1. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ በግጭት ዐውድ ውስጥና ከግጭት ዐውድ ውጪ ባሉ አካባቢዎች ያሉ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን ለመለየት እና ለመሰነድ ከሚያዝያ ወር 2017 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2018 ዓ.ም. በተለያዩ ክልሎች የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም መሠረት በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎችን፣ የዓይን ምስክሮችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን እንዲሁም የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላትን በማነጋገር መረጃ እና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ከለያቸው አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች መካከል የሰዎችን ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነትን የተመለከቱ ግኝቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል።
  2. ይህ መግለጫ በክትትል እና ምርመራ በተሸፈነው ጊዜ እና ቦታ የተለዩ ሁሉንም ግኝቶች የሚይዝ ሳይሆን የመዘዋወር መብት አፈጻጸምን የሚሸረሽሩ እና የተከሰቱ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመለየት የሰብአዊ መብት ሁኔታውን ለማሳየት ታስበው የተመረጡ ጉዳዮችን ያካተተ ነው።
  3. ኢሰመኮ በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይም ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት በበጀት ዓመቱ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን መግለጹ የሚታወስ ነው። በዚህ መግለጫ በዓመታዊ ሪፖርቱ ከተገለጹ ግኝቶች የተወሰኑ የተካተቱ ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት የሰብአዊ መብት ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን ለማሳየትና በድጋሚ ጥሪ ማቅረብ በማስፈለጉ እንዲሁም ዓመታዊ ሪፖርቱ ይፋ ከሆነ በኋላ የታዩ ተጨማሪ ጉዳዮች በመኖራቸው ነው።
  4. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ሀገር ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር ነጻነት እንዳለው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል። ይህ መብት በተሟላና ትርጉም ባለው ሁኔታ ሊተገበር የሚችለው ሰዎች በነጻነት፣ በሰላምና ያለአግባብ ገደብ ሳይጣልባቸው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው።
  5. ክትትል እና ምርመራ በተከናወነባቸው ቦታዎች በተለይም በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚጣሉ የሰዓት እላፊ የእንቅስቃሴ ገደቦች፣ በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በመንገዶች ላይ በሚጣሉ ኬላዎች፣ የመንገድ መዝጋት ትዕዛዞችና እርምጃዎች እንዲሁም በመንገዶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እገታዎች፣ የንብረት ዘረፋዎች እና ውድመቶች የሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት መብት አደጋ ላይ መውደቁን ኢሰመኮ ለመገንዘብ ችሏል። ኢሰመኮ እነዚህ እርምጃዎች እና ጥቃቶች ከመዘዋወር ነጻነት መብቶች ባሻገር በሕይወት የመኖር፣ የአካልና የንብረት ደኅንነት መብቶች ላይም ጥሰቶችን ማስከተላቸውን አረጋግጧል። እንዲሁም የዕለት ከዕለት ተግባራትን በማወክና የማኅበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽነትን በመገደብ በድርጊቶቹ ተጎጂዎች ላይ በቀጥታ ከሚደርሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪም በኅብረተሰቡ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆናቸውን ለመረዳት ችሏል።
    • በመንገዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና እገታዎች
