ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶችን ያማከለ የሽግግር ፍትሕ ምንድነው?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሽግግር ፍትሕ መመሪያ ማስታወሻ እና የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ እንዳስቀመጡት፣ የሽግግር ፍትሕ ማለት አንድ ማኅበረሰብ ያለፉ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን፣ ክፍፍሎችን እና አለመመጣጠኖችን ለማስወገድ፣ ፍትሕን ለማስፈን እና ዕርቅን ለማውረድ፣ ለደኅንነትም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚወስዷቸው የተለያዩ (መደበኛ እና ባህላዊ/መደበኛ ያልሆኑ) የፖሊሲ እርምጃዎችን እና ተቋማዊ አሠራሮች የሚያመለክት ሂደት ነው። የሽግግር ፍትሕ አጠቃላይ ዓላማ ላለፉ በደሎች እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተገቢ ምላሽ በመስጠት ዘላቂ ሰላም እና ፍትሕ ማምጣት እንዲሁም ወደ ዕርቅ ማምራት ነው። ይህን ለማሳካት አራት (4) እርስ በርስ የተያያዙ እና የሚደጋገፉ መሠረታዊ ይዘቶችን/ስልቶችን የሚያካትት ነው። ይህም እውነትን ማፈላለግ፣ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ለተጎጂዎች ማካካሻ መስጠት፣ እና ጉዳቶች/ጥሰቶች እንዳይደገሙ ዋስትና ለመስጠት የሚወሰዱ ተቋማዊና ሌሎች ማሻሻያዎች ማድረግን ጨምሮ በማኅበረሰባዊ እና ባህላዊ ዘርፎች የሚወሰዱ እርምጃዎችን መተግበር ያካትታል (የተ.መ.ድ. የሽግግር ፍትሕ መመሪያ ማስታወሻ፣ መርሕ 8) ።
ምንም እንኳን በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ላይ የሚፈጸሙ መዋቅራዊ እና ስልታዊ ጥሰቶች ለግጭቶች ምክንያት የሚሆኑና በግጭት ወቅት በሚፈጸሙ ድርጊቶችም መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚያዊ እና የማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶች የሚደርሱ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ከግጭት በኋላ በሚኖሩ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች የኢኮኖሚያዊ እና የማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን ያለማካተትና በሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ጥሰቶች ብቻ ላይ የማተኮር አካሄድ ይስተዋልባቸዋል።
ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶችን ከሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች የተለዩ አድርጎ የመመልከት የቆየ አዝማሚያ መኖሩና፣ የሽግግር ፍትሕ አሠራር እና ፅንሰ ሐሳብ ከመዋቅራዊ የፍትሕ መጓደሎች ይልቅ አትኩሮቱን በዋናነት የግለሰብ ተጠያቂነት ማስፈን ላይ ባደረገው ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ በከፍተኛ ሁኔታ መቃኘቱ ለክፍተቱ እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ። ይህ የቆየ የሽግግር ፍትሕ እሳቤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁሉን አቀፍ በሆነ አረዳድ እየተተካ የመጣ ሲሆን፣ በተለይም በተለምዶ የአረብ ሀገራት አብዮት በመባል የሚታወቀው እና በዋናነት በቱኒዝያ እና በግብጽ ከተካሄዱት አብዮቶች በኋላ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲሁም የማኅበራዊ ፍትሕ ጉዳዮችን ማካተት እንደሚኖርባቸው ታምኖበታል።
ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶችን ያማከለ የሽግግር ፍትሕ ይህን ሁሉን አቀፍ አረዳድ የሚከተልና በግጭት ለደረሱ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ጥሰቶች መፍትሔ ከማፈላለግ ባለፈ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች ለግጭቶች ምክንያት/አባባሽ ሆነው የቆዩ መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጉዳዮችን ጨምሮ በግጭት ወቅት ለደረሱ ሁሉም የመብት ጥሰቶች ምላሽ በሚሰጥ መልኩ ሊተገበሩ ይገባል የሚለውን አስተሳሰብ የሚወክል ነው።
በሽግግር ፍትሕ ሂደት ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች እንዴት መካተት ይችላሉ?
