የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በተለያዩ ከተሞች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር በመዋል ላይ የሚገኙ ሰዎች ሁኔታና የአያያዝ ሂደት እንደሚያሳስበው ገለጸ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሰዎች ከስራ ቦታቸው፣ ከመኖሪያ ቤታቸው እና ከመንገድ ላይ ጭምር በቁጥጥር ስር ውለው በተለያዩ የከተማዋ ፖሊስ ጣቢያዎች ተይዘው እንደሚገኙ አረጋግጧል፡፡
ምንም እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራሉ ተብለው ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠሩ ሰዎችን” ይዞ የማቆየት ሥልጣን ለሕግ አስከባሪ አካላት ቢሰጥም፤ ኮሚሽኑ በክትትሉ እንዳረጋገጠው እስሩ ማንነትን/ብሔርን መሰረት ባደረገ መልኩ በሚመስል ሁኔታ መከናወኑ፣ በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች የቤተሰብ ጥየቃ፣ ልብስ እና ስንቅ ማቀበል መከልከሉ እና እስሩ ሕጻናት ልጆች ያሏቸውን እናቶች አረጋዊያን ጭምር ያካተተ መሆኑ እጅግ ያሳስበዋል፡፡
ኢሰመኮ የሕግ አስከባሪ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና መመሪያዎቹን በሥራ ላይ ሲያውሉ እና ሲያስፈጽሙ የሕጋዊነት፣ የጥብቅ አስፈላጊነትና ተመጣጣኝነት እንዲሁም ከመድልዎ ነፃ መሆን የሚሉትን የሰብአዊ መብት መርሆዎችን ባከበረ መልኩ ሊሆን ይገባል። የሕግ አስከባሪ አካላት በማንኛውም ሁኔታ ሊገደቡ የማይችሉ ሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር፣ ተግባራቶቻቸውንም በከፍተኛ የሙያ ሥነምግባር በመመራት የማከናወን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እንዲሁም በተለይም አረጋውያንን፣ የሕጻናት ልጆች እናቶች እንዲሁም የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን ጨምሮ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አያያዝ በተመለከተ ፈጣንና ልዩ የማጣራት አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል።
ኢሰመኮ በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ወቅት ሰብአዊ መብቶችን የሚከታተል መሆኑንና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለኮሚሽኑ የክትትል ተግባራት ትብብር የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ለማስታወስ ይወዳል፡፡