የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙ ላይ ጥር 18 እና 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ በተጠቀሰው ጊዜ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተከናወኑ ዐበይት ተግባራትን፣ የተገኙ ውጤቶችን እና ያጋጠሙ ችግሮችን ከኢሰመኮ ዓመታዊ እና የ6 ወራት ዕቅድ አንጻር በመገምገም የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም ሊወሰዱ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ ለመመካከር ያለመ ነው። በመድረኩ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፣ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ የዋና ኮሚሽነሩ የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች አማካሪ ዶ/ር ሚዛኔ አባተ እንዲሁም በዋናው መሥሪያ ቤት የሚገኙ የሥራ ክፍሎች እና የከተማ ጽሕፈት ቤቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ኢሰመኮ በ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ባስቀመጣቸው የትኩረት መስኮች ያከናወናቸው ዐበይት ተግባራት እና የተገኙ ውጤቶች እንዲሁም የፋይናንስ አጠቃቀም መግለጫ እና በዕቅድ አፈጻጸም ያጋጠሙ ችግሮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በዚህም መሠረት በሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል በ321 ፖሊስ ጣቢያዎች፣ 9 መደበኛ ያልሆኑ ማቆያዎች እና 42 ማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ክትትል መደረጉ፣ በ28 ፖሊስ ጣቢያዎች እና በ33 ማረሚያ ቤቶች የክትትል ግኝቶችን መሠረት በማድረግ በሥራ ክፍሉ በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ የአፈጻጸም ክትትል መደረጉ ተገልጿል። በተመሳሳይ ተንቀሳቃሽ የአቤቱታ መቀበያ ማእከላትን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች 883 የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አቤቱታዎች እና ጥቆማዎች ለኢሰመኮ መቅረባቸው፣ ከእነዚህም መካከል ለ547ቱ በምርመራ፣ በምክር አገልግሎት እና በቅብብሎሽ ሥርዓት የሕግ እና ሌሎች የድጋፍ አገልግሎቶችን ወደሚሰጡ ባለድርሻ አካላት በመምራት መፍትሔ እንዲያገኙ መደረጉ ተመላክቷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ከፌዴራል መንግሥት እንዲሁም ከ11 የክልል መንግሥታት ፕሬዚዳንቶች እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በየክልሉ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ያካሄዱት ምክክር እና የጀመሩት ገንቢ ውይይት የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና ጥሰቶች ቅድመ መከላከል ሥራ ላይ ውጤት ማስገኘቱ ተገልጿል። በተደረጉት ገንቢ ውይይቶች መሠረት በየክልሉ ሕጋዊ ባልሆነ ምክንያት በፖሊስ ጣቢያዎች ተይዘው የነበሩ 1427 ሰዎች ከእስር መለቀቃቸው እና 108 ሰዎች የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው የተደረገ መሆኑ እንዲሁም 85 ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው እንዲታይ መደረጉ በማሳያነት ተጠቅሷል። በማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን ለማሻሻል በአብዛኛው ክልሎች የታራሚዎች የቀን የምግብ ፍጆታ በጀት መሻሻሉ፣ በተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች አልጋ፣ ፍራሽ እና ሌሎች አልባሳት መሟላታቸው ተነግሯል። በተጨማሪም በሰብአዊ መብቶች ምርመራ በተለዩ ግኝቶች መሠረት ኢሰመኮ የሰጣቸው 14 ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ጋር የተያያዙ ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚ መደረጋቸው በአወንታዊ ትብብር ከተገኙ መልካም ውጤቶች መካከል መሆናቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ሥራ ክፍል አማካኝነት በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ፣ በተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች መብቶች አያያዝ፣ በአረጋውያን መብቶች፣ በሰብአዊ መብቶች ተኮር አሠራር (Human Rights Based Approach) እና በዘላቂ የልማት ግቦች (Sustainable Development Goals) ላይ ያተኮሩ 20 የገጽ ለገጽ የአሰልጣኞች ስልጠናዎች እና ስልጠናዎች በአጠቃላይ 593 ለሚሆኑ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ ፖሊሶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትና ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች መሰጠቱ ተገልጿል። በተጨማሪም በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የአሰልጣኞች ስልጠና የወሰዱ ሰዎች በ7 የስልጠና መድረኮች ስልጠናዎችን መልሰው (training cascading) እንዲሰጡ በተደረገ ድጋፍ በድምሩ 286 ሰዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉም ተገልጿል፡፡ በበይነ መረብ አማካኝነት መሰል ስልጠናዎችን ለመውሰድ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች በተያዙ ሰዎች መብቶች ክትትል እና በሴቶች መብቶች ላይ ያተኮሩ 2 የበይነ መረብ የስልጠና መርኃ ግብሮች ተዘጋጅተው ተደራሽ መደረጋቸው እና በአጠቃላይ 1579 ሰዎች ስልጠናዎቹን ወስደው የምስክር ወረቀት የወሰዱ መሆናቸው ተጠቁሟል።

የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች የሥራ ክፍል በዘርፉ የተለያዩ ተግብራትን ማከናወኑ እና ከእነዚህም መካከል ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹ መሆናቸውን እና የተማሪዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን እንዲሁም በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና የሕፃናት ፍትሕ የማግኘት መብትን በተመለከተ የምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ክትትሎችን በማከናወን ስኬቶችንና ተግዳሮቶችን መለየቱ፣ ያልተፈጸሙ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ ተከታታይ ውትወታ ማድረጉ ተጠቅሷል።

በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል በተለይም የማኅበረ ሥነ-ልቦና ጉዳት ያለባቸው ሰዎች የጤና መብት እንዲሁም የአካል ድጋፍ ተሐድሶ አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን የተመለከቱ 2 የሰብአዊ መብቶች ክትትሎች መደረጋቸው ተገልጿል። ቀደም ሲል በአረጋውያን እንክብካቤ ማእከል የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ባላቸው ተደራሽነት ላይ በተደረጉ የሰብአዊ መብቶች ክትትሎች መነሻነት በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ላይ ክትትል መደረጉ ተመላክቷል። በተጨማሪም በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የውይይት መድረኮችን ጨምሮ በርካታ የውትወታ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት መከናወናቸው በሥራ ክፍሉ በዝርዝር ማሳያዎች ተገልጿል።

የኢሰመኮ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የስደተኞች እና የፍልሰተኞች መብቶች የሥራ ክፍል በመንፈቅ ዓመቱ 11 ክትትሎችን ማከናወኑ በውይይቱ ተነስቷል። የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች፤ የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች መብቶች እና ኢመደበኛ ፍልሰትን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ስደተኞች በሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች፤ ከጅቡቲ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ሁኔታን እና በምሥራቁ የፍልሰት መንገድ (Eastern Migration Route) ያለውን የፍልሰተኞች እና በሰው የመነገድ ወንጀል ሰለባዎች ጥበቃን በተመለከተ በድሬዳዋ ከተማ እና ደዋሌ የተመላሾች ማእከል የሰብአዊ መብቶች ክትትሎች መደረጋቸው ተመላክቷል። በክትትሎቹ በተለዩ ግኝቶች እና ግኝቶቹን መሠረት በማድረግ በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ላይ ያከናወናቸው የውይይት፣ ምክክር እና ውትወታ ተግባራትም ቀርበዋል።

በሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ሥራ ክፍል አማካኝነት የመገናኛ ብዙኃን እና መረጃ ነጻነትን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ እና በ7 ክልሎች የዳሰሳ ጥናት መደረጉ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ለኢትዮጵያ በሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች አፈጻጻም ላይ በ20 የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ክትትል መከናወኑ እንዲሁም የፍትሐ ብሔር ግዴታን ባለመወጣት ምክንያት የሚፈጸም እስርን በተመለከተ በ4 ክልሎች ክትትል መደረጉ በውይይቱ ተገልጿል። በተጨማሪም ፍትሕ የማግኘት መብት ጥበቃ ላይ በ3 ክልሎች በተካሄደ ክትትል በተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ መዘጋጀቱ፣ በጋዜጠኞች ጥበቃና ሕጋዊ ከለላ ላይ ያተኮረ ተከታታይ የባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መዘጋጀቱ እና በረቂቅ ሕጎች ላይ ከሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች አኳያ ግምገማዎችና አስተያየቶች ለሚመለከታቸው አካላት መሰጠታቸው በመንፈቅ ዓመቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቅሰዋል።

