የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለ4ኛ ጊዜ እያካሄደ ባለው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር የመጀመሪያው ምዕራፍ ውድድር ተጠናቀቀ፡፡ ውድድሩ በ12 ክልሎች እና በ2 ከተማ አስተዳደሮች የተካሄደ ሲሆን ከ81 ትምህርት ቤቶች 162 ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ተማሪዎቹ የመከራከሪያ ጽሑፋቸውን በማዘጋጀት የመወዳደሪያ መስፈርቱን ያሟሉ ሲሆን ሚያዝያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. የቃል ክርክር አካሂደዋል፡፡
በኢሰመኮ አዘጋጅነት በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ ችሎት ውድድር ምናባዊ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ ተማሪዎች የአመልካች እና የተጠሪ ወገንን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት ሲሆን የመደበኛ ፍርድ ቤት የክርክር ሥርዓትን የሚከተል ሆኖ በተወዳዳሪ ተማሪዎች እና በትምህርት ቤቶች ማኅበረሰብ ዘንድ የሰብአዊ መብቶች ዕውቀትንና ክህሎትን ለመገንባት ያለመ ነው፡፡
በክልል ደረጃ በተካሄደ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት (ከኦሮሚያ ክልል)፣ አባ ፖስካል ትምህርት ቤት (ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል)፣ ሊች ጎጎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል)፣ ዳዕሮ አካዳሚ (ከትግራይ ክልል)፣ ሳቢያን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር)፣ እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት (ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር)፣ ጅግጅጋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ከሶማሊ ክልል)፣ አሶሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል)፣ ዱፕቲ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ከአፋር ክልል)፣ ሪስፕንስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት (ከአማራ ክልል)፣ ቢሻው ወልደዮሃንስ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት (ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል)፣ ቅዱስ ገብርኤል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ከሲዳማ ክልል)፣ ማሪፍ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት (ከሐረሪ ክልል) እና ኤላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ከጋምቤላ ክልል) አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ውድድሩን በበላይነት ካጠናቀቁት 14 ትምህርት ቤቶች መካከል በጽሑፍ ክርክር የላቀ ነጥብ የሚያስመዘግቡ 8 ቡድኖች በግንቦት ወር በአዲስ አባባ ከተማ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
የዚህ ዓመት ምናባዊ ጉዳይ ወቅታዊ በሆነው በሽግግር ፍትሕ ሂደት ላይ ያተኮረ ሲሆን ታሳቢ ሊደረጉ የሚገቡ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በማንሳት የተወዳዳሪ ተማሪዎችን እና የትምህርት ቤቶች ማኅበረሰብን ዕውቀትና ግንዛቤ ለመገንባት ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