የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን፣ በቆላ ሻራ ቀበሌ ውስጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች (የክልሉ ፖሊስ አባላት) እና በቀበሌው ነዋሪዎች መካከል የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በተከሰተው ግጭት እና የጸጥታ መደፍረስ የደረሰውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሁኔታ በሚመለከት ከነሐሴ 22 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በአካባቢው በመገኘት ጭምር ምርመራ አድርጓል፡፡ በዚህም የሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ኮሚሽኑ ምርመራውን ለማከናወን ከተጎጂዎች፣ ከዐይን ምስክሮች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ በፖሊስ ጣቢያ ተይዘው ከነበሩ ተጠርጣሪዎች፣ በተለያዩ መዋቅሮች ሥር ከሚገኙ የመንግሥት የአስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የትምህርት መዋቅር ኃላፊዎች ጋር ቃለ መጠይቆችን እና የቡድን ውይይቶችን አድርጓል፡፡ ለምርመራው አግባብነት ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎችን ከሆስፒታል፣ ከከተማ አስተዳደር ተቋማት እና ከተጎጂዎች አሰባስቧል፣ እንዲሁም ከክስተቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቦታዎች ላይ ኮሚሽኑ በአካል ምልከታ አድርጓል።
ከጥር ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ወራት በቆላ ሻራ ቀበሌ እና በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር መካከል ያለው አስተዳደራዊ ግንኙነት ላይ ችግር መፈጠሩን ተከትሎ፤ የቆላ ሻራ ቀበሌ ነዋሪዎች የቀበሌውን የሚሊሻ አባላትን፣ የአካባቢው ወጣቶችን እና የተወሰኑ ሽማግሌዎችን በመመልመል የቀበሌውን ጸጥታ እንዲያስጠብቁ እና አስተዳደራዊ ሥራዎችን እንዲሠሩ ኃላፊነት መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአንጻሩ የክልሉ የአስተዳደር እና የጸጥታ አመራሮች ለኮሚሽኑ እንደገለጹት የቆላ ሻራ ቀበሌን የጸጥታ እና የአስተዳደር መዋቅር የተቆጣጠሩ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የተመደቡ የአስተዳደር እና የጸጥታ አመራሮች ወደ ቀበሌው እንዳይገቡ በማድረጋቸው ምክንያት ቀበሌውም ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ሆኖ መቆየቱንና የጸጥታ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና እና ሌሎች የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት መቋረጡን ያስረዳሉ።
ከዚህ በታች በተያያዘው የኢሰመኮ ምርመራ ዝርዝር ሪፖርት እንደተመለከተው፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሦስት ያልታጠቁ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሆነ ግድያ የፈጸሙና ያሰፈጸሙ፤ በቁጥጥር ሥር በዋሉ ሰዎች ላይ ድብደባ የፈጸሙ እንዲሁም በሰዎች ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ የመንግሥት የጸጥታ አባላት እና ሌሎችም ሰዎች ላይ አስፈላጊ የሆነውን የተሟላ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፤ እንዲሁም ለሟቾች ቤተሰቦች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እንዲሁም ንብረታቸው ለወደመባቸው ሰዎች፣ ለደረሰባቸው ጉዳት ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ እንዲከፈል ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ተጠያቂነትን ከማረጋገጥና የተጎዱትን ከመካስ በተጨማሪም ለዚህና ተመሳሳይ ግጭቶች ምክንያት የሆነው የአካባቢ አስተዳደር መዋቅር ጥያቄና ውዝግብ ነዋሪዎችን ተዓማኒ በሆነ መንገድ ባሳተፈ ሰላማዊ ውይይት አፋጣኝ መፍትሔ ይሻል” ብለዋል፡፡
ዝርዝር የምርመራው ግኝቶች ከዚህ በታች ተያይዟል ⬇️
በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. በቆላ ሻራ ስለተፈጠረው ሁኔታ ዝርዝር