  6. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአሶሳ ከተማ በኦሮሚያ ክልል በኩል አድርጎ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደውና ከከማሽ ዞን ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚወስደው መንገድ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) በሚያደርሰው የጥቃት ስጋት ምክንያት እንዲሁም ከአሶሳ ዞን ወደ መተከል ዞን የሚወስደው መንገድ ቀሪ በእርቅ ወደ ሰላም ባልተመለሱ የጉሙዝ ታጣቂዎች የጥቃት ስጋት ምክንያት ይህ ሪፖርት እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ዝግ በመሆናቸው የክልሉ ነዋሪዎች በነጻነት መንቀሳቀስ የማይችሉ መሆኑና አልፎ አልፎ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እጀባ የሚደረገው ጉዞ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ እንግልት እያስከተለ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
  7. ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 1200 ሰዓት አካባቢ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ስሬ ወረዳ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) መነሻውን አዳማ ከተማ አድርጎ ስሬ ከተማን አቋርጦ ወደ ጮሌ ከተማ በጉዞ ላይ የነበረን የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ከስሬ ከተማ 10 ኪ.ሜ ላይ ልዩ ቦታው ‘አሞላ ታቦ’ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በማስቆም ሴቶችንና ሕፃናትን በማስቀረት ቁጥራቸው በግምት 40 የሚሆኑ ተሳፋሪዎችን አግቶ ወደ ማይታወቅ ቦታ እንደወሰዳቸው ለማረጋገጥ ተችሏል። ከተሳፋሪዎች መካከል 1 ሰው በእገታ ወቅት ከመኪና ወርዶ ለማምለጥ ሲሮጥ በታጣቂ ቡድኑ በተተኮሰበት ጥይት ተመቶ መገደሉን እና አስከሬኑ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. መቀበሩን ኢሰመኮ አረጋግጧል። በቡድኑ ታግተው ከተወሰዱት ሰዎች መካከል የተወሰኑት ለታጣቂ ቡድኑ ገንዘብ በመክፈል መለቀቃቸውን እና የተቀሩት ደግሞ ዘግይቶ በታጣቂ ቡድኑ ያለክፍያ መለቀቃቸውን ኢሰመኮ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማረጋገጥ ችሏል። በተመሳሳይ በአካባቢው በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው መርቲ ወረዳ (አቦምሳ ከተማ) በታጣቂ ቡድኑ እንቅስቃሴ ምክንያት በተፈጠረው የጸጥታ ስጋት እና ተደጋጋሚ የመንገደኞች እገታ ምክንያት ወደ አዳማ ከተማ እና በአከባቢው ሲደረግ የነበረው መደበኛ የሕዝብ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ለማወቅ ተችሏል።
  8. ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ጠዋት 2፡00 ሰዓት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ዶሮ ቦሮ ቀበሌ ልዩ ቦታው አንዶዴ ዲቾ በተባለ ቦታ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን (በተለምዶ ፋኖ) ከጊዳ አያና ወደ አዲስ አበባ ሕዝብ አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ እገታ በመፈጸም ከእገታው ለማምለጥ ሙከራ ባደረጉት ተሳፋሪዎች ላይ በተተኮሰ ጥይት 1 መንገደኛ መገደሉን፣ 6 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸውን እና እያንዳንዳቸው 200,000 ብር በመክፈል መለቀቃቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል
  9. ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ በተለምዶ ‘ፋኖ’ ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ከጊዳ አያና ወረዳ ወደ ጉትን ከተማ ሕዝብ ጭኖ በመጓዝ ላይ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በማስቆም ተሳፋሪዎች የያዙትን ገንዘብና የተለያዩ ንብረቶችን ዘርፎ መሰወሩን ማወቅ የተቻለ ሲሆን ታጣቂ ቡድኑ በአካባቢው እየፈጸመ ባለው ተደጋጋሚ እገታ እና ዘረፋ ምክንያት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ያለመንግሥት የጸጥታ አካላት እጀባ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው በአከባቢው በመደበኛ ሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ መስተጓጎል መፈጠሩን ማረጋገጥ ተችሏል።
