የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ባለ 50 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው ይህ የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተጨማሪነት የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ በዝርዝር በማተኮር በበጀት ዓመቱ የለያቸውን አበረታች እመርታዎች፣ አሳሳቢ ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦችን አካቷል፡፡
ሪፖርቱ የተዘጋጀው ኢሰመኮ በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸውን ክትትሎችና ምርመራዎች፣ የአካል ምልከታዎች፣ የቀረቡ አቤቱታዎች፣ የሕግና የፖሊሲ ግምገማዎች፣ ምክክሮች እንዲሁም የውትወታ ሥራዎችን መሠረት በማድረግ ነው።
በግጭት እና ድኀረ ግጭት ወቅት የሴቶች እና የሕፃናት የጤና መብቶች፣ በግጭት ዐውድ ውስጥ ከጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች የመጠበቅ መብት፣ በድኀረ ግጭት ወቅት የአካል ጉዳተኛ ሴቶች እና ሕፃናት መብቶች፣ የተፈናቃይ ሴቶች እና ሕፃናት መብቶች፣ የትምህርት መብት፣ ሕፃናትና ታዳጊዎች ከጥቃት እና ከጉልበት ብዝበዛ የመጠበቅ መብቶች፣ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝ፣ ከእናቶቻቸው ጋር በማቆያ/በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሕፃናትን ጨምሮ የሴት ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች አያያዝ፣ የወላጆቻቸውን እንክብካቤ ማግኘት ያልቻሉ ሕፃናት እንዲሁም በሰፋፊ የእርሻ ልማቶች ውስጥ የሚሠሩ የሴቶች እና የታዳጊዎች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ በዋናነት ትኩረት ያደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው።
በሪፖርት ዘመኑ ከተለዩት አበረታች እመርታዎች መካከል አማራጭ የሕፃናት ድጋፍና ክብካቤ መመሪያ ቁጥር 976/2023 ጸድቆ ከጥር ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉ፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሃዲያ ዞን ሻሸጎ፣ ሶሮና ምዕራብ ሶሮ ወረዳዎች የገና በዓልን አስታኮ ሊፈጸሙ የታቀዱ የሴት ልጅ ግርዛቶች እንዲቀሩ መደረጉ፣ በአፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋር የታሰሩ ሴት ተጠርጣሪዎች በልዩ ሁኔታ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር የሚለቀቁበት አሠራር መኖሩ፣ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከታራሚ እናቶቻቸው ጋር ያሉ ሕፃናት የማቆያ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ፣ በተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች ለሴት ታራሚዎችና ተከሳሾች በእርግዝና ወቅት እና በወሊድ ጊዜ የሚደረገው የሕክምና ድጋፍና ክትትል እንዲሁም በአፋር ክልል በአብአላ ፖሊስ ጣቢያ የሴት ተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ መሻሻል ማሳየታቸው ይገኙበታል።
በተጨማሪም በሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃቶች አንዱ የወንጀል ምርመራ የሚደረግበት እና ክስ የሚቀርብበት ጉዳይ ሆኖ በግልጽ መቀመጡ እንዲሁም ሴቶችን ጨምሮ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሽግግር ፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚሳተፉበት እና ከጥቃት የሚጠበቁበት አማራጮች መካተታቸው በመልካም እመርታነት በሪፖርቱ ተካተዋል።
በሌላ በኩል በግጭት ውስጥ ባሉ እና በትጥቅ ግጭት ውስጥ በቆዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖች በተለያየ ጊዜ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሴቶችና ሕፃናትን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃቶች መጋለጣቸው፤ በግጭት ዐውድ ውስጥ በቆዩት አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ትግራይ ክልሎች በቂ መልሶ የማቋቋም ሥራ ባለመከናወኑ በሕክምና ተቋማት የውሃና ኤሌክትሪክ፣ የሕክምና ቁሳቁስ፣ የአምቡላንስ፣ የመድኃኒት፣ የክትባትና የምግብ አቅርቦት ውስንነት ምክንያት እናቶችና ጨቅላ ሕፃናት በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ፣ በድንገተኛ ወሊድ ወቅት ሊያገኙ የሚገባቸውን መሠረታዊ አገልግሎቶች እያገኙ ባለመሆኑ የእናቶችና ሕፃናት ሞት እየጨመረ መምጣቱ፣ እንዲሁም በሀገሪቱ በቀጠሉ ግጭቶች እና በተፈጠረው የደኅንነት ሥጋት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው በሪፖርቱ በአሳሳቢነት ተጠቅሰዋል፡፡
ግጭቶች እና ግጭቶቹ በፈጠሩት ሥጋት ምክንያትም የሕፃናት ፓርላማ አባላት እና አመራሮች በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት አለመቻላቸው፤ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ የሚያድጉ ሕፃናት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ አለመሻሻል እና ኢሰመኮ ሰጥቷቸው የነበሩ ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ አለመደረጋቸው፤ በአፋር፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚጣሉ ጨቅላ ሕፃናት ቁጥር መጨመር እና በክልሎቹ በቂ አማራጭ የቤተሰብ እንክብካቤ አገልግሎት አለመኖር፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወንጀል ነገር ውስጥ ተገኝተው በተሐድሶ (ማቆያ) ማእከል ውስጥ ያሉ ሕፃናት ለተለያዩ ጥቃቶች መጋለጣቸው እና የተሟላ የአገልግሎት አቅርቦት አለመኖር፣ ከእናቶቻቸው ጋር ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ከሆኑ እና በወንጀል ከተፈረደባቸው ሰዎች ጋር አንድ ላይ መያዛቸው እና ምቹ የሆነ አገልግሎት የማይቀርብላቸው መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በተጨማሪም በሰፋፊ የእርሻ ልማቶች ውስጥ የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች እና ታዳጊዎች ምቹና ፍትሐዊ የሥራ ሁኔታዎችን የማግኘት መብቶቻቸው ያልተጠበቀላቸው መሆኑ እና በተወሰኑ የእርሻ ልማቶች ውስጥ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ተቀጥረው እንደሚሠሩና በጤናቸው፣ በአካላቸው እና በትምህርታቸው ላይ ጉዳት ለሚያስከትል የጉልበት ብዝበዛ እና ሌሎች ተያያዥ ጥቃቶች መጋለጣቸው በሪፖርቱ ተገልጿል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ፣ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በቀጠሉ ግጭቶች፣ በድኅረ ግጭት ሁኔታ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች፣ በመፈናቀል እና በድርቅ ሳቢያ የጤና፣ የትምህርት እንዲሁም ከሁሉም ዐይነት ጥቃቶች የመጠበቅ መብቶች ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል። አክለውም የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲሁም በሕግና በተቋማዊ የአሠራር ክፍተቶች ረገድ በኢሰመኮ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ ለሴቶች እና ሕፃናት መብቶች የተሻለ ጥበቃ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