንዲሁም ፍትሕን እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት በማረጋገጥ ረገድ የየራሳቸው አስተዋጽዖ ያላቸው ናቸው። ሆኖም በሚመሩበት የሕግና ተቋም ማዕቀፍ፣ በዓላማቸውና በግባቸው እንዲሁም በሚከተሉት የማስረጃ ምዘና ስልት (ሥነ-ዘዴ) መሠረታዊ ልዩነቶች አሏቸው።
የሰብአዊ መብቶች ምርመራ እና የወንጀል ምርመራ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፎች ምንድን ናቸው?
የሰብአዊ መብቶች ምርመራ የሚከናወነው ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ሕጎችን እና ሰነዶችን መሠረት በማድረግ ነው። ይህ የምርመራ ዐይነት በእነዚህ ሰነዶችና ሕጎች ዕውቅና በተሰጣቸው መብቶች ላይ የተፈጸሙ ጥሰቶችን አስፈላጊ ከሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች/ሁኔታዎች ጋር የሚለይና የሚተነትን ነው። ለምሳሌ የአንድ የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ውጤት በአንድ በተወሰነ አካባቢ ወይም ጊዜ ማንነታቸው ወይም ቁጥራቸው በውል በታወቀ ወይም ባልታወቀ ሰዎች ላይ ከሕግ/ፍርድ ውጭ ግድያ የተፈጸመ መሆኑን ሊያመለክት ይችላል።
የወንጀል ምርመራ በአንጻሩ አግባብነት ባላቸው የወንጀል ሕጎች መሠረት ወንጀልነቱ የተደነገገ አንድ ድርጊት መፈጸሙን፤1 ይህም ሲባል ወንጀሉን የሚያቋቁሙት ሕጋዊ (legal)፣ ግዙፋዊ (material) እና የሐሳብ ክፍል (moral) አላባዎች በሚገባ መሟላታቸውን በሚያስረዳ ሁኔታ መረጃዎችና ማስረጃዎች የሚሰበሰቡበት የምርመራ ዐይነት ነው። ስለዚህ ከላይ በተጠቀሰው ምሳሌ አንድ የወንጀል ምርመራ ከሕግ/ፍርድ ውጭ ግድያ የተፈጸመ መሆኑን ከማመልከት ባሻገር ወንጀሎቹን በሚዘረዝሩት ድንጋጌዎች መሠረት ከባድ የሰው ግድያ፣ ተራ የሰው ግድያ፣ በቸልተኛነት የሚፈጸም የሰው ግድያ ወይም ሌላ የግድያ ወንጀል ዐይነት ስለመፈጸሙ ለይቶ እንዲያስረዳ ይጠበቃል። የወንጀል ድርጊቱ ዓለም አቀፍ ወንጀልን የሚያቋቁም ከሆነም በዚሁ መሠረት አስፈላጊ የሆኑ አላባዎችን በመመሥረት፣ የትኛው ዓለም አቀፍ ወንጀል፣ በማን፣ እንዴት፣ መቼ፣ ወዘተ. ጥያቄዎችን መመለስ እና የግል ወይም የወል ተጠርጣሪዎችን በስም ጭምር ለይቶ ክስ መመሥረት እና ፍትሕና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አለበት።
የሰብአዊ መብቶች ምርመራዎች በብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ብሔራዊ፣ አህጉራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች፣ በጊዜያዊነት በሚቋቋሙ እውነት አፈላላጊ አደረጃጀቶች፣ ወዘተ. ሊከናወኑ ይችላሉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንደ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ቅሬታዎች ሲቀርቡለት ወይም በራሱ አነሳሽነት ምርመራ የማድረግ ሥልጣንና ተግባር ተሰጥቶታል።2 የምርመራ ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ወንጀል መሠራቱን ያመነ እንደሆነ ለሚመለከተው አካል በጽሑፍ የማስታወቅ ግዴታ አለበት፤3 ሆኖም በራሱ የወንጀል ምርመራ ለማከናወን የሚችልበት ሥልጣን የለውም።
ከሀገር ሀገር መጠነኛ ልዩነት ሊኖረው ቢችልም፣ በብሔራዊ ደረጃ የወንጀል ምርመራ የሚከናወነው በመንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካላት በተለይም በፖሊስ እና በዐቃቤ ሕግ ተቋማት ነው።4 ለምሳሌ በኢትዮጵያ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የፌዴራል ፖሊስ ኅብረተሰቡን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የወንጀል ምርመራ የማከናወን ኃላፊነት የተጣለበት ሲሆን፤ የፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር የማድረግ፣ አፈጻጸሙን የመከታተል፣ በሕግ በተደነገገው መሠረት እንዲቋረጥ ወይም የተቋረጠው እንዲቀጥል የመወሰን እንዲሁም ምርመራው በሕግ መሠረት መከናወኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት።
የሁለቱ የምርመራ ዐይነቶች ዓላማዎችና ግቦች ምንድን ናቸው?