  10. ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ጠዋት 3፡00 ሰዓት አካባቢ ከነጌሌ ቦረና ከተማ ወደ ጉሜ ኤልደሎ ወረዳ ሲጓዝ የነበረው የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ሊበን ወረዳን ተሻግሮ ጉሚ ኤልደሎ ወረዳ ድንበር ላይ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂ ቡድን በተፈጸመ እገታ የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት እና የመንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጂስትክ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችን ጨምሮ በአጠቃላይ 22 መንገደኞች መታገታቸውን ለማወቅ ተችሏል። ከታገቱት ሰዎች መካከል አሽከርካሪው፣ ረዳቱ እና ሌሎች 4 ሰዎች በዕለቱና ቀሪዎቹ ደግሞ በግንቦት ወር መጨረሻ አካባቢ መለቀቃቸውን እንዲሁም አሽከርካሪው የተለቀቀው 60,000 ብር ከፍሎ መሆኑና ሌሎቹ ታጋቾች ደግሞ ያለ ክፍያ የተለቀቁ መሆኑን ኢሰመኮ ማረጋገጥ ችሏል።
  11. ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ከምሽቱ 200 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ ከቀርጫ ወረዳ ወደ ብርብርሳ ኮጆዋ ወረዳ ሁለት የምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳደር ኃላፊዎችን ጭኖ ሲጓዝ በነበረው ተሽከርካሪ ላይ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ቢሊዳ ቀበሌ ላይ እገታ ተፈጽሟል። ከተፈጸመው እገታ ለማምለጥ ጥረት ያደረገ አሽከርካሪ በተተኮሰ ጥይት የተገደለ ሲሆን ሁለቱ ተጓዦች ማምለጡን ለማወቅ ተችሏል።
  12. ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ሰዓት አካባቢ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ጀጁ ወረዳ አርቦዬ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ቄያቸው እየተመለሱ እያለ በመንገድ ላይ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) ታጣቂዎች በአካባቢው ከሚገኘው ጫካ በመውጣት በከፈቱባቸው ተኩስ 4 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ 1 ሰው ደግሞ ለከፍተኛ አካል ጉዳት በመዳረጉ ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ ማገገሙን ኢሰመኮ አረጋግጧል።
  13. ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የክረምት ትምህርት ለመከታተል በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ከመነስቡ ወረዳ ወደ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጉዞ ላይ የነበረ 1 ሰው በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ብርመጂ ወረዳ ሀዋ ወንዝ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) ታጣቂ ቡድን አባላት ታግቶ ወደ ማይታወቅ ቦታ ተወስዶ ከ3 ቀናት በኋላ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. መለቀቁን ማረጋገጥ ተችሏል።
  14. ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ የሚንቀሳቀሱ የቅማንት ታጣቂዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ታጅበው ከጎንደር ከተማ ወደ ገንዳ ውሃ ከተማ እየሄዱ የነበሩ መኪኖች ውስጥ አብዛኞቹ ዋሊ ዳባ ቀበሌን እንዳለፉ ከኋላ የነበሩ አሽከርካሪዎችን በማስቆም 10 ሰዎችን (5 ሹፌሮች እና 5 ተሳፋሪዎች) አግተው ከወሰዱ በኋላ የአካባቢው ሽማግሌዎች ታጣቂዎችን በማወያየት ሁሉንም የታገቱ ሹፌሮች እና ተሳፋሪዎችን ማስለቀቃቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