ዳራ
የቆላ ሻራ ቀበሌ በአማካኝ ግምት ወደ 20 ሺህ የሚገመቱ ነዋሪዎች ያሉትና በጋሞ ዞን፣ አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ሥር ይተዳደር የነበረ ሲሆን፤ በተለይም በሙዝ ምርት የሚታወቅ አካባቢ ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም. በቀድሞ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል (በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ) የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ አማካኝነት የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር መዋቅራዊ ፕላን ክለሳ ሲደረግ፣ ቆላ ሻራ ቀበሌን ጨምሮ ቦላ ጉርባ፣ ጊዞላ እና ጫኖ ዶርጋ የተባሉ አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ሥር የነበሩ በአጠቃላይ አራት ቀበሌዎች፣ ወደ አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር መዋቅር ሥር እንዲካለሉ የተወሰነ ሲሆን፤ በውሳኔው መሠረት ቦላ ጉርባ፣ ጊዞላ እና ጫኖ ዶርጋ ቀበሌዎች ወደ አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ሲካለሉ የቆላ ሻራ ቀበሌ የተወሰኑ ነዋሪዎች ይህንን ውሳኔ ባለመቀበላቸው ምክንያት ውሳኔው ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል።
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ከጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ የጀመረ ቢሆንም፣ ከተወሰኑ የቀበሌው ነዋሪዎች ተቃውሞ ገጥሞት እንደ ነበር ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡ ውሳኔውን የተቃወሙ ነዋሪዎች ቀበሌው የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚካለል ከሆነ የእርሻ መሬታችን ተወስዶብን መተዳደሪያ እናጣለን የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር፣ የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር፣ የጋሞ ዞን እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቀድሞ ደ/ብ/ብ/ሕ/ክ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በቆላ ሻራ ቀበሌ ነዋሪዎች ዘንድ የተፈጠረውን ሥጋት ለማስወገድ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ተደጋጋሚ የሆኑ ውይይቶችን ከነዋሪዎች ጋር ቢያደርጉም መግባባት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ይናገራሉ።
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የቆላ ሻራ ቀበሌ ወደ አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር በመካለሉ በቀበሌው ነዋሪዎች ላይ የተፈጠረውን ሥጋት በመገንዘብ፣ የነዋሪዎችን የመኖሪያም ሆነ የእርሻ ይዞታቸውን የመንጠቅ ፍላጎት እንደሌለው እና ያላቸውን የመሬት ይዞታ የእርሻ ከሆነ በከተማ ግብርና አረንጓዴ ሰርተፍኬት እና የመኖሪያም ከሆነ በይዞታቸው ልክ ሕጋዊ የይዞታ ሰርተፍኬት እንደሚሰጣቸው ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቀበሌው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ ያሳወቀ መሆኑን ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡ ይሁንና የነዋሪዎቹ ሥጋት ሊወገድ ባለመቻሉ አለመግባባቱ እንደቀጠለ ነበር፡፡
በቆላ ሻራ ቀበሌ እና በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ከጥር ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የመንግሥት ልዩ ልዩ አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ሥራ እና አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል፡፡