የሰብአዊ መብቶች ምርመራ በአንድ በተወሰነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጥርጣሬ (allegation) ላይ ተመሥርቶ የሚከናወን እውነትን የማፈላለግ ተግባር ሲሆን፣ ለምርመራው መነሻ የሆነውን ጉዳይ (incident) ዝርዝር ሁኔታ የተመለከቱ መረጃዎችና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ እና በማጣራት የተጎጂዎችን እና የአጥፊዎችን ማንነት ይለያል፤ የተጣሱ የሰብአዊ መብቶች ሕጎች ድንጋጌዎችን እና ጉዳዩ የሚያቋቁመውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዐይነትና ደረጃ ይበይናል፤ እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገባቸውን የመፍትሔ እርምጃዎች (ምክረ ሐሳቦች) ያመላክታል። የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ወደ ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ የሚችል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተቀዳሚ ዓላማውና ውጤቱ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን፣ መከበርን እና መስፋፋትን ትኩረቱ ላደረገ የውትወታ ሥራ (advocacy) መሠረት የሚሆኑ ግኝቶችን መለየት ነው። በሰብአዊ መብቶች ምርመራ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ይለያሉ፤ ይሰነዳሉ፤ ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች እንደ አስፈላጊነቱ በይፋዊ ሪፖርቶች ወይም በምስጢራዊ ግንኙነቶች ለሚመለከታቸው አካላት ይገለጻሉ። ምክረ ሐሳቦቹ ምርመራ በተደረገበት ጉዳይ ላይ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት እና የተጎጂዎችን ተመጣጣኝ ካሳ የማግኘት መብት የሚያረጋግጡ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንዲሁም የፖሊሲና የሕግ ወይም የአሠራር ማሻሻያዎች እንዲደረጉ የሚጠይቁ ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላ በኩል የሰብአዊ መብቶች ምርመራ በተከናወነበት ጉዳይ ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲካሄድ ምክረ ሐሳብ ሊቀርብ የሚችል ሲሆን፤ ኢሰመኮ በሶማሊ ክልል ቦምባስ ከተማ በባሕላዊ ሥነ-ሥርዓት የጎሳ መሪ (ሱልጣን) ለመምረጥ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ እና የአካል ጉዳት በተመለከተ እንዲሁም በአፋር እና በአማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በቆየው የሰሜኑ ጦርነት የተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ያከናወናቸው ምርመራዎች የዚህ ማሳያዎች ናቸው።
የወንጀል ሕግ የሰብአዊ መብቶችን ጥሰት ወንጀል አድርጎ በመበየን ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ የሚያደርግ የሕግ ዘርፍ ከመሆኑ አንጻር፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የወንጀል ምርመራን ሊያነሳሱ ይችላሉ። የወንጀል ምርመራ አድራጊዎች ከወንጀል መፈጸም ጥርጣሬ በመነሳት፣ የወንጀል ድርጊቱን ዝርዝር ሁኔታ፣ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ማንነት እና የተሳትፎ ደረጃ እንዲሁም የተጎጂዎችን ብዛት፣ ማንነት እና የጉዳት ሁኔታ የተመለከቱ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በመተንተንና በማደራጀት ፍትሐዊ የወንጀል ዳኝነት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። የወንጀል ምርመራ በአጥፊዎች ላይ ክስ ለማቅረብ፣ የጥፋተኝነት ውሳኔ ለማሰጠት እና ተገቢውን የቅጣት ውሳኔ ለማሳለፍ መሠረት የሚሆነውን የምርመራ ውጤት/ሰነድ ያቀርባል።
በሁለቱ የምርመራ ዘርፎች መካከል ያለው የማስረጃ ምዘና ስልት ልዩነት ምን ይመስላል?