  15. ነሐሴ 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በአማራ ክልል የሰሜን ጎንደር ዞን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት 3 ሠራተኞች ለጃን አሞራ ወረዳ የሚያገለግል አዲስ አምቡላንስ አስረክበው እና የሰብአዊ አገልግሎት አከናውነው ወደ ደባርቅ ከተማ በመመለስ ላይ እያሉ አርጅን ጅና ቀበሌ ጨነቅ አካባቢ ሲደርሱ ማንነታቸው ያልታወቁ 4 ሰዎች (2ቱ የታጠቁ) ከመኪና እየደበደቡ አስወርደውና አግተው በእግር የ2 ሰዓት መንገድ በማስጓዝ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ወደ ሚገኘው አምባ ራስ ተራራ እንደወሰዷቸው ኢሰመኮ አረጋግጧል። አጋቾች ሁሉንም የታገቱ ሰዎች ማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፍሉ ለየቤተሰቦቻቸው ስልክ እንዲደውሉ ሲጠይቁ አቶ ሆነልኝ ፋንታሁን የተባለው ታጋች ‘ባለቤቴ የጤና ችግር ስላለባት ትደነግጣለች ስልክ አልደውልም’ በማለቱ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበታል። የታጋቾች ቤተሰቦች እና የሥራ ባልደረቦች ገንዘብ አሰባሰበው 400,000 ብር ለአጋቾች ከተሰጠ በኋላ ታጋቾች ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የተለቀቁ ቢሆንም፤ አቶ ሆነልኝ ፋንታሁን በደረሰበት ድብደባና በእገታ የቆዩበት ቦታ በጣም ቀዝቃዛ በመሆኑ በነበረው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት ራሱን ስቶ ስለነበር በአምቡላንስ ወደ ደባርቅ ከተማ በመመለስ ላይ እያሉ ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ላይ ሕይወቱ እንዳለፈ የዐይን ምስክሮች አስረድተዋል። በተጨማሪም የታጋቾች የአንገት ሐብል፣ ልብሶች እና በኪሳቸው የነበረ ገንዘብ የተዘረፈ መሆኑን ኢሰመኮ አረጋግጧል።
  16. ነሐሴ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በአማራ ክልል ከሰሜን ወሎ ዞን ወደ ደቡብ ጎንደር በሚወስደው መንገድ የፋኖ ታጣቂዎች ነዳጅ ጭነው ወደ ነፋስ መውጫ ከተማ አቅጣጫ ሲጓዙ የነበሩ 2 ቦቴ መኪኖች ደብረ ዘቢጥ (ልዩ ስሙ ወርቅ ዋሻ) ከሚባል ቦታ በማስቆም አንድ ተሽካርካሪ ላይ የተጫነውን ነዳጅ ቀድተው መውሰዳቸውን፣ ሁለተኛውን ተሽከርካሪ ደግሞ ማቃጠላቸውን፣ የሁለቱም ቦቴ መኪኖች አሽከርካሪዎች ከመኪናው ቀድመው ወርደው ያመለጡ መሆኑን፤ እንዲሁም ነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌላ ቦቴ ተሽከርካሪ ጨጨሆ ላይ ሲደርስ ማቃጠላቸውን ኢሰመኮ ማረጋገጥ ችሏል።
    • የመንገድ መዘጋት እና በኬላዎች ላይ የሚደረጉ ቁጥጥሮች
  17. የደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማን ከምስራቅ ጎጃም መርጦ ለማሪያም ከተማ የሚያገናኘው መንገድ ከመጋቢት ወር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከጸጥታ ጋር በተያያዘ በመዘጋቱ እንዲሁም የአዴት-ሞጣ-ብቸና መንገድ ከሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ጀምሮ ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የተዘጋ በመሆኑ እና የኅብረተሰቡን መደበኛ እንቅስቃሴ ያስተጓጎለ መሆኑን ኢሰመኮ ለመረዳች ችሏል። በተመሳሳይ ከባሕር ዳር-ደብረ ማርቆስ መንገድ ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ተዘግቶ የነበረ በመሆኑ የኅብረተሰቡን እንቅስቃሴ ገድቦ ቆይቷል።
  18. በግንቦት እና በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከአማራ ክልል ለሥራ ጉዳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማና ዙሪያው ወደሚገኙ ወረዳዎች ከሚሄዱ ሰዎች መካከል የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መታወቂያ እያዩ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ብቻ በመያዝ በአሶሳ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 1 እና ወረዳ 2 ፖሊስ ጣቢያዎች እንዲሁም በሸርቆሌ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ የሚያስሩበት እና አስገድደው ወደመጡበት አከባቢዎች እንዲመለሱ የሚደረጉበት ሁኔታ እንደነበር በተደረጉ ክትትሎች ለማወቅ ተችሏል። ስለጉዳዩ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የመንግሥት ኃላፊዎች እነዚህ እርምጃዎች በየዓመቱ በበልግ (በእርሻ) ወቅት የሚወሰዱ ነገር ግን አሁን የሌሉ መሆኑን፤ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል እና በተለምዶ “ፋኖ” ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀላቀል የጸጥታ ስጋት እንዳይሆን ለማድረግ የሚወሰዱ መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል።
