የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ሁኔታ የተመለከተ ዓመታዊ ባለ 29 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ላይ በማተኮር የታዩ መልካም እመርታዎች፣ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አሳሳቢ ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦችን አካቷል።
ሪፖርቱ ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ሲሆን ኮሚሽኑ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ካከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራዎች፣ ጥናቶች፣ የውትወታ ሥራዎች፣ በግለሰቦች ከቀረቡ አቤቱታዎች፣ ከልዩ ልዩ የምክክር መድረኮች ላይ የተገኙ ግብአቶችን እና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን በማጠናቀር የተዘጋጀ ነው።
በሪፖርት ዘመኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በባለሦስት እና አራት እግር አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) ላይ ያሳለፈውን የእገዳ ውሳኔ ተከትሎ የኢሰመኮን ምክረ ሐሳቦች በመቀበል ለጉዳዩ እልባት መሰጠቱ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሊ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ በተደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት በኮሚሽኑ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ላይ በተለይም የዘላቂ መፍትሔ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን በተመለከተ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸው እና የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞች መብቶች አተገባበር እየተሻሻለ መምጣቱ በመልካም እመርታነት በሪፖርቱ ተካተዋል። በተጨማሪም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም በፌዴራል መንግሥት ይፋ የተደረገው “የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም” እና እነዚህን ተቋማት ወደ ነበሩበት ለመመለስ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችም ተጠቃሽ ናቸው።
በሌላ በኩል፣ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ ችግር እና እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት፣ ሊደረስበት የሚችል ከፍተኛ አካላዊና አእምሯዊ ጤና የማግኘት፣ ትምህርት እና መጠለያ የማግኘት፣ የመሥራት፣ ከሚኖሩበት ቦታ ያላግባብ በኃይል ያለመፈናቀል እና ንብረት የማፍራት መብቶችን ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው በአሳሳቢነት ከተለዩ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸውም በላይ ወቅቱ የግብርና ሥራ ቅድመ ዝግጅት የሚደረግበት የነበረ በመሆኑ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የግብርና ሥራውን እንዳይሠራ እና መደበኛ ሕይወቱን እንዳይመራ አድርጎታል። ግጭቱ ይህ ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ወቅትም የቀጠለ እና እልባት ያልተበጀለት በመሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሱ መባባሱ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች፤ የቤት እንስሳትና የንብረት ዝርፊያዎች፣ ቤቶችን የማቃጠልና ነዋሪዎችን በኃይል ማፈናቀል እና ቤተ-እምነቶችን ማቃጠል ምክንያት ኅብረተሰቡ በአካባቢው ተረጋግቶ የዕለት ተዕለት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወቱን እንዳይመራ ማድረጉንና በርካታ ሰዎች ያለመጠለያ እንዲኖሩ፤ የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኙ እና ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ ምክንያት እንደሆነ በሪፖርቱ ተብራርቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጸጥታና ደኅንነት ሥጋት በሚል እና በሌሎች ምክንያቶች የንግድና የመኖሪያ ቤቶች በማፍረስ ሂደት ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አካል ጉዳተኞች ሳይቀር የንግድ ቤቶቻቸው ያላግባብ እንዲፈርሱ መደረጉና ንብረታቸው መወሰዱ በገቢያቸውና በኑሯቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
በኦሮሚያ፣ በሶማሊ እና በተለያዩ የደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ድርቅ በመከሰቱ የሕብረተሰቡ መተዳደሪያ የሆኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቤት እንስሳት ሞተዋል፤ ነዋሪዎችም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። በመንግሥት በኩል ለችግሮቹ መፍትሔ ለማፈላለግ የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረጉም የቅድመ መከላከል ሥራ በበቂ ሁኔታ ባለመተግበሩ ችግሩን የከፋ እንዲሆን እንዳደረገው በሪፖርቱ ተጠቁሟል። የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በ2015 ዓ.ም. በኮሚሽኑ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን ከመተግበር ረገድ አበረታች ተግባራት መስተዋላቸውን ገልጸው የትምህርት፣ የጤና፣ ንብረት የማፍራት፣ በቂ በሆነ የኑሮ ደረጃ የመኖር፣ የሥራና ተያያዥ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች እንዲከበሩ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያ ማድረግ እንዲሁም ጠንካራ የክትትልና የድጋፍ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።