በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት እ.ኤ.አ. በየዓመቱ ታኅሣሥ 10 ቀን የሚውለውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ለማሰብ የተጀመረው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል አራተኛ ዙር፣ ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ፣ ያሬድ ሙዚቃ ትምሕርት ቤት፣ አሸናፊ ከበደ የክዋኔ ጥበባት አዳራሽ በይፋ ተጀምሯል። የዘንድሮው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በኢሰመኮ 2016 ዓ.ም. ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት አሳሳቢ ተብለው በተለዩት በሕይወት የመኖር መብት (የሴቶች ሕይወት) እና በቂ ምግብ እና በቂ ውሃ በማግኘት መብቶች ላይ ያተኮረ ነው።
ዓመታዊው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዋነኛ ዓላማ ዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶች ቀን ለማሰብ፣ የኪነ ጥበብን እና የሰብአዊ መብቶችን ትስስር ለማጠናከር፣ በሁለቱ ዘርፎች መካከል ያለውን ጥምረት በተመለከተ ግንዛቤ ለማስፋፋት፣ እንዲሁም ኪነ ጥበብ “ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት” የሚለውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ራዕይ ለማሳካት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማስታወስ ነው።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን በዋነኝነት ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ንቅናቄዎች እና ሰነዶች መሠረት እና መነሻ የሆነው የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ የጸደቀበት 76ኛ ዓመት በተጨማሪ በአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር መሠረት የተቋቋመውን የአፍሪካ የሴቶች መብት ልዩ ራፖርተር መዋቅር 25ኛ ዓመት የሚታሰብበት (25th Anniversary of the Special Rapporteur on the Rights of Women in Africa- African Commission on Human and Peoples’ Rights (ACHPR)) እንዲሁም በሁሉም ግዛቶች የሁሉም ፍልሰተኞች ሰብአዊ መብቶች እና መሠረታዊ ነጻነቶች መከበር እንዳለባቸው ለማስታወስ የሚከበረውን የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ቀን 12ኛ ዓመት (12th Anniversary of International Migrants Day to remind all states to ensure respect for the human rights and fundamental freedoms of all migrants) የምናስብበት ነው።
ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በተካሄዱት የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሎች በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አጫጭርና ረዘም ያሉ ፊልሞች እንዲሁም የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን የሚዳስሱ ዘጋቢ ፊልሞች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን የአጫጭር ፊልም እና የፎቶግራፍ ውድድሮች ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዳቸው ይታወሳል። በዘንድሮው ፊልም ፌስቲቫል የኪነ ጥበብ ዘርፎች ተደራሽነትን ለማስፋት ከፎቶግራፍ በተጨማሪ የአጫጭር ሥነ ጽሑፍ እና ሥዕል ሥራዎች በውድድሩ ተካትተዋል።
ውድድሩ ከጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በይፋ ተጀምሮ እስከ ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ለተወዳዳሪዎች ክፍት ሆኖ የቆየ ሲሆን 234 ተሳታፊዎች የኪነጥበብ ሥራቸውን ለኮሚሽኑ በመላክ ተወዳድረዋል። ትኩረቱን “በቂ ምግብ እና በቂ ውሃ የማግኘት መብት” ላይ ባደረገው የፎቶግራፍ ውድድር 96 ፎቶግራፎች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን፣ “በሕይወት የመኖር መብት (የሴቶች ሕይወት)” ላይ ባተኮረው ውድድር ደግሞ 83 ሥዕሎች እና 55 አጫጭር ሥነ ጽሑፎች ቀርበዋል።
ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የፌስቲቫሉ መክፈቻ ዝግጅት የተመረጡ ፎቶግራፎች፣ ሥዕሎችና አጫጭር ጽሑፎች በዐውደ ርዕይ መልክ ለታዳሚዎች ለዕይታ ቀርበዋል። በተጨማሪም የአጫጭር ሥነ ጽሑፍ እና የፎቶግራፍ ውድድር አሸናፊዎች ይፋ ተደርገዋል። በዚህም መሠረት፦
በአጫጭር ሥነ ጽሑፍ ውድድሩ:-
1ኛ. ጥላሁን ደመቀ ታሪኩ (ለኛ ይብሳል)
2ኛ. አብርሃም ኃይሉ (ተሸንፏል)
3ኛ. ዘላለም ግዛው (ጓንታናሞ ቤይን የበጣጠሰ ዐይን)
በፎቶግራፍ ውድድር፦
1ኛ. የአብቃል አበበ (In the Shadow of West)
2ኛ. እስጢፋኖስ ምንይችል (በቂ ምግብና ውሃ)
3ኛ. በረከት ፈለቀ (ያልተሰሙ ድምጾች)
በመርኃ ግብሩ ለተገኙ የውድድሩ ተሳትፊዎችም የዕውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቷል።
በፌስቲቫሉ በልዩ ሁኔታ ለዚህ ለ4ተኛው ዙር ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምሕርት ክፍል የተዘጋጀ ‘‘ተመለሽ’’ ቲያትር ለዕይታ ቀርቧል።
በዝግጅቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው በኪነጥበብ ዘርፍ ሙያ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎች፣ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ በሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና የውጪ ሀገራት ተወካዮች፣ መገናኛ ብዙኀን፣ ተወዳዳሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል፡፡ ዓመታዊው ፌስቲቫል ከታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ እስከያዝነው ወር መጨረሻ በአዳማ፣ በአርባ ምንጭ፣ በአሶሳ፣ በባሕር ዳር፣ በጋምቤላ፣ በሃዋሳ፣ በጅግጂጋ፣ በጅማ፣ በመቀሌ እና በሰመራ ከተሞች ተካሂዶ ይጠናቀቃል።
“ሰብአዊ መብቶች ጽንሰ ሐሳብ ብቻ አይደሉም – ተግባራት ጭምር እንጂ” ያሉት የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፤ የጥበብ ወዳጆች ሥራቸው ጥበብ ብቻ አለመሆኑን ይልቁንም ተሟጋችነትም ጭምር መሆኑን አስታውሰዋል።