የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢትዮጵያ ዐይነ ሥውራን ብሔራዊ ማኅበር ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የማራካሽ ስምምነትን የአማርኛ ትርጉም ኅትመት የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የማራካሽ ስምምነት ሰኔ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. በሞሮኮ ማራካሽ ከተማ የተፈረመ ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው። ይህ ስምምነት ዐይነ-ሥውራን እና የሕትመት ውጤቶችን መደበኛ በሆነ የንባብ ስልት ማንበብ ለማይችሉ አካል-ጉዳተኞች፣ የቀለም ኅትመት ውጤቶችን የአእምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት ፍቃድ ሳያስፈልጋቸው እንዲሁም የቅጂ ባለመብቶችን የባለቤትነት መብት በማይጋፋ መልኩ በተደራሽና አማራጭ ቅርጽ በማመቻቸት እንዲጠቀሙ የሚፈቅድ ነው፡፡
የማራካሽ ስምምነት ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መካከል አንዱ ሲሆን በሕገ-መንግሥቱ መሰረትም የሀገሪቱ ሕግ አካል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) አንቀጽ 6(8) መሰረት ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የመተርጎም እና የማሰራጨት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ኅትመቱን የኢትዮጵያ ዐይነ ሥውራን ብሔራዊ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰብስቤ ይልማ ለኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ አስረክበዋል፡፡ ለርክክብ በተሰናዳው መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ዐይነ ሥውራን ብሔራዊ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን፣ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የዩኤስኤድ ፍትሕ ፕሮጀክት ወኪል እንዲሁም ሌሎች በትርጉም ሂደቱ ላይ የተሳተፉና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡ ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ በዝግጅቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ዐይነ ሥውራን ብሔራዊ ማኅበር ኮሚሽኑ የማራካሽ ስምምነትን ለመተርጎም የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በማጤን በጋራ ለመሥራት ያደረገውን ተነሳሽነት አድንቀው፤ “የማራካሽ ስምምነት በአማርኛ ቋንቋ መተርጎሙ የማስፈጸሚያ ሕግ ማውጣትን ጨምሮ በስምምነቱ ተግባራዊነት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል” ብለዋል፡፡