  19. በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ የሚንቀሳቀሱ የቅማንት ታጣቂዎች ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የታጀቡ የአፈር ማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ ሸቀጣሸቀጦች እና ሰዎችን ጭነው የሚሄዱ መኪኖችን ኬላ ዘርግተው ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲያስቆሙ በተነሳ ግጭት ታጣቂዎች በመንግሥት የጸጥታ አባላት ላይ ባደረሱት ጥቃት በርካታ ሹፌሮች እና ተሳፋሪዎችን እንደገደሉ እና 3 ሹፌሮችን አግተው ወስደው ከቀናት በኋላ እንደለቀቋቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን የሥራ ኃላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። በዕለቱ ግጭቱ ካቆመ በኋላ እንዲሁም ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም. የቅማንት ታጣቂዎች ወደ መቃ ቀበሌ ገብተዋል በሚል ምክንያት በታጣቂዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ በተወሰደ የተኩስ እርምጃ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በበኩላቸው በርካታ ሰዎችን እንደገደሉ ለማረጋገጥ ተችሏል።
    • የሰዓት እላፊ እገዳዎች
  20. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ቡለን፣ ድባጤ እና ወምበራ ወረዳዎች ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እንቅስቃሴና የጸጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ ከሰኔ ወር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ ሪፖርት እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በዞኑ ተዋቅሮ በሚገኘው ኮማንድ ፖስት ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 12፡00 ሰዓት የሰዓት እላፊ እንቅስቃሴ ገደቦች ተጥለው የሚገኙ በመሆኑና በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ነዋሪዎች እንደልባቸው መንቀሳቀስ የማይችሉ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል
  21. በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን የባቲ ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ምክር ቤት አንድ ግለሰብ ባልታወቁ ሰዎች መገደሉን ተከትሎ “የታጣቂዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር” በሚል ከነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ተግባራዊ የሚሆን የሰው እና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን ማረጋገጥ ተችሏል። የሰው እንቅስቃሴ ገደቡ ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት የሚጀምር ሲሆን፤ የባጃጅ እንቅስቃሴ ደግሞ ከቀኑ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ የተከለከለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የቀጠለው ይህ የእንቅስቃሴ ገደብ በነፍሰ ጡር እናቶች፣ ታማሚዎች እና በአጠቃላይ በነዋሪው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።
  22. በጋምቤላ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች በሞተር ሳይክል በመታገዝ በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተስፋፍተዋል በሚል ምክንያት ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ተወያይቶ ባሳለፈው ውሳኔ የሞተር ሳይክል ከምሽቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ መንቀሳቀስ እንደማይችል፣ የሰሌዳ ቁጥር ሳይኖራቸው የሚንቀሳቀሱ ሞተር ሳይክሎች እንዲወረሱ ውሳኔ ተላልፎ የነበረ ሲሆን ይህ ሪፖርት በተጠናቀረበት ወቅት እገዳው የተነሳ መሆኑን ኢሰመኮ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ማወቅ ችሏል።
