የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን፣ አንቀጽ 12
አባል ሀገራት የማንኛውንም ሰው ሊደረስበት የሚችለውን ከፍተኛውን የአካል እና የአእምሮ ጤና ደረጃ የማግኘት መብት ዕውቅና ይሰጣሉ። ይህን መብት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ አባል ሀገራት የሚወስዷቸው እርምጃዎች፡-
- ከተወለዱ በኋላ የሚሞቱ ጨቅላ ሕፃናትን ቁጥር እና ሞተው የሚወለዱትን ምጣኔ ለመቀነስ እንዲሁም የሕፃናትን ጤናማ ዕድገት ለማመቻቸት፤
- የሁሉንም የአካባቢና የኢንዱስትሪ ንጽሕና ዘርፎች ለማሻሻል፤
- ወረርሽኝን፣ አካባቢያዊና ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚመጡ ወይም ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል፣ ለማከም እና ለመቆጣጠር፤
- በሕመም ጊዜ ሁሉንም የሕክምና አገልግሎት እና ክትትል አቅርቦት መኖሩን የሚያረጋግጡ ሁኔታዎችን ለመፍጠር አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች ሊያካትቱ ይገባል።