የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለ5ተኛ ጊዜ በሚያካሂደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ለዕይታ የሚቀርቡ አጫጭር ፊልሞች እና ፎቶግራፎች ውድድር እስከ ኅዳር 3 ቀን 2018 ዓ.ም. ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ መገለጹ ይታወቃል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሥራዎቻቸውን ያቀረቡ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም፣ ለተጨማሪ ሰዎች ዕድል መስጠት በማስፈለጉ እና በውድድሩ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ባለሙያዎች የጀመሯቸውን ሥራዎች ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው ለውድድር የሚቀርቡ ሥራዎችን የማስገቢያ ጊዜው እስከ ኅዳር 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ተራዝሟል።
ቀለል ያሉ የቴክኒክ መስፈርቶች እንዲሁም አበረታች ሽልማቶችን ያካተተው ውድድሩ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የሚካሄድ ሲሆን ፍላጎቱ ያለው ማንኛውም ሰው እንዲሁም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚሳተፉበት ነው።
የፎቶግራፍ ውድድሩ በትምህርት መብት ላይ የሚያተኮር ሲሆን፣ የአጫጭር ፊልሞች (በጀማሪዎች እና ባለሙያዎች ምድብ) በነጻነት መብት ላይ ያተኮረ ነው።
በየውድድር ዘርፉ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ይዘው ለሚያጠናቅቁ አሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማቶች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ለሁሉም ተሳታፊዎች የዕውቅና የምስክር ወረቀት ይሰጣል።
ሽልማቶች
| ደረጃ | የፎቶግራፍ ውድድር አሸናፊዎች | የአጫጭር ፊልሞች ውድድር አሸናፊዎች – የጀማሪዎች (5-6 ደቂቃ) | የአጫጭር ፊልሞች ውድድር አሸናፊዎች – ባለሙያዎች (10-15 ደቂቃ) |
| አንደኛ | 75 ሺህ | 100 ሺህ | 125 ሺህ |
| ሁለተኛ | 50 ሺህ | 75 ሺህ | 100 ሺህ |
| ሦስተኛ | 25 ሺህ | 50 ሺህ | 75 ሺህ |
ኢሰመኮ ወጣቶች እና ታዳጊዎች እንዲሁም የኪነጥበብ ዘርፍ ባለሞያዎችን ጨምሮ በፎቶግራፍ እና በአጫጭር ፊልም ሥራዎች ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በውድድሩ እንዲሳተፉ እና ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
——–
የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልም ውድድሮች የተሳትፎ ቅጽ፣ በሁለቱም ዘርፍች የተቀመጡ የውድድር የቴክኒክ መስፈርቶች እና የውድድሩ አጠቃላይ መመሪያዎችና ደንቦች ይመልከቱ።