የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሚያካሄደውን 5ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር (National High Schools Human Rights Moot Court Competition – NHSHRMCC) መጀመሩን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ ጥር 21 እና 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። በውይይቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር፣ የሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችና እና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ኢሰመኮ በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያካሂደው የሁለተኛ ደርጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት የክርክር ሥርዓትን የሚከተል ውድድር ሲሆን በተመረጠ ምናባዊ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ በመመሥረት ተማሪዎች የአመልካች እና ተጠሪ ወገንን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር ያደርጉበታል። ውድድሩ በተወዳዳሪ ተማሪዎች እና በትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ዘንድ የሰብአዊ መብቶች ዕውቀትን እና ክህሎትን ለማጎልበት፤ አመለካከትን እና ባሕርይን ለመቅርጽ ያለመ ነው። ውድድሩ በክልል እና ከተማ አስተዳደር ደረጃ በትምህርት ቢሮዎች አስተባባሪነት ተጀምሮ ፍጻሜውን በአዲስ አበባ ከተማ የሚያደርግ ሲሆን ምናባዊ ጉዳዩም ወቅታዊ እና ለተማሪዎች ቅርብ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።

በመድረኩ በ2016 ዓ.ም. የተካሄደው 4ኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር ሂደት የተገመገመ ሲሆን ውድድሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን እና ተግዳሮቶችን በመለየት ውይይት ተደርጓል። እንዲሁም ባለፉት ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የነበሩ እና በአሁን ወቅት በዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት በመከታተል ላይ የሚገኙ 3 ተማሪዎች የነበራቸውን መልካም ተሞክሮዎች አጋርተዋል። በተጨማሪም ውድድሩ የሚመራባቸውን መመሪያዎች እንዲሁም የውድድሩ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ በማድረግ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ማበልጸጊያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ቴዎድሮስ ሸዋረገጥ በአዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት የግብረገብ እና የሥነዜጋ ትምህርቶች መካተታቸው ቀጣዮ ትውልድ እንደ ራስን ማወቅ፣ ሰብአዊነት፣ መከባበር፣ እኩልነት፣ ኃላፊነት እና በመሳሰሉ ዕሴቶች እንዲታነጽ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድሩ በተማሪዎች፣ በመምህራን እንዲሁም በማኅበረሰቡ ዘንድ ተጽዕኖ ለመፍጠር አስተዋጽዖው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በበኩላቸው ኢሰመኮ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እና እንዲስፋፉ የምስለ-ችሎት ውድድርን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አስታውሰው፣ ቀደም ባሉ ውድድሮች ከአካታችነት አንጻር የሴቶችን እኩል ተሳትፎ ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል። ነገር ግን አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን በማሳተፍ ረገድ ክፍተት መታየቱን ጠቁመው በዘንድሮው ውድድር አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን በተወዳዳሪነት ወደ ውድድሩ ለማመጣት የሚመለከታቸው ሁሉ በተለይም ትምህርት ቢሮዎች እና ትምህርት ቤቶች ተገቢውን ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በመጨረሻም የዚህ ዓመት ውድድር ምናባዊ ጉዳይ “ለልማት ሲባል በግዳጅ ከመፈናቀል ጋር የተያይዙ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች” ላይ እንደሚያተኩር ይፋ አድርገዋል።