ቀበሌውን ወደ መደበኛ የመንግሥት መዋቅር ለመመለስ እና የተቋረጠውን አገልግሎት ለማስቀጠል ነሐሴ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. የጋሞ ዞን እና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካ እና የጸጥታ አመራሮች እንዲሁም በአካባቢው የሚገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ እና የፌዴራል ፖሊስ የአርባምንጭ ምድብ አመራሮች በጋራ በመሆን የጸጥታ ግብረ ኃይል በማቋቋም ወደ ሥራ መግባታቸውን በመንግሥት ኃላፊዎቹ ተገልጿል፡፡ ግብረኃይሉ ለቀበሌው ወጣቶች “ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት” እና “ነዋሪዎችን ለሁከት በማነሳሳት” ቀበሌው ከመንግሥት መዋቅር ውጪ እንዲሆን አድርገዋል ያላቸውን አራት ተጠርጣሪዎችን ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አክለው ገልጸዋል።
ይህንኑ እስር ተከትሎ በዕለቱ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ገደማ ጀምሮ የተወሰኑ የቀበሌው ነዋሪዎች ወደ ዋና የአስፋልት መንገድ በመውጣት ተቃውሞ ማሰማታቸውን ማወቅ ተችሏል። ነዋሪዎቹ በጸጥታ አካላት ላይ ድንጋይ በመወርወር፣ በቀበሌው የሚኖሩና ቀበሌው ወደ አርባምንጭ ከተማ እንዲካለል ፍላጎት አላቸው ያሏቸውን ግለሰቦችም ላይ ጥቃት ለመፈጸም እንቅስቃሴ መጀመራቸውን፣ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ አባላት በጊዜያዊነት ባረፉበት ከአርባምንጭ ወደ ወላይታ ሶዶ በሚወስደው ዋና የአስፋልት መንገድ ዳር ባሉ ቤቶች ውስጥ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ፍራሾች እና ቦርሳዎች በአድማው ተሳታፊዎች መወሰዳቸውን የአርባምንጭ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ለኮሚሽኑ አስረድቷል። በወቅቱ በቦታው የነበሩ የጸጥታ ኃይሎች ጥይት ወደ ሰማይ በመተኮስ እና አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ለተቃውሞ የወጡ ሰዎችን ለመበተን መቻላቸውን ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው ከአርባምንጭ ከተማ ፖሊስ እንዲሁም ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ለመረዳት ችሏል።
በዕለቱ ሰልፉ በጸጥታ ኃይሎች መበተኑን ተከትሎ አብዛኛዎቹ ሰልፈኞች ከዋናው መንገድ ሲሸሹ፣ የተወሰኑ የቀበሌው ነዋሪዎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት ቀበሌውን እንዳይቆጣጠሩ ለመከላከል በሚል በቆላ ሻራ ቀበሌ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ መሰባሰባቸውን የአካባቢው የመንግሥት ኃላፊዎች እና ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የቀበሌው ነዋሪዎች ጨምረው አስረድተዋል፡፡
የሰዎች ሞትና የአካል ጉዳት
ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በአካባቢው የነበረው የመንግሥት የጸጥታ ግብረ ኃይል በቀበሌው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ለተሰበሰቡ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ለታጠቁ የቀድሞ የቀበሌው የሚሊሻ አባላት ሰላማዊ ጥሪ ማቅረቡን ሆኖም ተሰብሳቢዎቹ ከመንግሥት የጸጥታ ግብረ ኃይል ለቀረበላቸው ሰላማዊ ጥሪ አወንታዊ ምላሽ ባለመስጠታቸው፤ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የቆላ ሻራ ቀበሌን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢን ከሕግ አግባብ ውጪ ተቆጣጥረዋል ካሏቸው ግለሰቦች በኃይል ለማስለቀቅ ከሦስት አቅጣጫ የፖሊስ እርምጃ (ኦፕሬሽን) መጀመራቸውን በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኃላፊዎች ገልጸዋል። በቀበሌው ጽሕፈት ቤት ግቢ ውስጥ የነበሩ የታጠቁ የቀበሌው ሚሊሻዎችም ወደ መንግሥት የጸጥታ አካላት ጥይት መተኮሳቸውም ተገልጿል። በሁለቱ ቡድኖች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን፤ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ ሚሊሻዎች ሲሆኑ፣ የተቀሩ ሁለቱ ደግሞ የቀበሌው ነዋሪዎች መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል።
ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ከንጋቱ በግምት 12፡30 ሰዓት ገደማ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቀበሌውን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ አባላት ዩኒፎርም (ደንብ ልብስ) የለበሱ ሁለት የግብረ ኃይሉ አባላት በቀበሌው የአስተዳደር ጽሕፈት ቤት በአንድ ክፍል ውስጥ ሦስት ሰዎች (ሁለት የቀበሌ ሚሊሻ አባላት እና አንድ የቀበሌ ነዋሪ) ተደብቀው የነበሩበትን ክፍል በር ሰብረው በመግባት እየገፈተሩ ወደ ውጭ እንዲወጡ ካደረጓቸው በኋላ እዚያው በተለያየ የሰውነት ክፍላቸው ላይ ጥይት በመተኮስ መግደላቸውን ኮሚሽኑ በወቅቱ በስፍራው ከነበሩ የዐይን ምስክሮች ማወቅ ችሏል። ድርጊቱ ሲፈጸም በቦታው የነበሩ አንድ የዐይን ምስክር የነበረውን ሁኔታ ለኮሚሽኑ ሲያስረዱ፦
“በሩ ሲሰበር ከውስጥ 3 ሰዎች ነበሩ፣ ከእነዚህም አንደኛው ወገላ ዋሻ የተባለ ሙሉ የሚሊሻ ዩኒፎርም የለበሰ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ያኑዌ ያቻ የተባለ ከሚሊሻ ዩኒፎርም ሸሚዝ ብቻ ያደረገ እና ሦስተኛው የቀበሌው ነዋሪ የሆነ ሙሴ ሙንዴ የተባለ ወጣት ነበሩ። በወቅቱ ሦስቱም አልታጠቁም (መሣሪያ በእጃቸው አልያዙም) ነበር፤ ሁለት የደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ የጸጥታ አባላት እየገፈተሩ ካስወጧቸው በኋላ መሬት ላይ ገፍተው በመጣል በያዙት መሣሪያ ዋጋላ ዋሪሳን ቀኝ ጎኑ ላይ፣ ያኑዌ ያቻን ደረቱ ላይ እንዲሁም ሙሴ ሙንዴን ልቡ ላይ ጥይት በመተኮስ በእኛ ፊት ገደሏቸው” በማለት ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በዕለቱ በተፈጠረ ተቃውሞ እና ግጭት 9 የቀበሌው ነዋሪዎች እና 4 የግብረ ኃይሉ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ድርጊቱ ሲፈጸም በቦታው የነበሩ የዐይን ምስክሮች በግጭቱ ሕይወታቸው ያለፈ የሰባት ሰዎችን አስከሬን እዚያው የቀበሌ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በአንድ ቦታ መሰብሰባቸውን፤ በወቅቱ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የሟች ቤተሰቦች የሟቾችን አስከሬን እንዲወስዱ የፈቀዱ ቢሆንም፣ የአንዱ ሟች ቤተሰብ ብቻ በዕለቱ በመምጣት አንዱን አስከሬን እንደወሰደ፤ በተፈጠረው የጸጥታ ሁኔታ በአካባቢው የነበሩ አብዛኛዎቹ ወንዶች ከቀበሌው በመሸሻቸው ቀሪዎቹ አምስት አስከሬኖች እስከ ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. አመሻሽ ድረስ እንዳልተነሱ እና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ቆላ ሻራ ቀበሌ፣ ሥላሴ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው የሚሽን መካነ-መቃብር ስፍራ ውስጥ ሦስት ጉድጓዶችን በማስቆፈር በአንድ ጉድጓድ ሁለት አስከሬን አድርጎ መቅበሩን ኮሚሽኑ በአካባቢው ባደረገው ምልከታ እንዲሁም ከዐይን ምስክሮች ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ ችሏል።
በግለሰቦች ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት
የመንግሥት የጸጥታ ግብረኃይል ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በቀበሌው አራት ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ተከትሎ የተጠራው ሰልፍ በአካባቢው በነበሩ የመንግሥት የጸጥታ አካላት እንዲበተን ከተደረገ በኋላ፤ ከሰልፈኞቹ መካከል የተወሰኑ ግለሰቦች “የመንግሥት ደጋፊ ናቸው” እንዲሁም ቀበሌው ወደ አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር መካለሉን ይደግፋሉ ያሏቸው ግለሰቦች ንብረት ላይ ጥቃት ስለመፈጸማቸው ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው የአካባቢ ሽማግሌዎች፣ ተጎጂዎች እና ከመንግሥት ኃላፊዎች ገለጻ ለመረዳት ችሏል። በዚህም ንብረትነቱ የሰባት ግለሰቦች የሆነ በግምት በአራት ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ የሙዝ ተክል በመጨፍጨፍና በማውደም፣ በመኖሪያ ቤት እና በዙሪያው አጥር ላይ ድንጋይ በመወርወር ጉዳት ማድረሳቸውን ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች ጋር ባደረገው ውይይት እና የመስክ ምልከታ ለመረዳት ችሏል፡፡
