የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሴት ልጅ ግርዛትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት እና ከምክር ቤቱ ሴቶችና ወጣቶች ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተወያይቷል። 

ውይይቱ የሴት ልጅ ግርዛት በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የሚያስከትላቸው የጤና እክሎች እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። እንደዚሁም የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶችን ለማስፋፋት እና ለማስከበር ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በቀጣይ በትብበር መሥራት የሚቻልባቸው ጉዳዮች ተነስተው ምክክር ተደርጎባቸዋል። 

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሸይኽ ሙሐመድዘይን ዘኽረዲን በግርዛት ሳቢያ ሴቶች እና ሕፃናት ለአካላዊም ሆነ ለሥነ-ልቦናዊ ጉዳት እንዲጋለጡ ማድረግ የሃይማኖቱ አስተምህሮ አለመሆኑን፤ ነገር ግን በዚህ ዙሪያ የተሳሳቱ አካሄዶች መኖራቸውን ገልጸዋል። በሴቶች እና በሕፃናት ላይ አካላዊ ጉዳትና የሥነልቦና ችግር የሚፈጥሩ አሠራሮችን እና ልማዶችን ለመቅረፍ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል። ኃላፊው ኢሰመኮ በግርዛት ሳቢያ በሴቶችና በሕፃናት ላይ በሚደርሱ የጤና ችግሮች እና በመፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ከዑለማ ጉባኤው ጋር በጋራ ለመሥራት ላሳየው ፍላጎትም አመስግነዋል። 

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በበኩላቸው ግርዛት በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የጤና እና የማኅበራዊ ጉዳቶችን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያስከትል ድርጊት መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም በሴቶች እና በሕፃናት ላይ ዘርፈብዙ ጉዳት የሚያደርሰውን ግርዛት ለማስቆም ምክር ቤቱን ጨምሮ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።