የሰብአዊ መብቶች ምርመራም ሆነ የወንጀል ምርመራ ሥራዎች መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን በአግባቡ መሰብሰብን፣ ማደራጀትን፣ መተንተንን እና መመዘንን ይጠይቃሉ። ሆኖም ሁለቱ የምርመራ ዐይነቶች ይዘውት ከሚነሱት ዓላማና ግብ፣ ምርመራውን ከሚያከናውኑት ተቋማት ባሕሪ፣ ዓላማና ዐቅም እንዲሁም በምርመራው የተደረሰበት ግኝት በተለይም በአጥፊዎች ላይ ከሚኖረው አንድምታ አንጻር የተለያየ የማስረጃ ምዘና ስልት ወይም ደረጃ ይከተላሉ።
የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ሪፖርት በተአማኒ የመረጃ ምንጮች እና በተረጋገጡ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ምክንያታዊ ጥርጣሬ (reasonable suspicion)፣ ሚዛን የሚደፋ ግምት/በቂ ማስረጃ (balance of probabilities/sufficient evidence)፣ ግልጽ እና አሳማኝ ማስረጃ (clear and convincing evidence)፣ እንዲሁም ከበቂ በላይ የሆነ ማስረጃ (overwhelming evidence) እንደሁኔታው በአንድነት እና በተናጠል አገልግሎት ላይ ሊውሉ የሚችሉ ተቀባይነት ያላቸው የሰብአዊ መብቶች ምርመራ የማስረጃ ደረጃዎች ናቸው። ለአብነት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሰብአዊ መብቶች ምርመራዎቹ ላይ የሚጠቀመው የማስረጃ ምዘና ስልት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሰል ሥራዎች አገልግሎት ላይ የሚውለው “ምክንያታዊ አሳማኝነት” (reasonable grounds to believe) ነው። ይህም ከአንድ ተአማኒ ምንጭ የተገኘውን መረጃ ቢያንስ ከሁለት ተጨማሪ ገለልተኛ እና አስተማማኝ ምንጮች በተገኘ ተመሳሳይ ወይም የማይጣረስ መረጃ በመደገፍ/በማረጋገጥ (corroboration)፣ አንድ ምክንያታዊ የሆነን ሰው ስለ አንድ ነጠላ ክስተት ወይም ተደጋጋሚ ጥሰት መፈጸም ሊያሳምን በሚችል አግባብ ድምዳሜ ላይ የሚደረስበት የማስረጃ ምዘና ስልት ነው።
በአንጻሩ አንድ የወንጀል ምርመራ የወንጀሉን መፈጸም “ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በላይ” (beyond reasonable doubt) ማስረዳት የሚችል ማስረጃ ማሰባሰብን ታሳቢ በማድረግ መከናወን አለበት። ምክንያቱም በአንድ በኩል የወንጀል ምርመራ አጥፊዎች ላይ የወንጀል ክስ በመመሥረት በፍርድ ቤት ውሳኔ ጥፋተኛነትን ለማረጋገጥ ስለሚውል፤ በሌላ በኩል ማንኛውም ሰው ወንጀል መሥራቱ በፍርድ ቤት እስካልተረጋገጠ ድረስ ከጥፋት ነጻ ሆኖ የመቆጠር መብት ያለው በመሆኑ እና በተካሄደው የወንጀል ምርመራ ውጤት መሠረት በፍርድ ቤት ጥፋተኛ መባሉ በመብቱና በነጻነቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስለሚያሳድርበት ነው።
ሁለቱ የምርመራ ዘርፎች የሰብአዊ መብቶችን ጥበቃ ለማሻሻል በምን መንገድ ሊደጋገፉ ይችላሉ?