በተጨማሪም የሟቾች አስከሬን በጸጥታ ግብረኃይሉ ከተቀበረ በኋላ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ አባላት የሟች ቤተሰቦች በአካባቢው ባህል መሠረት ለቅሶ እንዳይቀመጡ መከልከላቸውን፣ በዚህም ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የአንድ ሟች ቤተሰብ አባላት በልጃቸው ሞት ምክንያት ማልቀሳቸውን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ “ምን ተፈጥሮ ነው የምታለቅሱት?” በማለት የቤቱን በር፣ መስኮት እና ቴሌቪዥን መስበራቸውን እንዲሁም በወቅቱ በግቢው ውስጥ የነበረ ንብረትነቱ የሟች በሆነ ሞተር ሳይክል ጉዳት ማድረሳቸውን ማወቅ ተችሏል።
የትምህርት አገልግሎት መቋረጥ
የቆላ ሻራ ቀበሌ ወደ አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር መካለሉን ተከትሎ ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የቀበሌው የመንግሥት ሠራተኞች ወደ አርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር እንዲገቡ ተደርጎ ሙሉ ወርሃዊ ደመወዛቸው በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር በኩል የተከፈለ ቢሆንም፤ የቀበሌው የወቅቱ አስተዳደር ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በቀበሌው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች በጻፈው ደብዳቤ፣ በቀበሌው ውስጥ የሚገኙ የቆላ ሻራ 2ተኛ ደረጃ እና የሻራ ሙጃ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት በኩል የሚሰጥ ማንኛውንም የሥራ መመሪያ እንዳይቀበሉ በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይህንን ተከትሎ በትምህርት ቤቶቹ የሚገኙ ተማሪዎች “በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት በኩል የተዘጋጀ ካልሆነ በስተቀር በአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት በኩል የመጣ ፈተና አንፈተንም” በማለታቸው፤ በቀበሌው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የትምህርት አገልግሎት መቋረጡን ኮሚሽኑ ከአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ካሰባሰበው መረጃ ለማወቅ ችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን ለመውሰድ ተዘጋጅተው ከነበሩ 174 ተማሪዎች 17 ተማሪዎች ብቻ ሲፈተኑ፣ የተቀሩት 157 ተማሪዎች አለመፈተናቸውን የትምህርት ጽሕፈት ቤቱ ለኮሚሽኑ አስረድቷል። በተመሳሳይ በቀበሌው የ6ኛ ክፍል ፈተናን ለመፈተን ተዘጋጅተው የነበሩ 183 ተማሪዎች በሙሉ ፈተናውን እንዳልተፈተኑ እንዲሁም ከ274 የ7ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 273 ፣ ከ201 የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 198 ፣ ከ97 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 94 እና የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 100 ተማሪዎች የ2015 ዓ.ም. የሁለተኛ ሴሚስተር ማጠቃለያ ፈተና ሳይፈተኑ መቅረታቸውን የትምህርት ጽሕፈት ቤቱ ለኮሚሽኑ አረጋግጧል።