በተ.መ.ድ. ዋና ጸሐፊ የወጣው የመመሪያ ማስታወሻ እንደተገለጸው በሽግግር ፍትሕ ወቅት ተግባራዊ የሚደረጉ አሠራሮች የግጭት መንስኤዎችን ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ እና ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶችን ጨምሮ ለደረሱ የመብት ጥሰቶች ሁሉን አቀፍ እና በተቀናጀ መልኩ መፍትሔ ለመስጠት ያለሙ መሆን ይገባቸዋል። ስለሆነም ከዚህ በመቀጠል ባለው ክፍል ተግባራዊ የሚደረጉ የሽግግር ፍትሕ ስልቶች (የወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነትን ማፈላለግ፣ ለተጎጂዎች ማካካሻ መስጠት፣ እና ጉዳቶች/ጥሰቶች እንዳይደገሙ ዋስትና መስጠት) ለኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽ ከመስጠት አንጻር ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና እንመለከታለን።
1. የወንጀል ተጠያቂነት
የተ.መ.ድ. መመሪያ በሽግግር ፍትሕ ሂደት የኢኮኖሚያዊ እና የማኅበራዊ መብቶች እንዲሁም የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ጥሰት ሆነው የሚቆጠሩ ድርጊቶችን በሀገር አቀፍ ወይም በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት መመርመር፣ ክስ ማቅረብ እና መቅጣት እንደሚገባ ያሳስባል።
በመሆኑም በሽግግር ፍትሕ የጊዜ ወሰን በሚሸፈኑ ጊዜያት በግጭትም ሆነ ከግጭት ውጪ በሆነ መልኩ የተፈጠሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን ደረጃዎችን በማውጣት አመልካች በሆነ መንገድ (symbolic) የክስ ሂደት አካል እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን በሁለት መልኩ ማድረግ ይቻላል። አንደኛ ከግጭት ውጪ ባለው አውድ በሙስና እንዲሁም በሌሎች ቀጥተኛ ድርጊቶች ለምሳሌ አስገድዶ በማስነሳት እና በሌሎች ሁኔታ የማኅበረሰቡ ኑሮ የተመሠረተባቸውን የተፈጥሮ ሀብቶች በማሳጣት ለደረሱ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ነው። ሁለተኛ በግጭት ወቅት የደረሱ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን በተለየ ሁኔታ መመርመር እና መቅጣት ነው። ለምሳሌ መጠነ ሰፊ የመኖሪያ ቤትና የንብረት ውድመት/ዝርፊያ፣ በግዳጅ ማፈናቀል፣ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይደርስ መከልከል፣ ለማኅበረሰቡ ሕልውና አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ማውደም እና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶች እንደነገሩ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች (በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ የጦር ወንጀል እንዲሁም የዘር ማጥፋት ወንጀል) ሆነው ሊወሰዱ የሚችሉ እንደመሆናቸው እንደዚህ ያሉ ጥሰቶችን አለመመርመር፣ ክስ አለመመሥረት እና አለመቅጣት ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችም ሆነ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊነት እና የወንጀል ሕግጋት አንጻር ተቀባይነት አይኖረውም።
ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን የሚያንጸባርቁ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎችን ማውጣት እንዲሁም ያለመከሰስ እና የይርጋ መብቶችን የሚመለከቱ ደንቦች ተያያዥ ጉዳዮችን ለመመርመር እና ክስ ለማቅረብ እንቅፋት በማይሆኑ መልኩ ማሻሻል የሽግግር ፍትሕ ሂደት የስኬት አመላካቾች እንደሆኑ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ ያስቀምጣል።
2. የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖች
ሀገራት የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖችን ሲያቋቁሙ የኢኮኖሚያዊ እና የማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲመረምሩ እና የማስተካከያ ምክረ ሐሳቦችን እንዲያቀርቡ በሚያስችል መልኩ ማዋቀር እንደሚገባቸው የተ.መ.ድ. የሽግግር ፍትሕ መመሪያ ማስታወሻ ያስቀምጣል።