  23. በመንግሥት አካላት የሚጣሉ የሰዓት እላፊ የእንቅስቃሴ ገደቦች፣ በመንግሥት የጸጥታና ሌሎች በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች መንገዶች ላይ የሚጣሉ ኬላዎችና የመንገድ መዝጋት እርምጃዎች እንዲሁም የመንገድ ደኅነት ባለመረጋገጡ የታጠቁ ኃይሎችን ጨምሮ በመንገዶች ላይ የሚፈጸሙ የእገታ፣ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ወንጀሎች ከመዘዋወር መብት ባለፈ የጥሰቱን ሰለባዎችና ቤተሰቦቻችውን ለበርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሚዳርጉ ናቸው። በእነዚህ ድርጊቶች ተጎጂ በሆኑ ሰዎች ላይ በቀጥታ ከሚደርሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪም በቤተሰብ ላይ የሚደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት፣ የሥነ ልቡና ጫና እንዲሁም በአጠቃላይ ማኅበረሰብ በሕግ ሥርዓት ላይ ያለውን እምነት የመሸርሸር አደጋ ኢሰመኮ አሳሳቢ ሆኖ አግኝቶታል።
  24. ከዚህ አንጻር ሰዎች በሕገ መንግሥቱ የተጠበቀላቸውን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል፤ የሚደረጉ የእንቅስቃሴ ክልከላዎች፣ ያለአግባብ የሚጣሉ ኬላዎች እንዲሁም ሰላም እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ተብለው የሚወሰዱ የእንቅስቃሴ ገደብ እርምጃዎች በጥብቅ አስፈላጊና ተመጣጣኝ መሆናቸውን፣ ከመጠን በላይ እንቅስቃሴን የሚገድቡ፣ ከፍተኛ መስተጓጎልን የሚያስከትሉ እና የአስፈላጊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት የሚያናጉ አለመሆናቸውን የክልል እና የፌዴራል አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት ሊያረጋግጡ ይገባል።
  25. መንግሥት ሰዎች በሰላም እና ነጻነት ወጥተው መግባት እንዲችሉ በመንገዶች ላይ በታጠቁ ኃይሎች ለሚደርሱ ጥቃቶች፣ እገታዎች፣ የንብረት ዘረፋዎች እና ውድመቶች ተገቢውን ትኩረት በመስጠትና በአካባቢው ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር በቅርበት በመሥራት ችግሮች ሲከሰቱ በወንጀሉ የተሳተፉ ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ተገቢ የሆኑ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል።
  26. ኢሰመኮ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የጸጥታና ደኅንነት ሥጋት፣ ዘርፈ ብዙ ወንጀሎች፣ በመንግሥትና በሕዝብ አገልጋዮች ላይ በሚፈጸም ጥቃትና ግድያ ምክንያት የወንጀል መከላከል እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሥራ ፈታኝ መሆኑን የሚገነዘብ ቢሆንም ማናቸውም ሕግና ሥርዓትን የማስከበር፣ የወንጀል መከላከልና አጥፊዎችን ተጠያቂ የማድረግ እርምጃ ሙሉ በሙሉ ሕግና ሥርዓትን በተከተለና ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ ብቻ ሊመራ ይገባል።
  27. የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡ የሰዎችን የመዘዋወር መብት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን ለመከላከልና በአስቸኳይ እልባት ለመስጠት መንግሥት በተደጋጋሚ ጥቃት፣ እገታ፣ የንብረት ዘረፋና እና ውድመት የሚፈጽምባችው መንገዶች ላይ በቂ የጸጥታ ኃይል ሊያሰማራ፣ በመንግሥት የጸጥታና የአስተዳደር አካላት ለተራዘመ ጊዜያት የተዘጉ መንገዶችና የተጣሉ የመንገድ ላይ የፍተሻ ኬላዎች አስፈላጊነታቸውን እንደገና በመፈተሽ የማስተካከያ እርምጃ ሊወስድ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለወደፊት የሚወሰዱ እርምጃዎች የሰብአዊ መብቶች መርሖች የሆኑትን የጥብቅ አስፈላጊነትና የተመጣጣኝነት መስፈርቶች የሚያሟሉ መሆኑን ሊያረጋግጥ፣ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎችና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ የተሟላ ማጣራት በማድረግ ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ እንዲሁም በድርጊቶቹ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች ፍትሕ ሊያሰፍን ይገባል” በማለት አሳስበዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ከመንግሥት ውጪ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች የነዋሪዎችን ሰብአዊ መብቶች ከሚጥሱና ከወንጀል ተግባራት በተለይም በሰዎች የመንቀሳቀስ መብትና ተንቀሳቅሰው የዕለት ከዕለት ተግባራት በማከናወን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸው እርምጃዎችን ከመውሰድ እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።