በተጠርጣሪዎች ላይ የተፈጸመ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በነሐሴ 18 እና 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በቀበሌው በተከሰተው ተቃውሞ እና ግጭት መነሻነት ኮሚሽኑ ምርመራውን እስካጠናቀቀበት ቀን ድረስ 126 (ወንድ 124 እና ሴት 2) ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን፣ ከእነዚህ መካከል 80 ተጠርጣሪዎች (ወንድ 78 ሴት 2) ከእስር መለቀቃቸውን፣ እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ ተይዘው ከሚገኙት መካከል 24 ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ለኮሚሽኑ አስረድቷል። ከተቀሩት 22 ተጠርጣሪዎች መካከል በተጠረጠሩበት ጉዳይ ካላቸው ተሳትፎ አኳያ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለባቸውን እና በፖሊስ በኩል መለቀቅ ያለባቸውን የመለየት ሥራ እየተሠራ እንደነበር ኮሚሽኑ ተረድቷል፡፡
ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎች ተይዘው በሚገኙባቸው በአርባምንጭ ከተማ፣ በሴቻ እና በየት ነበርሽ ፖሊስ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ከተጠርጣሪዎች ጋር ውይይት እና ቃለመጠይቅ አድርጓል። ተጠርጣሪዎቹ ተይዘው በሚገኙበት ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳልተፈጸመባቸው ቢገልጹም በቁጥጥር ሥር ሲውሉ እንዲሁም በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በክልሉ የግብረ ኃይል አባላት ድብደባ የተፈጸመባቸው እንደሆነ ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡
የመንግሥት አካላት ምላሽ
ኢሰመኮ ስለሁኔታው የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት፣ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት፣ ትምህርት ጽሕፈት ቤት፣ የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ የጋሞ ዞን ፍትሕ መምሪያ እና የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያን አነጋግሯል፡፡
የመንግሥት አካላት ቀበሌው ከጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የቀበሌ ተወካዮች በተገኙበት ወደ አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ሥር በመዘዋወሩ ርክክብ እንደተደረገ ገልጸው፤ ይህ ከመሆኑ በፊት ለአምስት ጊዜ ከቀበሌው ነዋሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን፤ ይሁንና በወቅቱ ኅብረተሰቡ የተለያዩ ሐሳቦችን እና ሥጋቶችን በማንሳት ውይይቶቹ በስምምነት ሳይቋጩ መቅረታቸውን ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡ የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ነዋሪዎች ያነሱትን ሥጋት ለማስወገድ፣ ነዋሪዎቹ የያዙት የእርሻ ማሳም ሆነ የመኖሪያ ቦታ ተለክቶ በያዙት የይዞታ ልክ የይዞታ መጠቀሚያ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸው እና የእርሻ ማሳቸውም የከተማ ግብርና አካል ሆኖ እንደሚቀጥል በውይይት ወቅት ግልጽ ለማድረግ እንደተሞከረ፤ ሆኖም ተመሳሳይ ጥያቄዎች እና ሥጋቶች በመቀጠላቸው ምክንያት የጽሑፍ ማረጋገጫ ጭምር የተሰጠ ቢሆንም “በቀበሌው የአመራር ቦታዎች ላይ ተመድበው ሲሠሩ የነበሩ ግለሰቦች ያለአግባብ ያገኙትን የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ብቻ ሲሉ ሕዝቡ የከተማ አስተዳደሩን ውሳኔ እንዳይቀበል አድርገዋል” በማለት ገልጸዋል፡፡
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችም የቆላ ሻራ ቀበሌ ለስድስት ተከታታይ ወራት በሁሉም ደረጃ ከሚገኘው የመንግሥት ተቋማት ቁጥጥር ውጪ ሆኖ መቆየቱን ገልጸው፤ መንግሥት ችግሩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በቀበሌው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት መሽገው የተቀመጡ የታጠቁ የቀበሌ ሚሊሻ አባላት ትጥቃቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አሊያም ከአካባቢ የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ ውይይት እና ጥሪ የተደረገላቸው ቢሆንም፤ ይህንን እንደማያደርጉ በግልጽ ለክልሉ እና ለአካባቢው መስተዳድር አካላት መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡
በቀበሌው ከሚገኙ ከታጠቁ ሚሊሻ አባላት በተጨማሪ ራሳቸውን የቀበሌ አመራር በማድረግ የሾሙ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና በተለያዩ ምክንያቶች በዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ አካላት፤ ጉዳዩ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ወደ መድረክ እንዲመጡ ጥሪ ስናቀርብላቸው የውይይት መድረኮችን ከመበተን እና በመድረኮች ላይ በመገኘት የአመጽ ድምጾችን ከማሰማት ባለፈ ለውይይት ዝግጁ ሳይሆኑ ቀርተዋል ሲሉ ገልጸዋል። እነዚህ አካላት ቀበሌውን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ መንግሥት በቀበሌው የመደባቸው የቀበሌ አመራሮች፤ የጸጥታ አካላት እና የመንግሥት ሠራተኞች ወደ አካባቢው ተንቀሳቅሰው መደበኛ ሥራቸውን እንዳይሠሩ ሲያደርጉ መቆየታቸውን እና ቀበሌውን ወደ አርባምንጭ ከተማ ለማካለል የያዘውን ዕቅድ ይደግፋሉ ተብለው የተለዩ ግለሰቦችን በመለየት ማስፈራሪያ እና ዛቻ ሲፈጽሙባቸው ነበር በማለት ለኮሚሽኑ አስረድተዋል። በተጨማሪም ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. እነዚህ አካላት ዓላማችንን አልደገፉም ወይም ከመንግሥት ጎን ቆመዋል በተባሉ የቀበሌ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ ዕቅድ መያዛቸውን መንግሥት አስቀድሞ መረጃ በማግኘት የነዋሪዎችን ደኅንነት በማስጠበቅ እና የሕግ የበላይነትን በማስከበር ቀበሌውን ከታቀደው ጥፋት መታደግ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ፖሊስም ሁኔታውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ ዘርፈ-ብዙ ጥረቶች ሳይሳካ መቅረቱንና፣ በቀበሌው ለሚገኙ ወጣቶች እና ለታጠቁ የሚሊሻ አባላት የተደራጀ ወታደራዊ ስልጠና የሚሰጥ አካል ስለመኖሩ ማረጋገጣቸውን ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪ በቀበሌው በቅርብ ርቀት የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች አልፎ አልፎ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ፤ እነዚህም ቡድኖች ከዚህ ታጣቂ ኃይል ጋር የሚቀናጁ ከሆነ ለአካባቢው ከፍ ያለ የጸጥታ ሥጋት የሚፈጥር በመሆኑ ችግሩን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በመወሰን ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ከፍርድ ቤት በተሰጠ ትእዛዝ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ለኮሚሽኑ አስረድቷል። ይህን ተከትሎም በዕለቱ በጎዳና ላይ አመጽ እና በሰዎች ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በቀበሌው በሚገኙ የመንግሥት የጸጥታ አባላት ላይ ጥቃት ለማድረስ እና ንብረት ለመዝረፍ እንቅስቃሴ መደረጉን ፖሊስ ገልጿል። በወቅቱ በአካባቢው የነበረው የጸጥታ ግብረኃይል በሰልፈኞች ላይ ጉዳት ሳያደርስ ጥይት ወደ ሰማይ በመተኮስ እና አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም የአመጽ እንቅስቃሴውን መቆጣጠሩን፤ ሆኖም ‹‹የሕገ-ወጥ ቡድን አባላት›› የተባሉት ግለሰቦች በሰዎች የእርሻ ማሳ እና መኖሪያ ቤት ላይ ጉዳት እንዳደረሱ ፖሊስ ለኮሚሽኑ ጨምሮ አስረድቷል፡፡ የጋሞ ዞን ፍትሕ መምሪያ እና የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊዎች ለኮሚሽኑ በሰጡት ምላሽ በወቅቱ በጸጥታ ግብረኃይሉ በተወሰደው የኃይል እርምጃ በድምሩ የሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል። በግብረ ኃይሉ የተወሰደውን የኃይል እርምጃ ሕጋዊነት እና ተመጣጣኝነት አስመልክቶ የአካባቢው መስተዳድር ተገቢውን ምርመራ እንደሚያደርግ እንዲሁም ለተፈጸሙ ጥፋቶች ተጠያቂነትን እንደሚያረጋግጥ ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡
ግኝት እና መደምደሚያ
- በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 14 እና 15 እንዲሁም የሲቪልና የፖሊቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 6(1) መሠረት፣ ማንኛውም ሰው በከባድ ወንጀል በፍርድ ቤት ውሳኔ ካልሆነ በስተቀር በዘፈቀደ ሕይወቱን ሊነጠቅ የማይገባ መሆኑንና መንግሥት የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት የማክበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ይሁንና ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የክልሉ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የቆላ ሻራ ቀበሌ አስተዳደር ጽሕፈት ቤትን በመቆጣጠር በቀበሌው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ቢሮ ውስጥ ተደብቀው የነበሩ እና ያልታጠቁ ሁለት የሚሊሻ አባላትን እንዲሁም አንድ ሌላ የቀበሌው ነዋሪን ጨምሮ ሦስት ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ከተደበቁበት ክፍል በማውጣት ነዋሪዎች ፊት በጭካኔ በጥይት ተኩሰው መግደላቸውን ኢሰመኮ አረጋግጧል፤ ይህም ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ (extra-judicial killing) ነው፡፡
- በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 18(1) እንዲሁም የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 7 በተደነገገው መሠረት ማንም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት ኢ-ሰብአዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው።
ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በቀበሌው ጽሕፈት ቤት በታሰሩ የተወሰኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በቁጥጥር ሥር በሚውሉበት ወቅት እና ቁጥጥር ሥር ከዋሉም በኋላ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ ድብደባ እና ማንገላታት ተፈጽሟል፡፡
- በተቃውሞ እና ግጭቱ ተሳታፊ የነበሩ የተወሰኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የክልሉን መንግሥት ሐሳብ የሚደግፉ ናቸው ብለው የለዩትን ሰዎች የእርሻ ቦታ እና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል፣ የክልሉ ጸጥታ አባላትም ቢያንስ አንድ የተገደለ ሰው ቤት ውስጥ በንብረትም ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
ስለሆነም የክልሉ አስተዳደር የተሟላ ምርመራ በማካሄድ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ሊያረጋግጥ፣ የተጎዱ ሰዎችንና ቤተሰቦችን በተገቢው መንገድ ሊክስ እንዲሁም ለችግሩ የሥር ምክንያት ዘላቂ መፍትሔ ሊተገብር ይገባል፡፡ በተለይም የክልሉ አስተዳደር የሚከተሉትን እርምጃዎች እንዲወስድ ኢሰመኮ ያሳስባል፡፡
- ሥር የዋሉ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሆነ ግድያ የፈጸሙና ያሰፈጸሙ፤ እንዲሁም በቁጥጥር ሥር በዋሉ ሰዎች ላይ ድብደባ የፈጸሙ፣ በሰዎች ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ የተሳተፉ የክልሉ መንግሥት የጸጥታ አባላት ላይ አስፈላጊ የሆነ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፤
- በግለሰቦች ቤት እና ሰብል ላይ ጉዳት በማድረስ የተሳተፉ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊ የሆነ የወንጀል ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፤
- ቤተሰቦች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እንዲሁም ንብረታቸው ለወደመባቸው ሰዎች፣ ለደረሰባቸው ጉዳት ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ እንዲከፈል፤ እንዲሁም
- ተቃውሞ እና ግጭት ምክንያት የሆነው የቀበሌ አስተዳደር መዋቅር ውዝግብ ነዋሪዎችን ባሳተፈ፣ ሰላማዊና ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ ዘላቂ መፍትሔ በአፋጣኝ መተግበር እና የተቋረጡ አገልግሎቶችን በሙሉ መቀጠላቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