በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት እ.ኤ.አ. በየዓመቱ ታኅሣሥ 10 ቀን የሚውለውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ለማሰብ በ2014 ዓ.ም. የተጀመረው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል 5ኛ ዙር፣ ታኅሣሥ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአዲስ አበባ የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር አዳራሽ በይፋ ተጀምሯል። የዘንድሮው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በኢሰመኮ የ2017 ዓ.ም. ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት አሳሳቢ ተብለው በተለዩት በነጻነት መብት እና ትምህርት በማግኘት መብቶች ላይ ያተኮረ ነው።
ዓመታዊው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዋነኛ ዓላማ ዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶች ቀን ለማሰብ፣ የኪነ-ጥበብን እና የሰብአዊ መብቶችን ትስስር ለማጠናከር፣ ኪነ-ጥበብ “ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት” የሚለውን የኢሰመኮ ራዕይ ለማሳካት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማስታወስ እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ በተለያዩ ዘርፎች የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችንና ተቋማትን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤን ማስፋፋት ነው።
ባለፉት 4 ተከታታይ ዓመታት በተካሄዱት የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሎች በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አጫጭርና የሙሉ ሰዓት ፊልሞች፣ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን የሚዳስሱ ዘጋቢ ፊልሞች፣ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች፣ ቲአትር እንዲሁም ፎቶግራፎችና ሥዕሎች ቀርበዋል። በዘንድሮው ፊልም ፌስቲቫል የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልም (በጀማሪ እና ባለሙያ ዘርፍ) ሥራዎች ለውድድር ቀርበዋል።
ውድድሩ ጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በይፋ ተጀምሮ እስከ ኅዳር 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ለተወዳዳሪዎች ክፍት ሆኖ የቆየ ሲሆን 75 ተሳታፊዎች የኪነጥበብ ሥራቸውን ለኢሰመኮ በመላክ ተወዳድረዋል። ትኩረቱን “ትምህርት የማግኘት መብት” ላይ ባደረገው የፎቶግራፍ ውድድር 50 ፎቶግራፎች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን፣ “የነጻነት መብት” ላይ ባተኮረው ውድድር ደግሞ 22 በጀማሪዎች እንዲሁም 3 በባለሙያዎች የተሠሩ አጫጭር ፊልሞች ቀርበዋል።
ታኅሣሥ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የፌስቲቫሉ መክፈቻ ዝግጅት የተመረጡ ፎቶግራፎች በዐውደ ርዕይ መልክ ለታዳሚዎች ለዕይታ ቀርበዋል። በተጨማሪም የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልሞች ውድድር አሸናፊዎች ይፋ ተደርገዋል። በዚህም መሠረት፦
በፎቶግራፍ ውድድር፦
1ኛ. ኤደን ቀለም (“እኔስ”)
2ኛ. ያዕቆብ በለጠ (“ወደ ዕውቀት መድረስ”)
3ኛ. ቃልኪዳን አንዷለም (“ተስፋ?”)
በአጫጭር ፊልሞች (ጀማሪ ዘርፍ) ውድድር:-
1ኛ. አስመላሽ ተፈራ (“ወርቃማው ሕግ”)
2ኛ. ታምራት ግርማ (“The Butter Fly Lesson”)
3ኛ. ማሩፍ እንደራሴ (“ክብ ድል”) አሸናፊ ሆነዋል፡፡
በመርኃ ግብሩ ለተገኙ የውድድሩ ተሳታፊዎች የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።
በፌስቲቫሉ በልዩ ሁኔታ ለ5ተኛው ዙር ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል የተመረጠ ‘‘ጀቢና’’ የተሰኘ ፊልም ለዕይታ ቀርቧል።
በዝግጅቱ ላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና በሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሠሩ ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የውጪ ሀገራት ተወካዮች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ ተወዳዳሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል፡፡ ፌስቲቫሉ ከታኅሣሥ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እስከታኅሣሥ ወር መጨረሻ በአርባ ምንጭ፣ አሶሳ፣ ባሕር ዳር፣ ቦንጋ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ ሃዋሳ፣ ጅግጂጋ፣ ጅማ፣ መቀሌ እና ሰመራ ከተሞች ተካሂዶ ይጠናቀቃል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሀኑ አዴሎ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን ሲታሰብ፣ በሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ ዕውቅና የተሰጠውን የሰው ልጆች ሁሉ ነጻ እንዲሁም እኩል ክብርና መብቶች ያሏቸው ሆኖ መወለድን በማስታወስ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል። አክለውም ለሰብአዊ መብቶች መከበርና መስፋፋት የመንግሥት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበረሰቡ እና የሚዲያው ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ መብቱን እና ግዴታውን በሚገባ ተረድቶ፣ በመብቶቹ መጠቀም እና የሌሎች ሰዎች መብቶችን ማክበር እንደሚገባው አመላክተው፣ ለዚሁ ዓላማ የኪነጥበብ እና የፈጠራ ሥራዎችን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።