ዶ/ር አብዲ ጅብሪልየኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኀበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር

በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል የተከናወኑ ዐበይት ተግባራት እና የተገኙ ውጤቶች በውይይቱ የቀረቡ ሲሆን፣ በቂ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብትን እና በአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት መብት አተገባበርን በተመለከተ የሰብአዊ መብቶች ክትትሎች የተደረጉ መሆኑ እና በክትትሉ በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መደረጉ በውይይቱ ተነስቷል። የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ብሔራዊ መርኃ ግብር ዝግጅትን በተመለከተ ለባለሙያዎች ኮሚቴ እና ለሚከናወኑ የምክክር መድረኮች ግብዓት የሚሆን ማብራሪያ መዘጋጀቱ እንዲሁም በንግድ እና ሰብአዊ መብቶች (business and human rights) ላይ ያተኮረ የዐቅም ግንባታ ስልጠና ለንግዱ ማኅበረሰብ መሰጠቱ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዘርፍ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የተገለጹ ናቸው።

በኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት አማካኝነት ኢሰመኮ እንደ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም አግባብነት ባላቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሂደቶች/ተቋማት (human rights mechanisms) ለምሳሌ በአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን፣ በተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት፣ በአፍሪካ የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ኅብረት እና በዓለም አቀፍ የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ጥምረት ጉባኤዎች ላይ በመሳተፍ ዓላማውን እና ተልዕኮውን መሠረት ያደረጉ ውጤታማ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎችን ማከናወኑ ተመላክቷል። በተጨማሪም በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ሂደቶች እና ከሂደቶቹ በሚመነጩ ምክረ ሐሳቦች ውጤታማ አፈጻጸም ላይ ያተኮሩ የዐቅም ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸው፣ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰብአዊ መብቶችንና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ባከበረ መልኩ እንዲተገበር የማማከር፣ ዐቅም የመገንባት፣ ግንዛቤ የማስጨበጥ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ የድጋፍ ሥራዎች መከናወናቸው ተጠቁሟል።

ብርሃኑ አዴሎ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ለሁለት ቀናት በቆየው የግምገማና ውይይት መርኃ ግብር በሌሎች የኢሰመኮ የሥራ ክፍሎች የተከናወኑ ተግባራት፣ የተገኙ ስኬቶች እና ያጋጠሙ ችግሮችም በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና ውይይት መርኃ ግብሩ ኢሰመኮ ተቋማዊ ነጻነቱን ጠብቆ የሰብአዊ መብቶች ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ያሳየ መሆኑን ገልጸው፣ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች የቀረቡት ሪፖርቶች ይህንኑ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይም ኢሰመኮ በልዩ ትኩረት ከፌዴራል እና ከክልል መንግሥታት የሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚ እና ዳኝነት አካላት ጋር ያደረጋቸው ተከታታይ የተናጠልና የጋራ ውይይቶች እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር ያለው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል ኢሰመኮ ከሰብአዊ መብቶች ጥበቃ፣ ጥሰቶችን አስቀድሞ ከመከላከል እንዲሁም ጥሰቶች በሚፈጸሙበት ወቅት የተቀናጀ ምላሽ ከመስጠት አንጻር አበረታች ተግባራት እንዲያከናውን ቁልፍ ሚና የተጫወቱ መሆናቸውን በተለያዩ ማሳያዎች አስረድተው፣ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው በጎ እርምጃዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። ኢሰመኮ በመንፈቅ ዓመቱ ላስመዘገበው አበረታች የዕቅድ አፈጻጸም ለሠራተኞች ሙያዊ ብቃት፣ ሥነ-ምግባር እና ትጋት ዕውቅና በመስጠት፣ ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎቹን ጥራት እና ተደራሽነት ለማጠናከር የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል። ዋና ኮሚሽነሩ ኢሰመኮ በአርባ ምንጭ፣ ቦንጋ፣ ደሴ፣ ባሌ ሮቤ እና ሆሳእና ከተሞች ያደራጃቸው 5 አዳዲስ የከተማ ጽሕፈት ቤቶች በአጭር ጊዜ መደበኛ ሥራቸውን በሙሉ ዐቅም እንዲያከናውኑ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።