የሰብአዊ መብቶች ምርመራ እና የወንጀል ምርመራ በመነሻም፣ በአካሄድም፣ በውጤትም መሠረታዊ ልዩነቶች ያሏቸው እና የማይተካኩ (non-interchangeable) የምርመራ ዘርፎች ናቸው። ሆኖም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎች ተገቢውን ፍትሕ እንዲያገኙ እና አጥፊዎችም ተጠያቂነት እንዲረጋገጥባቸው በማድረግ ረገድ እርስ በርሳቸው ይደጋገፋሉ። ለምሳሌ የሚከተሉትን ማንሳት ይቻላል፦
- የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን ጨምሮ ሌሎች በሕግ ወንጀል ተብለው የተበየኑ ጥፋቶች ስለመፈጸማቸው አመላካች የሆኑ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ያቀርባል። በዚህም የተሟላ የወንጀል ምርመራ እንዲደረግ ከማነሳሳት ባሻገር ለሂደቱ ጠቃሚ ግብአት የሚሆኑ መረጃዎችና ማስረጃዎችን ይሰጣል። በዚሁ መሠረት የሚከናወን የወንጀል ምርመራ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ይረዳል።
- እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ተጎጂ-ተኮር (victim-centered) የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ባልዳበረባቸው ሀገራት ተጎጂዎች በወንጀል ፍትሕ ሂደት ካሳን እና መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ምላሽ ለማግኘት ይቸገራሉ። የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ውጤቶችን ተመሥርተው የሚከናወኑ የሰብአዊ መብቶች ውትወታ (advocacy) ሥራዎች ተጎጂዎች ተጨማሪ የፍትሐ ብሔር እንዲሁም የአስተዳደር መፍትሔዎችን እንዲያገኙ ያግዛሉ። ስለዚህ የሁለቱ የምርመራ ዘርፎች ቅንጅት ለተጎጂዎች የተሟላ የምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት (comprehensive response system) ይፈጥራል።
- የወንጀል ምርመራ በሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችና መርሖች የተቃኘ መሆን አለበት። ሆኖም በአሠራር ሂደት ምርመራው የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብቶች ለምሳሌ ፍትሐዊ ዳኝነት የማግኘት፣ ከፍርድ በፊት ነጻ ሆኖ የመቆጠር፣ ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብአዊ ከሆነ ወይም ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝ የመጠበቅ ወዘተ. መብቶችን በሚጥስ ሁኔታ ሊካሄድ ይችላል። የሰብአዊ መብቶች መርማሪዎች በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ ሲፈቀድላቸው የወንጀል ምርመራ ሂደትን ወይም የተጠርጣሪ አያያዝ ሁኔታን በመመርመርና ጥሰቶችን በመለየት ተጠያቂነት ያለበት የወንጀል ምርመራ ሥርዓት እንዲረጋገጥ ያግዛሉ።
- ሁለቱን የምርመራ ዘርፎች ያቀናጀ ስልታዊ ምርመራ፣ በሰብአዊ መብቶች መከበርና ጥበቃ ረገድ ያሉ መዋቅራዊና ሥር የሰደዱ ችግሮችን፣ የሕግና የፖሊሲ ወይም የአሠራር ክፍተቶችን እንዲሁም የጥሰት ሁኔታዎችን እና አዝማሚያዎችን በሚገባ ለመለየት ይረዳል። ይህም ለተሻለ የሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ጥበቃ እና መስፋፋት ጠቀሜታ ያላቸውን የሕግና የፖሊሲ እንዲሁም የአሠራር ማሻሻያዎችን ለማመላከት ያስችላል።
[1] የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በሕግ በወንጀልነት እስከተደነገጉ ድረስ የወንጀል ምርመራ ጉዳዮች ሊሆኑ ሲችሉ፣ የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ግን ማንኛውንም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ይመለከታል።
[2] የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 210/1992 በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው፤ አንቀጽ 6 (4)
[3] የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 210/1992 በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው፤ አንቀጽ 28
[4] በአንዳንድ ሀገራት የግል መርማሪዎች (private investigators) እንዲሁም ለተወሰነ ጊዜ የሚቋቋሙ እውነት አፈላላጊ አደረጃጀቶች የሚሳተፉበት ሥርዓት አለ።