በሽግግር ፍትሕ ወቅት የሚቋቋሙ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖች ከሚያከናውኗቸው ተግባራት አንዱ የግጭቶች መሠረታዊ ምክንያቶች እንዲሁም በግጭቱ የደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን መለየት፣ ይፋ ማውጣት እና የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦችን ማቅረብ ነው። ይህም ለግጭቶች መሠረታዊ ምክንያት የሆኑ መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲሁም በግጭቱ ወቅት የደረሱ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመለየት፣ ለመሰነድ እና መፍትሔ ለማመላከት ምቹ ያደርጋቸዋል። የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን በእውነት የማፈላለግ እና ይፋ የማውጣት ተግባር አካል አለማድረግ ያለፉ ሁነቶች በተሟላ መልኩ እንዳይሰነዱ ከማድረግ አልፎም የሚወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች ውጤታማነት ላይ አሎታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ለግጭት ምክንያት የሆኑ መዋቅራዊ ጉዳዮችን እና በግጭት ወቅት የተፈጸሙ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን በእውነት የማፈላለግ ሂደቶች የማካተት አሠራር በሌሎች በሽግግር ፍትሕ ወይም በእውነት ማፈላለግ ሂደት ውስጥ ባለፉ ሀገራት ተሞክሮዎች አሉ። በተለይም የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን በጥልቀት በመመርመርና በዝርዝር በመሰነድ ረገድ የምሥራቅ ቲሞር የእውነት እና ዕርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ልምድን በዋናነት ማንሳት የሚቻል ሲሆን በላይቤሪያ እና በሴራሊዮን የተቋቋሙ የእውነት እና የዕርቅ ኮሚሽኖችም የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን በእውነት የማፈላለግ ተግባር ማካተታቸውን መመልከት ይቻላል።
3. ማካካሻ
ማካካሻ ተጎጂዎችን ወደነበሩበት መመለስ፣ ካሳ፣ ማገገሚያ፣ እርካታ እና ያለመድገም ዋስትና ለማረጋገጥ የሚረዱ እርምጃዎችን የሚያካትት ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮችን የያዘ የሽግግር ፍትሕ ስልት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በግጭትም ሆነ ከግጭት ውጪ በደረሱ ከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶች ተጎጂ ለሆኑ ግለሰቦች እና ማኅበረሰቦች የሚሰጡ ማካካሻዎች በተቻለ መጠን የተጎጂዎችን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ወደ ቀድሞ መኖሪያ ስፍራቸው መመለስን/በሌሎች ቦታዎች ማስፈርን፤ አላግባብ ያጡትን ንብረት፣ ቤት፣ መሬት፤ ሥራ እንዲያገኙ ማድረግን፣ የግጭት ጉዳቶችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ሥነ ልቦናዊ ድጋፎችን መስጠትን፤ በግጭቱ የታጡ የትምህርት ጊዜያትን የሚያካክስ የትምህርት ሥርዓት መተግበርን፣ እንደ ሆስፒታል እና ትምህርት ቤት ያሉ ጉዳት የደረሰባቸው የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ መገንባትን ባካተተ መልኩ ሊተገበሩ ይገባል። በተጨማሪም ተጎጂዎች ያሉባቸውን አንገብጋቢ እና አስቸኳይ ችግሮች በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ የተሟላ የማካካሻ ሥርዓት እስኪተገበር ድረሰ እንደ ምግብ፣ ውሃ፣ ንጽሕና መጠበቂያ፣ መጠለያ እና የጤና አገልግሎት ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ጣልቃ-ገብ የማካካሻ ወይም የድጋፍ ተግባራትን መቀየስ ያስፈልጋል።
4. ጥሰቶች እንዳይደገሙ ዋስትና ለመስጠት የሚወሰዱ እርምጃዎች (ተቋማዊ፣ የሕግና ሌሎች ማሻሻያዎች)
በሽግግር ፍትሕ ጥሰቶች እንዳይደገሙ ዋስትና ለመስጠት የሚወሰዱ እርምጃዎች ለምሳሌ ተቋማዊና የሕግ ማሻሻያዎች ለግጭቶች መንስኤ የሆኑ መዋቅራዊ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲሁም በግጭቱ ወቅት የደረሱ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲፈጸሙ ያስቻሉ የሕግ ማዕቀፎች እና አሠራሮችን በተገቢ መልክ መለወጥ እና ጥሰቶች እንዳይደገሙ ማድረግን ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል። ለዚህም በተለይም ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች በዝርዝር ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ እንዲሰጣቸው ማድረግን፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች በፍርድ ቤት ዳኝነት የሚያገኙ ጉዳዮች (Justiciable) እንደሆኑ በግልጽ ዕውቅና መስጠትን፤ የመሬት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን እኩል እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥን፣ ሙስናን መከላከልን፣ በታሪክ የተገለሉ እና በግጭቱ በተለየ ሁኔታ የተጎዱ ማኅበረሰቦችን የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች የግጭት ምክንያት ሆነው የቆዩ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በሕገ መንግሥት ወይም በሌሎች ሕጎች እንዲሁም ተቋማዊ ማሻሻያዎች እንዲፈቱ የሚያስችል ሂደት መከተል ያስፈልጋል።