የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በክልሉ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አጠቃላይ ምልከታ ላይ ጥቅምት 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ ከተማ ምክክር አካሂዷል። ምክክሩ ኢሰመኮ በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት ባደረጋቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትሎች እና ምርመራዎች በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ በመወያየት አሳሳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ለመወትወት ያለመ ነው።



በምክክሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ጥላሁን ከበደ፣ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አዳማ ትንዳዬ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክቡር አንዷለም አምባዬ እንዲሁም የክልሉ ፍትሕ እና ጸጥታ ቢሮ፣ ፖሊስ እና ማረሚያ ኮሚሽን፣ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር እና የሌሎች ተቋማት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።



የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ለውይይት መነሻ ባቀረቡት ገለጻ በክልሉ በዳሰነች ወረዳ ያሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የመብት አያያዝ ሁኔታ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚፈጸም ግድያ እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲሁም የሕዳጣን መብቶችን ማእከል ያደረጉ ግኝቶችን አብራርተዋል። የሽግግር ፍትሕም ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ኢሰመኮ ከክልሉ መንግሥት ጋር በትብብር ሊሠራ የሚችልባቸው የዐቅም ግንባታ እና የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ሥልጠና ሥራዎች ተዳስሰዋል።
የክልሉ ልዩ ልዩ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች በበኩላቸው በኢሰመኮ የተለዩ ግኝቶች ነባራዊ ሁኔታውን የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቁመው የክልሉ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ችግሮችን በመከታተል ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ሕግ የማስከበር ተግባሩን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ጥላሁን ከበደ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በክትትል እና በምርመራ የለያቸው ግኝቶች እና የሚሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዘን ለማሻሻል በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን አመልክተው ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ እና በሕግ አግባብ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የሰብአዊ መብቶች ከመጣሳቸው በፊት መከላከል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው “ስለሰብአዊ መብቶች የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ የሚያጎለብቱ እና ለሚፈጸሙ የመብቶች ጥሰት ተጠያቂነት በሚያሰፍኑ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል” ብለዋል። አክለውም ኢሰመኮ ነጻነቱን እና ገለልተኛነቱን ጠብቆ ከክልሉ መንግሥት ጋር የመረጃ ልውውጥን እና የተጀመሩ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።